
ከ 7 ሰአት በፊት
በአሜሪካ፣ ሜይን ውስጥ 18 ሰዎችን ተኩሶ በመግደል የተጠረጠረው የ40 ዓመቱ ሮበርት ካርድ ሞቶ እንደተገኘ ፖሊስ ገለጸ።
ለሦስት ቀናት ፖሊስ ሲያሳድደው ነበር። ነዋሪዎችም ከቤት እንዳይወጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ ነበር።
ራሱ ላይ ተኩሶ ሕይወቱ እንዳለፈ የሜይን የሕዝብ ደኅንነት ኃላፊ ማይክል ሳውሾክ ተናግረዋል።
በግለሰቡ በጥይት ተመትተው ከተገደሉት መካከል ዕድሜያቸው ከ14 እስከ 76 የሚደርስ ይገኙበታል።
አያትና ቦውሊንግ የሚጫወት የልጅ ልጃቸው እንዲሁም አራት መስማት የተሳናቸውም ይገኙበታል።
አገረ ገዢ ጃኔት ሚልስ የግለሰቡ አስክሬን በሊዝበን ከተማ መገኘቱን ገልጸዋል።
“ለማንም ስጋት አይሆንም የሚለውን በማወቄ ዛሬ እፎይታ ተሰምቶኛል” ብለዋል።
የሊዊስተን ፖሊስ ኃላፊ ዴቪድ ሴንት ፒሬ እንዳሉት ግለሰቡ ስጋት ባለመሆኑ ደስተኛ ቢሆኑም ፖሊስ አሁንም ሥራ እንደሚቀረው ገልጸዋል።
“ቤተሰቦቻቸውን ካጡ ጋር እናዝናለን። ሥራችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።
ኮሚሽነሩ እንዳሉት ተኩሱ ረቡዕ ተከፍቶ የግለሰቡ አስክሬን ዓርብ ነው የተገኘው።
የሜይን ሴናተር የሆኑት ሱዛን ኮሊንስ አሁን ሁሉም ሰው እፎይታ ሊሰማው ይገባል ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተኩሱ ከተከፈተ በኋላ “ለሊዊስተን ብቻ ሳይሆን ለመላው አሜሪካ አስጨናቂ ሁለት ቀናት ነበሩ። በድጋሚ አሜሪካዊያን በጅምላ ተኩስ ሰለባ ሆነዋል” ብለዋል።
የመሣሪያ ቁጥጥር በማድረግ ሪፐብሊካኖች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
- “ስኬታማ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የምሆን ይመስለኛል…” አኖልድ ሽዋዝኒገርከ 8 ሰአት በፊት
- የትግራይ አስተዳደር የማያውቀውን ስብሰባ በጠሩ ባለሥልጣናት ላይ እርምጃ መውሰዱን ገለጸ27 ጥቅምት 2023
- ቤተ-እስራኤላዊው አቨራ መንግሥቱ እና ለዓመታት በሐማስ እገታ ሥር ያሉ ሌሎች እስራኤላውያንከ 8 ሰአት በፊት
የተጠርጣሪው ወንድም ባለቤት ኬቲ ካርድ ለኤንቢሲ “ልባችን ተሰብሯል። ቤተሰባችን ፖሊሶችን ለመርዳት የተቻለውን እያደረገ ነው” ብላለች።
ግለሰቡ ተኩስ የከፈተው በአንድ ሬስቶራንትና በቅርብ ርቀት በሚገኝ የቦውሊንግ መጫወቻ ስፍራ ነበር።
በሬስቶራንቱ ሰባት ሰዎች በቦውሊንግ መጫወቻው ስምንት ሰዎችን ገድሏል።
መስማት የተሳናቸው ማኅበር የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት አካሂዷል። አስተባባሪው ቴሪ ሞሬል “ሐዘኔን ለመግለጽ ቃላት የለኝም። አራት ጓደኞቻችንን አጥተናል። ደንግጠናል። አዝነናል። ተቆጥተናል” ብሏል።