
27 ጥቅምት 2023
የጋዛ ሰፈሮችን ወደ ፍርስራሽ ክምርነት የቀየሩት የእስራኤል አየር ጥቃቶችን በድፍረት ሲዘግቡ ከነበሩት አንዱ ዋኤል አልዳህዱ ነው።
ዓለም ትኩረቱን ሁሉ በጋዛ ሰርጥ ላይ ባደረገበት ወቅት አልዳህዱ ከጋዛ ተሰሚ ድምጾች አንዱ ሆኗል።
በባለፉት ሦስት ሳምንታትም የአልጀዚራ ተመልካቾች የማያባሩ የአየር ጥቃቶችን ከአልዳህዱ ዘገባ ሲከታተል ነበር።
ከጥቂት ቀናት በፊትም እንደተለመደው በማዕከላዊ ጋዛ የተፈጸመውን የአየር ጥቃት ሪፖርት አድርጎ ነበር።
በዚህ ጥቃት ግን ቤተሰቦቹ እንደተገደሉ አላወቀም።
ኑሴይራት በተሰኘው የስደተኞች መጠለያ ላይ በተፈጸመው የአየር ጥቃት የሰባት ዓመት ታዳጊ ሴት ልጁን ጨምሮ ባለቤቱ፣ ሌላኛው ወንድ ልጁ እንዲሁም የልጅ ልጁ ተገድለዋል።
አልዳህዱ በዴይር ኤል ባላህ በሚገኘው የአልአቅሳ ሰማዕታት ሆስፒታል በአስከሬን ክፍል ውስጥ ከወንድ ልጁ አስከሬን አጠገብ ተንበርክኮ ሲያነባ፣ ፊቱን ሲነካካ እንዲሁም ባለቤቱ አስከሬን አጠገብ ተጎንብሶም አልጀዚራ አሳይቷል።
የሰባት ዓመት ሴት ልጁን ሻም ሕይወት አልባ አካል አቅፎ በደም የተለወሰ ፊቷን አተኩሮ እያየ ሲያነባም በርካታ ሚዲያዎች ተቀባብለውታል።
- በጋዛ የካቶሊክ መነኮሳት፡ “ሕዝባችንን ጥለን ወደ የትም አንሄድም”27 ጥቅምት 2023
- የጋዛን ሰፈር ወደ ፍርስራሽ ክምርነት የቀየረው ጥቃት24 ጥቅምት 2023
- 90 ሰዎችን ያስጠለለው ባለአራት መኝታው የጋዛ መኖሪያ ቤት22 ጥቅምት 2023

እስራኤል በጋዛ ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት የአልጀዚራ አረብኛ ቢሮ ኃላፊ የሆነው አልዳህዱ ቤተሰቦች መገደሉን በማውገዝ አልጀዚራ መልዕክቱን አስተላልፏል።
በዚህ ጥቃት የዋኤል አልዳህዱ ባለቤት፣ እንደ አባቱ ጋዜጠኛ መሆን የሚፈልገው የ15 ዓመቱ ታዳጊ ልጁ፣ የሰባት ዓመት ሴት ልጁ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት እንደተገደሉም አልጀዚራ በመግለጫው እንዲሁም በዘገባው አሳውቋል።
ከሁለት ሰዓታትም በኋላ የአንድ ዓመት ከስድስት ወር ዕድሜ ያለው አዳም የተሰኘው የልጅ ልጁም መገደሉን ጨምሮ አልጀዚራ ዘግቧል።
አልጀዚራ የጋዜጠኛው ቤተሰቦች መገደልን በማውገዝ መግለጫ አውጥቷል።
“እስራኤል ሰላማዊ ሰዎችን ባልለየው የአየር ጥቃቷ የዳህዱ ባለቤት፣ ወንድ ልጅ እና ባለቤቱ በአሳዛኝ ሁኔታ ተገድለዋል። የተቀሩት ቤተሰቦቹ ደግሞ በፍርስራሹ ስር ተቀብረዋል” ሲል የአልጀዚራ ባወጣው መግለጫ አትቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሰላማዊ ዜጎች ከሰሜን ጋዛ እንዲወጡ ያስተላለፉትን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ ቤተሰቡ ወደ ኑሴይራት የስደተኞች መጠለያ ካምፕ መፈናቀላቸውንም የአልጀዚራ መግለጫ አክሏል።
“በኑውሴይራት የስደተኞች መጠለያ የነበረውም ቤታቸውም በአየር ጥቃቱ ኢላማ መደረጉን” መግለጫው አስፍሯል።
እስራኤል በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሰሜን ጋዛ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ መስጠቷን ተከትሎ በርካቶች ወደ ማዕከላዊ እና ደቡብ ጋዛ ሸሽተዋል።
የጋዜጠኛው ቤተሰቦችም ሸሽተው ኑውሴይራት በተሰኘው የስደተኞች መጠለያ ተጠግተው ይገኛሉ።
