አቶ ፈቃዱ ደግፌ

ማኅበራዊ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ወለድ ያለው ብድር እንዳያዋውል ተከለከለ

ሰላማዊት መንገሻ

ቀን: October 29, 2023

በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት አማካይነት የወለድ ክፍያ ያለበት የብድር ውል ማዋዋል እንደማይቻል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ፡፡

በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት በኩል የወለድ ክፍያ ያለበትን የብድር ውል ማዋዋል እንደማይቻል፣ በቅርቡ በብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚሰት አቶ ፈቃዱ ደግፌ ተፈርሞ ለአገልግሎቱ የተላከው ደብዳቤ ያስረዳል፡፡

‹‹የወለድ ክፍያ ያለበትን ብድር ማበደር የሚችለውና ገንዘብ መሰብሰብ የሚችለው ባንክና ማይክሮ ፋይናንስ ብቻ በመሆኑ፣ ግለሰቦች ወለድ በማስከፈል ማበደር አይችሉም፤›› ሲሉ አቶ ፈቃዱ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ግለሰቦች ወይም ከፋይናንስ ተቋማት ውጪ ያሉ የንግድ ድርጅቶች፣ በመካከላቸው የሚያደርጉትን የወለድ ክፍያ ያለበትን ብድር ማዋዋል እንደሚቻልና እንደማይቻል ብሔራዊ ባንክን ጠይቆ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሠረት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተሰጠ የባንክ ወይም የአነስተኛ የፋይናንስ ሥራ ፈቃድ ካልተያዘ በስተቀር፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የባንክ ወይም አነስተኛ የፋይናንስ ሥራ መሥራት በሕግ የተከለከለ ተግባር ነው ሲል በደብዳቤው ተገልጿል፡፡

የፌዴራል ገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 እንደሚገልጸው፣ ብሔራዊ ባንክ ዕውቅና ከሰጣቸው የፋይናንስ ተቋማት ውጪ፣ ቁጠባ እንዲሰበስቡና ብድር እንዲሰጡ በልዩ ሕግ የተፈቀደላቸው የኅብረት ሥራ ማኅበራት ናቸው፡፡

ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ፈቃድ በተሰጣቸው የፋይናንስ ተቋማት ሥራ በሕገወጥ መንገድ እንዲሰማሩና ሕገወጥ የፋይናንስ ሥርዓት ለመፍጠር የወጣ ሕግ አለመሆኑን፣ አገልግሎቱ ለብሔራዊ ባንክ የላከው ደብዳቤው ይገልጻል፡፡

ብሔራዊ ባንክም ከሕግ ድንጋጌዎች ውጭ በብድር መልክ ገንዘብ መሰብሰብና የብድር ተመን አውጥቶ በወለድ ማበደር፣ በብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የተሰጣቸው የፋይናንስ ተቋማት ሥራ ብቻ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ መንገድ ገንዘብ የሚያበድሩ ግለሰቦች በወንጀል የሚያስቀጣቸው ተግባር በመሆኑ፣ በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ማንኛውም የወለድ ክፍያ ያለበት የብድር ውል ማዋዋል እንደሌለበት ብሔራዊ ባንክ ገልጿል፡፡

ከዚህ በፊት በወለድ ሲያበድሩ የነበሩ ግለሰቦች በምን ዓይነት መንገድ ሊጠየቁ እንደሚችሉ አቶ ፈቃዱ መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