ሲሳይ ሳህሉ

October 29, 2023

ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ

‹‹የሚወጣው አዋጅ አይምለከታቸውም›› የተባሉት አካላት የሚገዛቸው ሕግ የትኛው ነው?

ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ

በኢትዮጵያ ደኅንነት ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች ወደ አገር እንዳይገቡ፣ እንዳይወጡና ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር መልካም የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ከሌላቸው አገሮች የሚጉቡ ዕቃዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ የሚደነግግ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቷል፡፡

‹‹የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች የደኅንነት ማረጋገጫና ቁጥጥር አዋጅ›› በሚለው ረቀቂ አዋጅ ማብራሪያ፣ በአሁኑ ጊዜ በርካታ ዘመኑ ያፈራቸው የቴክኖሎጂ ምርቶች መደበኛ በሆኑ የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎችና መደበኛ ባልሆኑ የአገሪቱ አዋሳኝ ድንበሮች፣ ወደ አገር ውስጥ እየገቡና ከአገር እየወጡ መሆናቸውን፣ ምርቶቹ ሊፈጥሩ የሚችሉትን ከፍተኛ የደኀንነት ሥጋት መከላከል ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የሕዝብ ተወካየች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት (ኢንሳ) የሥራ ኃላፊዎች ጋር ጥቅምት 14 ቀን 2016 ዓ.ም. በረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡ ኢንሳ በተቋቋመበት መሠረት በአገር ውስጥ የመረጃ አነፍናፊ፣ የጥቃት ቴክኖሎጂዎችና የአገርን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ቴክኖሎጂዎች ላይ ቁጥጥር የማድረግ ሥልጣን የተሰጠው ቢሆንም፣ ቁጥጥሩን እንዴት ማካሄድ እንዳለበት የሚረዳው አዋጅ ባለመኖሩ የተዘጋጀ ረቂቅ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል፡፡

በመሆኑም በቀጣይ አዋጁ ፀድቆ ወደ ሥራ ሲገባ ምርቶቹን ወደ አገር ቤት በሚያስገቡ አካላትና ነጋዴዎች ላይ የቅድመ ፈቃድ ምርመራ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

ምርቶቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ የቴክኖሎጂ ምርቶቹ አስመጪዎች የሚያስገቡት ካልተፈቀደላቸውና ጥሩ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ከሌላኛው አገሮች ሊሆን ስለሚችል፣ ጠንካራ ክትትል ይደረጋል ያሉት የኢንሳ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግሥት ሃሚድ ናቸው፡፡

‹‹ይህ የሚደረገው እነዚህ አገሮች የሚልኳቸው ዕቃዎች የአገርን ደኅንነት አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ስለሚሆኑ በጥንቃቄ ለአስመጪዎች የቅድመ ግዥ ፈቃድ መሰጠት ስላለበት ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ዕቃዎቹ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ከደረሱ በኋላ ጊዜንና ወጪን ከማባከን በላይ እንደ ኮንትሮባንድ ተቆጥረው ሊወረሱ ይችላሉ፤›› ብለዋል፡፡

አንድ ምርት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የፈለገ አካል የፈቃድ ማረጋገጫ ሲጠይቅ ሊያስገባ ያሰበውን ምርት ዓይነት፣ ሥሪተ አገር፣ ሞዴል፣ መለያ ቁጥር፣ የምርት ዓመትና በቀጣይ አስተዳደሩ በሚያወጣቸው መመርያዎች መሠረት እንደሚወስን፣ ከማስገቢያ ፈቃድ በተጨማሪ ወደ አገር ለገቡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች የማስለቀቀያ ፈቃድ እንደሚሰጠው በረቂቅ አዋጁ ተደንግጓል፡፡

የኢንሳ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሶሎሞን ሶካ የቴክኖሎጂ ምርቶቹን በሰባት ክፍል ያስቀመጧቸው ሲሆን እነሱም ኤሌክትሮኒክስ፣ ኮምፒዩተር፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽንና የኢንፎርሜሽን ሴኪዩሪቲ (Cryptography)፣ ራዳርና ሳተላይት፣ የሬዲዮ መገናኛ፣ ሌዘርና ሴንሰር (Laser sensors)፣ ናቪጌሽንና አቪዮኒክስ (navigation and avionics) በሚል የተከፈሉ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ለምሳሌ በአንዱ ምድብ ውስጥ እስከ 48 የሚደርሱ በርከት ያሉ የቴክኖሎጂ የምርት ዓይነቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