የጋዜጠኛው የ15 ዓመት ልጁ ማህሙድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ዘንድሮው ያጠናቅቅ ነበር።
ሌሎች የቤተሰቡ አባላት በፍርስራሹ ወስጥ ተቀብረው የነበረ ሲሆን፣ የተወሰኑት በሕይወት መትረፋቸው ተገልጿል።
የእስራኤል መከላከያ የአልዳህዱ ቤተሰብ አባላት በተገደሉበት አካባቢ በሐማስ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጧል።
እስራኤል በጋዛ ላይ ባደረሰችው የአየር ጥቃት የጋዜጠኛው ቤተሰብን ጨምሮ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን በተመለከተ ቢቢሲ ለእስራኤል መከላከያ ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ቃለ አቀባይ ሌተናል ኮሎኔል ሌርነት “የማንኛውም ሰው ሕይወት መቀጠፍ አሳዛኝ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
አልዳህዱ ቤተሰቡ በአየር ጥቃቱ መገደላቸውን ካወቀ በኋላ ከአልጀዚራ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ “የሆነው ነገር ግልጽ ነው። ይህ በሕጻናት፣ በሴቶች እና በሰላማዊ ዜጎች ላይ በተከታታይ ያነጣጠረ ጥቃት ነው። ማንም ቢሆን ከዚህ ጥቃት እና ከዚህ ወረራ አይድንም” ሲልም ተደምጧል።
አልዳህዱ በጋዛ የአልጀዚራ አረብኛ ቢሮ ኃላፊ ሲሆን፣ ለበርካታ ዓመታትም በሚዲያው በጋዜጠኝነት አገልግሏል። ለዓመታት በከበባ ላይ ያለችው የጋዛ ታሪክ ትኩረት እንዲያገኝ ካደረጉት ጋዜጠኞችም አንዱ ነው።
አልጀዚራ ሌሎች ሠራተኞቹን በተመለከተ መግለጫ ያወጣ ሲሆን “በጋዛ ያሉ ባልደረቦቻችን ደኅንነት እና ሰላም በጣም ያሳስበናል። የእስራኤል ባለሥልጣናት ለደኅንነታቸው ተጠያቂ ናቸው” ብሏል።

አክሎም “ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ ገብቶ በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት እንዲቆም እና የንጹሃን ሕይወት እንዲጠብቅ እናሳስባለን” ሲልም ጥሪ አቅርቧል።
ሦስት ሳምንታት ገደማ ባስቆጠረው ጦርነት ቢያንስ 24 ጋዜጠኞች በጋዛ መገደላቸውን የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ኮሚቴ ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስት (ሲፒጄ) አስታውቋል።
እስራኤል ሐማስ ላደረሰው መብረቃዊ ጥቃት ምላሽ ነው በሚል የማያባራ የአየር ጥቃት እየፈጸመች ትገኛለች።
ሐማስ ባደረሰው ጥቃት 1 ሺህ 400 ሰዎች ተገድለዋል እንዲሁም ከ200 በላይ ሰዎች ታግተዋል።
እስራኤል አጠናክራ በቀጠለችው የአየር ጥቃት ከ7 ሺህ በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ከእነዚህም አብዛኛዎቹ ሕጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
እስራኤል ጋዛን በሙሉ ከበባ ውስጥ ያስገባቻት ሲሆን በዚህም የነዳጅ፣ የመብራት እና የውሃ አቅርቦት እንዲቋረጥ አድርጋለች።
በአሁኑ ጊዜ አነስተኛ መጠን ያለው እርዳታ በግብፅ በኩል እየገባ ሲሆን፣ የረድዔት ድርጅቶችም ሁኔታው አስከፊ እንደሆነ በመጥቀስ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ።
