October 27, 2023 – DW Amharic 

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ በፀጥታ አካላት የጅምላ እሥር እየተፈጸመ ነው ሲሉ ነዋሪዎች ለዶቼቬለ ተናገሩ። ነዋሪዎች እንዳሉት «ባለፉት ጥቂት ቀናት ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ የከተማይቱ ሰዎች ከመንገድና ከመኖሪያ ቤቶቻቸው ታፍሰው ተወስደዋል“።

ባለፈው ሳምንት በጉራጌ እና በቀቤና ብሔር አባላት መካከል ተከሰተ በተባለ ግጭት አራት ሰዎች ከሞቱና ሌሎች አሥራ ስድስት ከቆሰሉ በኋላ እንቅስቃሴዋ ተቀዛቅዞ በነበረው በወልቂጤ አሁን አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል ተብሏል። ይሁንና የከተማዋ ነዋሪዎች በፀጥታ ኃይሎች እየተፈጸመ ነው ያሉት የጅምላ እሥር ግን ሥጋት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል ፡፡ ባለፉት ጥቂት ቀናት ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመንገድና ከመኖሪያ ቤቶቻቸው ታፍሰው መወሰዳቸውን ነዋሪዎቹ ለዶቼቬለ ገልጸዋል ። ከትናንት በስቲያ ረቡዕ የፌዴራልና የዞን ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች ወደ መኖሪያ ቤታቸው በመግባት ሁለት ልጆቻውን ይዘውባቸው እንደሄዱ ለዶቼ ቬለ የተናገሩት አንድ የከተማዋ ነዋሪ “ ልጆቼ በወንጀል ሊያስጠረጥራቸው የሚችል ነገር በሌለበት የፀጥታ አባላት እየደበደቡ ይዘዋቸው ነው የሄዱት ፤ ላለፉት ሁለት ቀናት የት አንደታሰሩ እንኳን ማወቅ አልቻልኩም ነበር ፤ ከብዙ ፍለጋ በኋላ በከተማው “ አይሪሽ “ ተብሎ በሚጠራው አዳራሽ ውስጥ ከሌሎች ወጣቶች ጋር መታሠራቸውን ለማረጋገጥ ችያለሁ “ ብለዋል ፡፡

ዶቼ ቬለ የጅምላ እስር ስለተባለው የጉራጌ ዞን ባለሥልጣናትን ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ አልተሳካለትም ፡፡ ሆኖም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ ሰሞኑን ለመንግሥት ቅርበት ላላቸው የብዙሃን መገናኛዎች በወልቂጤ ከተማ አለመረጋጋት ሰፍኖ መቆየቱን ገልጸው የዚህ ምክንያቱ አዲሱን አደረጃጀት ያልተቀበሉ ቡድኖች በወጣቶች መካከል የተፈጠረውን ፀብ የብሄር መልክ ለማስያዝ በመሞከራቸው ነው ሲሉ ተናግረዋል ፡፡ ሃላፊው እስከአሁን የታሠሩ ሠዎችን በቁጥር አይጠቅስም። ግጭቱን በማስተባበርና በመሳተፍ ለሰውና ለንብረት ጉዳት ምክንያት ሆነዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች እየተያዙ እንደሚገኙ መናገራቸውን የሀዋሳው ወኪላችን ሸዋንግዛው ወጋየሁ ዘግቧል።