October 28, 2023

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተጠናቀቀ !

የጥቅምት 2016 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ለተከታታይ 6 ቀናት ማኅበራዊ ፣ መንፈሳዊ እንዲሁም አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ በማሳለፍ በዛሬው ዕለት ተጠናቋል።

ጉባኤው በዛሬ በ 6 ተኛ ቀን ውሎው አስተዳደራዊ ጉዳይን የያዘ የመሪ ዕቅድ ተመልክቶ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ ተጨማሪ ግብዓት ተጨምሮበት ለግንቦት ርክበ ካህናት እንዲቀርብ ወስኗል፡፡

በጸደቁ አጀንዳዎች ላይ ላለፈው አንድ ሳምንት ሲወያይ የቆየው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መንፈስ ቅዱስን አጋዥ በማድረግ መግባባት በሰፈነበት ሁኔታ ጉባኤውን ማጠናቀቁ የተገለጸ ሲሆን በማጠናቀቂያው በሕግ ፣ በመሪ ዕቅድ ትግበራ እና በልዩ ልዩ ጉዳዮች ጥናት ላቀረቡ እና ማብራሪያ ለሰጡ ባለሙያዎች ብፁዕ ወቅዱስ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ምስጋና ማቅረባቸውን ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ገልጸዋል።

በአጠቃላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎችን አስመልክቶ ቅዱስነታቸው ሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም መግለጫ እንደሚሰጡ ተገልጿል።

EOTC TV