
ከ 4 ሰአት በፊት
ካሌብ ምዋንጊ ከማለዳዎች በአንዱ ለቁርስ ከሚፈቀድለት በላይ ምግብ አነሳ። ለዚህ ድርጊቱ መቀጣት ነበረበት። ቅጣቱ በአርጬሜ ገላው እስኪተለተል መገረፍ ነበር።
በከፍተኛ ሁኔታም ተደበደበ። ግርፋቱ ከሞት አፋፍ አድርሶ መለሰው። የጽኑ ሕሙማን ክፍል (ICU) ገብቶ ነፍሱ ተረፈች።
“ሆስፒታል ስደርስ ከአልጋው መነሳት አይችልም። መናገርም አይችልም” ይላሉ አባቱ ፈሬድ ምዋንጊ ለቢቢሲ።
ይህ የሆነው የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም ነው። ካሌብ ያን ጊዜ 13 ዓመቱ ነበር።
ካሌብ አሁን በፍርሃት የሚንቀጠቀጥ፣ በብስጭት የሚንቀለቀል፣ በንዴት ግድግዳውን በቡጢ የሚነርት ሞገደኛ ልጅ ሆኗል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሥነ ልቦናው ተጎድቷል፤ ቅስሙ ተሰብሯል። ከሰው ጋር እያወራ ድንገት በሐሳብ እልም ብሎ ይጠፋል።
ያኔ ትምህርት ቤት የደረሰበት ግርፋት በአእምሮው ላይ ከባድ ጠባሳ ጥሎ ሳያልፍ አልቀረም።
አባቱ ምዋንጊ ለቢቢሲ ባልደረቦች የልጃቸውን ገላ ገልጠው አሳዩ። የካሌብ ጀርባ አይሆኑ ሆኗል። ለማየትም የሚሰቀጥጥ ነው። ድብደባው ቆዳውን ክፉኛ ተልትሎታል።
አባቱ እንደሚናገሩት ከጀርባው የተተለተለው ቆዳው ጥልቅ ከመሆኑ የተነሳ በቀዶ ሕክምና ከታፋው ቆዳ ተነስቶ ወደ ጀርባው መምጣት ነበረበት። ሐኪሞቹም ያን ነው ያደረጉት።

ተማሪዎችን በአርጩሜ መቅጣት በኬንያ ረዥም ጊዜን ያስቆጠረ ልማድ ነው። በተለይ ድሮ ሚሽነሪዎች እና ቅኝ ገዢዎች ተማሪዎችን ሰጥ ለጥ አድርገው የሚገዙበት መሣሪያቸው ነበር። የበላይነታቸውን ማሳያም ተደርጎ ይወሰድ ነበር።
እንደ አውሮፓዊያኑ በ2001 የኬንያ መንግሥት ይህን ተግባር ሕገ ወጥ ብሎ ፈርጆታል። ነገር ግን በትምህርት ቤቶች አካባቢ አሁንም ልማዱ አልቀረም።
በልጆች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን የሚዘግብ አንድ ሰነድ ከ18 እስከ 24 ዓመት ዕድሜ ያሉ ኬንያውያን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት እንዲህ ዓይነቱን ቅጣት እንደሚደግፉ ጥናት ሠርቶ አቅርቧል።
የቢቢሲ አፍሪካ አይ (BBC Africa Eye) የምርመራ ዘገባ መርሐ ግብር ይህን ተግባር ሲከታተል ቆይቶ የደረሰበት ነገር ቢኖር ድርጊቱ እየተባባሰ እንጂ እየቀነሰ አለመምጣቱን ነው።
ጀርባው በአርጬሜ የተተለተለው ካሌብ ይህን ድርጊት የፈጸመችብኝ የግሬሞን ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ናንሲ ጋቼዋ ናት ይላል።
ግሬሞን ትምህርት ቤት በባምቡሪ ከተማ ነው። ባምቡሪ ከተማ ደግሞ ከወደብ ከተማዋ ሞምባሳ ብዙም አትርቅም።
- አፄ ኃይለ ሥላሴን የሚዘክር ዝግጅት ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ተካሄደከ 5 ሰአት በፊት
- አሜሪካ ወደ እስራኤልም ሆነ ወደ ጋዛ ወታደር የመላክ ፍላጎት የላትም፡ ካማላ ሐሪስ29 ጥቅምት 2023
- ኬንያ የሁሉም የአፍሪካ አገራት ዜጎች ያለቪዛ ወደ አገሯ እንዲገቡ ልትፈቅድ ነውከ 4 ሰአት በፊት
