
27 ጥቅምት 2023
አሜሪካ በምሥራቃዊ ሶሪያ ውስጥ በሚገኙ ሁለት ወታደራዊ ተቋማት ላይ የአየር ደብድባ መፈጸሟን አስታወቀች።
የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት ፔንታገን ባወጣው መግለጫ በአየር ድብደባው የተመቱት ወታደራዊ ተቋማት በኢራን እና የኢራን ተባባሪ በሆኑ ቡድኖች ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበሩ ናቸው ብሏል።
በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር አርብ ንጋት ላይ በአሜሪካ ኤፍ-16 የጦር ጄቶች በተፈጸመው የአየር ጥቃት ኢራን ጦር መሳሪያ እና ተተኳሽ ለማከማችት የምትጠቀምበት ስፍራ ወድሟል ተብሏል።
የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን አአገራቸው ይህን እርምጃ የወሰደችው በኢራቅ እና ሶሪያ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠራዊት አባላትን ለመጠበቅ እና በቅርቡ በኢራን የሚደገፉ ቡድኖች ላደረሱት ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ነው ብለዋል።
መከላከያ ሚንስትሩ በኢራን የሚደገፉ ቡድኖች በአሜሪካ ጦር ሠራዊት ላይ የሚያደርሱት ጥቃት የማይቆም ከሆነ አሜሪካ አሁንም ተመሳሳይ እርምጃዎችን መውሰዷን ትቀጥላለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
- የዳጋሎ ኃይል የአገሪቱን ጦር ኃይል ከሱዳን ሁለተኛ ትልቋ ከተማ ማስወጣቱ ተገለጸ27 ጥቅምት 2023
- የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በጋዛ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረስ ድምጽ ሊሰጥ ነው22 ጥቅምት 2023
- የግጭቱ ሰለባ ሆነው ሞታቸው ያልታመነላቸው የ4 ዓመቶቹ የፍልስጥኤም እና የእስራኤል ሕጻናት27 ጥቅምት 2023
የእስራኤል እና የሐማስ ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በኢራቅ እና ሶሪያ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠራዊት አባላት እና ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ 12 ጥቃቶች የተፈጸሙ ሲሆን፣ በዚህም ከ20 የማያንሱ የአሜሪካ ሠራዊት አባላት ጉዳት እንደደረሰባቸው ፔንታገን አስታውቋል።
በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) እና በሮኬት የሚፈጸሙትን ጥቃቶች እያደረሱ ያሉት በኢራን የሚደገፉ እና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ናቸው ትላለች አሜሪካ።
ኢራን በሌባኖስ የሚንቀሳቀሱትን ሐማስ እና ሒዝቦላህን በቁስ እና በገንዘብ ትደግፋለች። ይሁን እንጂ እነዚህ ሁለት ቡድኖች ጥቃቶቹን ስለማድረሳቸው በስም አልተጠቁም።
አሜሪካ በሶሪያ 900፣ በኢራቅ ደግሞ 2 ሺህ 500 ወታደሮች አስፍራ የምትገኝ ሲሆን፣ ትናንት ሐሙስ ተጨማሪ 900 ወታደሮችን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንደምትልክ አስታውቃለች።
ኦስቲን ይህን የአየር ጥቃት በእስራኤል እና ሐማስ መካከል እየተደረገ ካለው ጦርነት ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር የለም ያሉ ሲሆን፣ የአየር ጥቃቱም ከእስራኤል ጋር በቅንጅት የተደረገ አይደለም ብለዋል።
ይሁን እንጂ ይህ የአየር ጥቃት በመከላከለኛው ምሥራቅ ያለውን ውጥረት ከፍ አድርጎታል።