
ከ 8 ሰአት በፊት
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት ነው የተወለደው።
አባቱ በናዚ ሠራዊት አገልግለዋል። እናቱ በመከራ ተራምደዋል። እሱ ድህነት አሳርሮ ቆልቶት ነው ያደገው።
በልጅነቱ የሚበላው አጥቶ ርቦታል። “ያ አስቸጋሪ ረሃብ ነው በኋለኛው ሕይወቴ ለስኬት እንድራብ ያደረገኝ” ይላል።
15 ዓመት ሲሞላው ከሚያገኘው ገንዘብ ለእናቱ መስጠት ነበረበት፤ እራቱን ለመብላት።
ይህ ፈታኝ ሁኔታ ነው ከኦስትሪያ እንዲሰደድ ያደረገው።
አባቱ ሁልጊዜም ይተቹት ነበር፤ የበለጠ እንዲተጋ ነው ነገሩ። የታንክ ሾፌር እንዲሆን ነበር ፍላጎታቸው። እሱ ግን ሰውነቱን የታንክ ጎማ ማስመሰልን መረጠ። በለስ ቀንቶት በጡንቻ ማጎልመስ ዘርፍ የዓለም አነጋገሪው ሰው ሆነ።
ይህን ስኬት ከመቀዳጀቱ በፊት ግን ከታንክ እና ከድህነት ሽሽት መግባት ነበረበት። እናት አገሩ ኦስትሪያ ለዚህ ሕልሙ አትሆንም።
ከኦስትሪያ ሙኒክ – ጀርመን ከዚያም ደግሞ አሜሪካ ገባ።
አሜሪካ እንደገባ ‘አሜሪካን ድሪም’ [የአሜሪካ ሕልም] የሚሉትን ማለም ጀመረ። በሰውነት ማጎልመስ፣ ከዚያም በሲኒማ፣ ከዚያም በቢዝነስ፣ ከዚያም በፖለቲካ ታላቅ ስኬትን ተቀዳጀ።
አኖልድ ሽዋዝኒገር ከሰሞኑ ለንደን ነው ያለው። መጽሐፉን እያስመረቀ ነው።
አዲስ አነቃቂ መጽሐፍ ጽፏል። “ቢ ዩዝፉል፤ ሰቨን ቱልስ ፎር ላይፍ” ይሰኛል።
“ጠቃሚ ሰው ሁን፤ ሕይወት እንዲሰምር የሚያስችሉ 7 መንገዶች” ሊባል ይችላል በደምሳሳው ሲተረጎም።
መጽሐፉ በብዙዎች ሃያሲያን ከወዲሁ “አበጀህ” እየተባለ ነው። በበጎ ሂስ እየተምነሸነሸ ነው።
ለምሳሌ ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ ብዙም የሪፐብሊካን ወዳጅ አይደለም። ሽዋዝኒገር ደግሞ ቅልጥ ያለ ሪፐብሊካን ነው። ዘ ጋርዲያን መጽሐፉን “ሕይወትን ለማቅናት የሚሆን ቀና መጽሐፍ” ሲል አወድሶታል።
ሎሳንጀለስ ታይምስ ግን ብዙም የወደደለት አይመስልም። “ጡንቻ ያላፈረጠመ ኮስማና መጽሐፍ” ሲል ለማፌዝ ሞክሯል።
መጽሐፉ ሰባት ምዕራፎች አሉት። ከእነዚህ መሀል “ዐይንህ እስኪጠፋ ድረስ በርትተህ ሥራ”፣ “አፍህን ዝጋው፤ አእምሮህን ግን ክፈተው” የሚሉ ምዕራፎችም ትኩረት የሚስቡ ናቸው።
- ከጆ ባይደን የአሜሪካን ትልቅ ሽልማት የተቀበሉት ተመራማሪው ፕ/ር ጋቢሳ ኤጄታ ማን ናቸው?25 ጥቅምት 2023
- ከ25 ዓመት በላይ ባሕር ማዶ ቆይታ በእንግሊዘኛ መጻሕፍትን የጻፈችው ኢትዮጵያዊት ደራሲ22 ጥቅምት 2023
- ጡረታ ከወጡ በኋላ አሁንም ሥራቸው ላይ የሚገኙት በጎ ፈቃደኛው ትራፊክ ፖሊስ25 ጥቅምት 2023
አኖልድ ሽዋዝኒገር እንዴት አነቃቂ መጽሐፍ ፀሐፊ ሆነ?