ካሌብ እንደሚለው የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህርት በአርጬሜ ጀርባውን መተልተሉ ሲደክማት ሌሎች ተማሪዎች እንዲደበድቡት አበረታታለች፤ አሳልፋ ሰጥታዋለች።
ቢቢሲ ናንሲ ጋቼዋን ስለጉዳዩ ጠይቋት እኔ ይህ ድርጊት ሲፈጸም በጭራሸ በትምህርት ቤቱም አልነበርኩም ስትል አስተባብላለች።
ለዚህ ሁሉ አሰቃቂ ቅጣት ካሌብን የዳረገው ምንድነው? በቁርስ ሰዓት በትምህርት ቤቱ ውስጥ ከሚፈቀድለት በላይ ምግብ በመውሰዱ ነበር።
“በጣም ርቦኝ ነበር፤ 5 ቻፓቲ ከሻይ ጋር ግጥም አድርጌ በላሁ” ይላል።
ርዕሰ መምህርት ናንሲ ጋቼዋ እና ኢድ ሳሊም የተባለ ሌላ በዕድሜ ተለቅ ያለ ተማሪ፣ በካሌብ ላይ አደረሱት ስለተባለ ከፍተኛ ቅጣት በቁጥጥር ሥር ውለው ክስ ተመሥርቶባቸዋል።
በዕድሜ ትልቅ የሆነው ኢድ ሳሊም አራት ዓመት ተፈርዶበታል። ሳሌም በርዕሰ መምህርቷም ላይ የመሰከረ ሲሆን የእሷን ጉዳይ ፍርድ ቤት ገና እየመረመረው ነው።
የተማሪ ካሌብ የትምህርት ቤት ቅጣት የከፋ ቢመስልም ይህ ግን በኬንያ ጉድ የሚባል ብቸኛው አጋጣሚ አይደለም።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚፈጸም ቅጣት ከዚህ ቀደም ከነበረው አሰቃቂ ቅጣት በአራት እጥፍ ጨምሯል።
ይህ ብቻ አይደለም አስደንጋጩ መረጃ። ባለፉት አራት ዓመታት ከተመዘገቡ የተማሪዎች ሞት 20 የሚሆኑት ተማሪዎች በገዛ መምህሮቻቸው ድብደባ ደርሶባቸው መሞታቸው ነው።
የ15 ዓመቷ ኢቢ ሳሙኤል ከእነዚህ አንዷ ናት።
ተማሪ ኢቢ፣ ሲሲኤም በሚባል አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪ ነበረች። በኅዳር 9/2019 (እአአ) እናቷ ማርታ ዋንጂሩ ስልክ ተወደለላቸው። ልጅዎ ታማለችና አሁኑኑ ሆስፒታል ይድረሱ ተባሉ።
እናት ሆስፒታል ሲደርሱ ልጃቸው ኤቢ ሕይወቷ አልፏል።
ምን ሆና ሞተች?
ትምህርት ቤቱ በተኛችበት ሞታ ተገኘች አለ። ምሥክሮች ግን በምክትል ርዕሰ መምህርት ከፍተኛ ድብደባ ደርሶባት ነው የሞተችው ይላሉ። ምን አጥፍታ ከተባለ ፀጉሯን የጎነጎነችበትን መንገድ ርዕሰ መምህርቷ ስላልወደደችው።
ሆስፒታል በኢቢ አስክሬን ላይ ምርምራ አደረገ።
የምርመራው ውጤት ተማሪዋ ጭንቅላቷ በከፍተኛ ሁኔታ ድብደባ እንደደረሰበት አጋለጠ።
እናት ጉዳዩን ፍርድ ቤት ወሰዱት። ጉዳዩን ፍርድ ቤት እንዲያይላቸው ለማድረግ ግን አራት ዓመት ሙሉ ታግለዋል።
ባለፈው ጥር ወር ላይ ምክትል ርዕሰ መምህርት ኤልዛቤጥ ጋቲሙ፣ ተማሪ ኢቢን ደብድቦ በመግደል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ዋሉ። ርዕሰ መምህርት ኤልዛቤጥ ድርጊቱን አልፈጸምኩም ብለዋል።
እናት “በሕይወቴ እስካለሁ ድረስ የልጄን ገዳይ እፋረዳታለሁ” ብለው ዝተዋል። ይህንንም ነው እያደረጉ ያሉት።
ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ የኬንያ ትምህርት ሚኒስትርን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ፍሬ አላፈራም።