

ማኅበራዊ ገቢሳ ኤጄታ (ፕሮፌሰር) ከፍተኛውን የብሔራዊ የሳይንስ ሜዳሊያ ተሸለሙ
ቀን:
October 29, 2023
ትውልደ ኢትዮጵያዊው ገቢሳ ኤጄታ (ፕሮፌሰር) በዕፀዋት ዘረመል ማዳቀል ላይ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የአሜሪካ የሳይንቲስት ቡድን ዕውቅና የሰጠውን የአሜሪካ የብሔራዊ የሳይንስ ሜዳሊያ ተሸለሙ፡፡ ፕሮፌሰሩ የተሸለሙትን ሜዳሊያ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ተቀብለዋል። ገቢሳ (ፕሮፌሰር) በዕፀዋት ዘረመል ማዳቀልና ዓለም አቀፍ ግብርና ተመራማሪ፣ የፑርዱ ግሎባል የምግብ ዋስትና ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ ሽልማቱ አሜሪካ በተለያዩ ዘርፎች ለተሰማሩ ተመራማሪዎች የምትሰጠው ከፍተኛ ዕውቅና ያለው ነው። ገቢሳ ኤጄታ (ፕሮፌሰር) በማሽላ እህል ላይ ሰፊ ጥናት ያደረጉ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ በ2009 የከፋ ድርቅንና አጥፊ አረምን የሚያቋቋም የማሽላ ዝርያ ላይ ባደረጉት ምርምር የዓለም ምግብ ሽልማትን አግኝተዋል። ምርምራቸው ከፍተኛ የማሽላ ምርትን በመጨመር ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመመገብ ረድቷል። ገቢሳ (ፕሮፌሰር) በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ብሔራዊ የክብር ሽልማት ከተሸለሙ 21 አሜሪካውያን ተመራማሪዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