“ይህን ነገር በጭራሽ አስቤው የማውቀው ነገር አልነበረም” ይላል፤ አጋጣሚዎች ወደዚህ እንዳመጡት ሲናገር። “አነቃቂ ተናጋሪ እና የአነቃቂ መጽሐፍ ፀሐፊ እሆናለሁ አላለም።”
“ምክንያቱም ልጅ ሳለሁ ሕልሜ ሁሉ አንድ ነበር፤ ከዓለም አንደኛ ባለ ትልቁ ጡንቻማ ሰው መሆን።”
ከዓመታት ጥረት በኋላ በቦክስ ኦፊስ አንድ ሁለት ሥራዎቹ ዕይታን ሲስቡለት ነገሮች ተለወጡ።
በተለይም ኮናን ዘ ባርቤሪያን (Conan the Barbarian) እንዲሁም ትዊንስ (Twins) እና ትሩ ላይስ (True Lies) የሽዋዝኒገርን ሕይወት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ቀየሩት።
ከዚህ በኋላ በዓለም ቁጥር አንድ ጡንቻማ ሰው የመሆን የመጨረሻ ሕልሙ በአዳዲስ ሕልሞች ተተካ።
ለምሳሌ ሰዎችን ወደ በስኬት ጎዳና በሚያደርጉት ጉዞ መርዳት።
“ሰዎች መነቃቃት አለባቸው። ከየት ተነስቼ ምን እንዳሳካሁ ይጠይቁኛል። ሰዎች መነቃቃት ያሻቸዋል” ይላል ሽዋዝኒገር።
አነቃቂ እና አጋዥ መጽሐፍ የደካማነት ሥነ ልቦና ልጆች ይሆኑ?
ሽዋዝኒገር ከዚህ የተለየ ሐሳብ አለው።
“ምን መሰለህ፤ አንድ የተሳሳተ አስተሳሰብ አለ። እገዛ መጠየቅ የሚለው ቃል ድክመት ሆኖ ይታየናል። እኔ ግን ሌሎችን መርዳትን በሌሎች መረዳትም እንዳለብን ይሰማኛል።”
አኖልድ ሽዋዝኒገር ሰዎች ደጋግመው አንድ ነገር ሲሉት ይበሳጫል። ብስጭቱ ወደ ጡጫ መሰንዘር ባይሻጋገርም ብሽቅ ይለዋል።
“ሰዎች ይመጡና አንተ እኮ በቃ ራስህን የፈጠርክ ሰው ነህ ይሉኛል። እንደዚህ ሲሉኝ ደስ አይለኝም። ሁላችንም እኮ እርዳታ እንሻለን” ይላል።

አኖልድ ሽዋዝኒገር እዚህ ለመድረሴ ምክንያት ናቸው የሚላቸውን በርካታ ሰዎች ይጠቅሳል። 5 ሚሊዮን ሕዝብ ድምጽ ባይሰጠው የካሊፎርኒያ አገረ ገዥ መሆን አይችል እንደነበር ቀላል ምሳሌ በመስጠት ሁላችንም በሌሎች ትከሻ ላይ እንዳለን ለማስረዳት ይሞክራል።
አኖልድ ሽዋዝኒገር ሌሎችን ሲረዳም ነው የኖረው። በተለይ ላለፉት ሦስት አሥርታት ብዙ በጎ ተግባራት ውስጥ ነበር። በወረርሽኙ ጊዜ ለምሳሌ አንድ ሚሊዮን ዶላር ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ሠራተኞች ለግሷል። ለስፔሻል ኦሊምፒክስ ብዙ እርዳታ አድርጓል።
