ኤርትራ ጦሯን ከኢትዮጵያ ግዛት ሙሉ ለሙሉ እንድታስወጣ የአውሮፓ ኅብረት ጠየቀ
(አዲስ ማለዳ) በኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ መሰረት ኤርትራ ጦሯን ሙሉ በሙሉ ከኢትየጵያ ግዛቶች እንድታስወጣ የአውሮፓ ኅብረት ጠይቋል።
የአውሮፓ ኅብረት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 78ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ጋር በተያያዘ የኤርትራን የሰብአዊ መብቶች ኹኔታ አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥም ሆነ ከትግራይ ክልል ውጭ፤ የኤርትራ ሠራዊት በንጹሃን ዜጎች ላይ “ፈጽሞታል” በተባለው ሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ ተአማኒና ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሄድ አሳስቧል።
ይህም ገለልተኛ ምርመራ መደረጉ በትግራይ ተካሂዶ በነበረው ጦርነት ወቅት ጉዳት የደረሰባቸው ተጎጂዎች ፍትህ እንዲያገኙ ያስችላል ሲል ኅብረቱ ገልጿል።
የአውሮፓ ኅብረት የኤርትራን ሪፖርተር ዋቢ በማድረግ ባወጣው መግለጫ፤ በአገሪቱ ብዙ ሰዎች በዘፈቀደ እየታሰሩ መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን፤ በርካታ ኤርትራውያንም ደብዛቸው ጠፍቶ እስካሁን አለመገኘታቸውን አመላክቷል።
“ይህ በአገሪቱ የሚታየው የዘፈቀደ እስር፣ በግዳጅ መሰወር እንዲሁም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የመሰብሰብ እና የመደራጀት ነፃነት አጠቃቀም ላይ ያለ ከፍተኛ ገደብ፤ የአለም ዓቀፍ የሰብአዊ መብት ሕጎችን የሚጥስ ነው፡፡” ያለው ሕብረቱ፤ አገሪቱ 13 የሚሆኑ የጅቡቲ ጦር ምርኮኞች ያሉበትን ኹኔታ እንድታሳውቅም ጠይቋል።
አሁን ላይ በኤርትራ ያለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ እንደሚያሳስበው የገለጸው ኅብረቱ፤ ኤርትራ የጠፉ ግለሰቦች የሚገኙበትን ቦታ በተመለከተ መረጃ እንድትሰጥና እንዲመለሱ እንድታደርግ እንዲሁም፤ ያለምክንያት የታሰሩት ዜጎችን እንድትፈታ አሳስቧል።
በተጨማሪም ኅብረቱ የኤርትራ መንግሥት ለብሔራዊ አገልግሎት ሕፃናትን ለውትድርና መመልመሉ፤ ለሕዝቡ በተለይም ለወጣቶች ትልቅ ስጋት መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ በአገሪቱ ዋነኛው የስደት ምክንያት ሆኖ መቀጠሉንም አስታውቋል።
ስለሆነም ኅብረቱ ኤርትራ ላልተወሰነ ጊዜ የምትሰጠውን ብሔራዊ አገልግሎት እና ሕፃናትን በግዳጅ የመመልመል ልምድ እንድታቆም ያሳሰበ ሲሆን፤ አገሪቱ ኹሉንም የሰብአዊ መብቶች ማስተዋወቅ እና መጠበቅ የሚያስችል ኹኔታን እንድትፈጥር ጥሪ አቅርቧል።
የአውሮፓ ኅብረት በኤርትራ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ያወጣውን ይህን መግለጫ ተከትሎ፤ ኤርትራ የኅብረቱ ትችት በዛሬው ዕለት ውድቅ አድጋለች፡፡
የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገ/መስቀል በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ አውሮፓ ኅብረት ስለ ኤርትራ ብሄራዊ የውትድርና አገልግሎት ለመናገር ሞራል የለውም በማለት ኅብረቱን ተችተዋል፡፡ ነገር ግን ቃል አቀባዩ ኤርትራ ጦሯን ከኢትዮጵያ ግዛት ሙሉ ለሙሉ እንድታስወጣ ኅብረቱ ያቀረበውን ጥያቄ አስመልክቶ ምንም ያሉት ነገር የለም፡፡