በዝርዝር ቴክኖሎጂ ምርትነት ከተካተቱት ውስጥ ድሮን፣ ሳተላይት ሬዲዮ ኮሙዩኒኬሽን፣ መኪኖች ላይ የሚገጠሙ የአድራሻ ጠቋሚዎችና ካሜራዎች ይገኙበታል፡፡ እነዚህ መሣሪያዎች ወደ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ተጠቃሚው ለምን አገልግሎት እያዋለው መሆኑን አዋጁ ለኢንሳ በሲስተም የመቆጣጠር ኃላፊነት የሚሰጠው ሲሆን፣ ተጠቃሚው ያስገባውን ዕቃ ሳያስፈቅድ ለሦስተኛ ወገን ማስተላለፍ አይችልም ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ወደ አገር ውስጥ የገቡ መሣሪያዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን በቴክኖሎጂ በተደገፈ መንገድ ፍተሻ ማድረግና በኦዲት የመቆጣጠር ሥልጣን አለው ተብሏል፡፡ ወደ አገር ቤት ተመዝግበው የሚገቡ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ሲገቡ በአድራሻቸው ተመዝግበው እንዲገቡ ይደረግና ኢንሳ በተመዘገቡበት አድራሻ ቁጥጥር ያደርግባቸዋል ተብሏል፡፡

የአፍሪኮም ቴክኖሎጂስ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ባህሩ ዘይኑ ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከሁሉም በፊት ዋናው ጥያቄ መሆን ያለበት አገሪቱ እንዲህ ዓይነት ሕግ ለመደንገግ ከማሰቧ በፊት ይህን ለማስፈጸም የሚያስችል አቅም አለ ወይ? የሚለው ጉዳይ መልስ ማግኘት አለበት፡፡ በአገሪቱ በሙያው የበቃ፣ የሠለጠነና የማስፈጸሚያ ቴክኖሎጂ ባለመኖሩ ምክንያት ኃላፊነት ወስዶ ዕቃዎች እንዲገቡ የሚፈቅድ አካል ባለመኖሩ፣ ብዙ ጊዜ አስቸጋሪ እየሆነ ያለው ጉዳይ አንድ ዕቃ ወደ አገር ቤት ከገባ በኋላ በጉምሩክ ቢያንስ ሦስትና አራት ወራት ሲቆይ እንደሚስተዋል ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህ ሊፈጠር የቻለው አገሪቱ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች ያላቸው ብቃትና የሚመጣው ቴክኖሎጂ የማይገናኙ ከመሆኑ የተነሳ፣ ከውጭ የመጣ ቴክኖሎጂ በመሆኑ ብቻ እንዲዘገይ ይደረጋል፡፡ በዚህ መሀል የሕፃናት መጫወቻ ሳይቀር ያለ ምክንያት ተይዞ ይቆያል፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ከዕውቀት ማነስ የተነሳ ይሆናል በሚል በሥጋት ብቻ የግብርና፣ የማዕድን፣ ወይም በአስቸኳይ የሚፈለጉ የቴክኖሎጂ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ለሚጠበቀው ዓላማ ሳይውሉ ያላግባብ ጊዜና ገንዘብ ሊጠፋባቸው ይችላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም በዘርፉ ያሉ ባለሙዎች ተለይተው ተገቢው ሥልጠና ካልተሰጠና ብቁ ሰው ካልተገኘ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል የሚሉት አቶ ዘይኑ፣ የሉዓላዊነት ጥያቄ መታሰቡ ማንም አገር የሚያደርገው ቢሆንም ኢንቨስትመንትም ሊጎዳ ይችላል ብለዋል፡፡ ‹‹ይህ ሕግ አስፈላጊ መሆኑ ላይ ጥያቄ ላይነሳበት ይችላል፡፡ ነገር ግን ሁሉን ነገር በአንዴ ወስኖ ከማጠር የተወሰነ መነሻ ወስዶ የፊት የፊቱን ማስተካከያ በማድረግ ማሳደግ ይሻላል፤›› የሚሉት አቶ ዘይኑ፣ አደጋ ያመጣል በሚል ብቻ በአንዴ ከውጭ የተገኘን ሕግ እንዳለ አምጥቶ ኮፒ በማድረግ መወሰን ነገሮችን ያወሳስባቸዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