ሰዎች ሽዋዚንገርን ሲያዩት ስኬት እና ማሸነፍ፣ በድል ላይ ድል መደራረብ እና መነቃቃትን ብቻ ነው የሚመለከቱት። “ነገር ግን በሕይወቴ ዝቅታም ከፍታም ነበር” በማለት “ድብታ ሽው አላለብኝም ብዬ አልዋሽም” ይላል።
በሰውነት ማጎልመስ ውድድር ሽንፈት መቅመሱን፣ ውድቀት የደረሰባቸው ፊልሞቹን ያነሳሳል። በትዳሩ ላይ የገጠመውን ፈተናም እንዲሁ።
ሽዋዝኒገር በዚህ መጽሐፉ ከልጁ ተንከባካቢ ጋር የነበረውን ግንኙነት፤ በትዳሩ መማገጡን ወዘተ ብዙም በዝርዝር አያነሳቸውም። ይህን ተከትሎ ከባለቤቱ ከማሪያ ሽሪቨር ጋር መለያየቱን አይዘረዝርም። የቀድሞ ባለቤቱ የጆን ኤፍ ኬኔዲ የእህት ልጅ ናት።
እነዚህን ነገሮች በ2012 (እአአ) በጻፈው ቶታል ሪኮል (Total Recall) ግለ ታሪኩ ነካክቷቸዋል።
ሽዋዝኒገር በአመዛኙ በአሜሪካ ታላቅ ስኬትን መቀዳጀት እንደሚቻል ማሳያ ታላቅ ምሳሌ ተደርጎ ይታያል። ማንኛውንም ነገር የማሳካት ተንቀሳቃሽ ሐውልት አድርገው የሚያዩትም ብዙዎች ናቸው።
ነገር ግን አንድ ነገር መሆን አይችልም። የአሜሪካ ፕሬዝዳንት። ምክንያቱም እሱ አሜሪካዊ እንጂ አሜሪካ አልተወለደም። ሕገ መንግሥቱ ደግሞ አሜሪካ ላልተወለደ ይህን ዕድል አይፈቅድም።
ሽዋዝኒገር ተወልዶ ያደገው በኦስትሪያ ነው። እስከ 19 ዓመቱ እዚያው ነበር።
ለመሆኑ ብዙ ሕልም አሳክቶ እዚህ ከደረሰ በኋላ ፕሬዝዳንት መሆን አለመቻሉ ያበሳጨው ይሆን?
“እውነት ለመናገር ታላቅ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እንደምሆን ይሰማኛል። ባለመሆኔ ግን አልጸጸትም። ይህን ሁሉ ያሳካሁት በአሜሪካ ምክንያት መሆኑ መጽናናትን ይሰጠኛል” ይላል።
“አሜሪካ ምን ያልሰጠችኝ ዕድል አለ? የአሜሪካ ሕዝብ እንግዳ ተቀባይ ነው። በሙሉ ልቡ፣ እጁን ዘርግቶ ነው የተቀበለኝ። ከስኬት ግስጋሴዬ ሊያቆመኝ የሞከረ የለም፤ አሁን አንድ የማልችለው ነገር የአሜሪካ ፕሬዝዳንት መሆን ነው ብዬ፣ ያን ታላቅ ዕድል አጣሁ ብዬ ላማርር ነው? አላማርርም” ይላል አኖልድ ሽዋዝኒገር።
ለፕሬዝዳንትነት መወዳደር ባይችልም ታዲያ በሚቀጥለው ዓመት ትራምፕ እና ጆ ባይደን ዕጩ ባይሆኑ ይመርጣል። በሆነ ተአምር ወጣት እና አዲስ ጉልበት ብቅ እንዲል ተስፋ ያደርጋል።