‹‹ለአብነትም በአደጉት አገሮች ለሙከራ የሚደረግ (Regulatory Sandbox) በሚባል የሕግ አሠራር መጀመርያ የታሰበውን ጉዳይ ይሞክሩታል በሒደት እየሞከሩ ሕጉን ያዘጋጃሉ፡፡ ይህ ሳይሆን በአንዴ ሕጉ ይወጣና ነገሩን በማወሳሰብ የታሰበው ዓላማ ሳይሳካና ግቡን ሳይመታ መጨረሻም ሕጉን እንደገና ወደ ማሻሻል ይገባል፡፡ ይህ የሚያሳየው ቅድመ ጥንቃቄና ተገቢውን ክትትል ካለማድረግ የሚመጣ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ማንም ሰው በኢንሳ የፀና ፈቃድ ሳይሰጠው ወደ አገር ውስጥ ይዞ ከገባ እንደ ኮንትሮባንድ ተቆጥሮ በወንጀል የሚያስቀጣው የተከለከሉ ተግባራትን ፈጽሞ ከተገኘ፣ ከአንድ ዓመት እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራትና ከ50 ሺሕ እስከ 100 ሺሕ ብር የሚደርስ ቅጣት ይጣልበታል፡፡ ይሁን እንጂ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ቅጣቱ አንስተኛ በመሆኑ ከሚደርሰው አገራዊ ጥፋት አንጻር እንዲጨምር ጠይቀዋል፡፡

ብዛት ባላቸው የቴክኖሎጂ ምርቶች ወይም በተደራጀ መንገድ የተፈጸመ ከሆነ፣ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ100 ሺሕ ብር እስከ 200 ሺሕ ብር ድረስ ቅጣት ተደንግጓል፡፡

ቴክኖሎጂዎችን በቀላሉ ወደ አገር ውስጥ ይዞ መግባት መሸጥ፣ መለወጥ፣ ማምረት፣ መገጣጠም፣ ማስተዋወቅና ከአገር እንዲወጣ ማድረግ፣ ጥቅም ላይ እንዲውል ማመቻቸት ቁጥጥር ይደረግበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት አንዳንዶች ቴክኖሎጂዎች አሁን እያስተዋወቁ ቢሆንም፣ ኢንሳ በአዋጁ ክትትል እንዲያደርግ ሥልጣን ባለመስጠቱ መሰናክል እንደፈጠረበት ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ለውይይት በቀረበው ረቂቅ አዋጅ እንደተብራራው ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሚሰጠው ፈቃድ፣ ብሔራዊ ደኅንነት ከማስጠበቅ አንፃር የሚሰጡትን ፈቃድና ቁጥጥር የሚያስቀር አለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በረቂቅ አዋጁ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች የሚቆጣጠሩ ባለሙያዎች የቴክኖሎጂ ምርት በሕገወጥ መንገድ በማንኛውም ቦታ ስለመያዙ ወይም ጥቅም ላይ ስለመዋሉ ምክንያታዊ ጥርጣሬ በሚኖርበት ወቅት፣ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከሚመለከታቸው የመንግሥት የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ወደ ተጠረጠረው ቦታ በመግባት ፍተሻና ምርመራ የማድረግ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ የአገር መከላከያ ሠራዊት ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የፌዴራል ፖሊስ የማይመለከታቸው መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ይሁን እንጂ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ ‹‹ይህ አዋጅ አይመለከታቸውም የተባሉ አካላት የትኛው ሕግ ይገዛቸዋል? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

‹‹ይህን ጉዳይ ከፓርላማው ሕግ ክፍል ጋር በመነጋገር ለመረዳት እንችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በየትኛውም አገር ሕግ የማይገዛው አካል ወይም ተቋም መኖር የለበትም፤›› ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ብዙ ተምራበታለች፣ አይመለከታቸውም ሲባሉ የነበሩ ተቋማትን ለብዙ ዓመታት ሲመሩ የነበሩ አካላት፣ ነገር ግን ታማኝ ተብለው ለአገር ያልታመኑ፣ አገር ላይ ክህደት የፈጸሙና ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ሁኔታ በመኖሩ በሕግ ሥልጣን የተሰጠው አካል ወይም የበላይ አካል እነዚህንም የሚቆጣጠርበት አመላካች ነገር ቢኖር ጥሩ ነበር በማለት ለኢንሳን ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ሕግ ይኖራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በዚህ አዋጅ ውስጥ ቅንጅት ላይ ችግር እንዳይፈጠር ማየት ጥሩ ነው፡፡ መከባበር ጥሩ ሆኖ እንዲሁም በሌላ ጎን መታየቱ አስፈላጊ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በረቂቅ አዋጁ ላይ በቅርቡ በይፋ የሕዝብ ውይይት ይካሄድበታል ተብሏል፡፡