ፍልስጥኤማዊያን ከሐማስ በኋላ የሚጠብቃቸው ምን ይሆን?
የምስሉ መግለጫ,ፍልስጥኤማዊያን ከሐማስ በኋላ የሚጠብቃቸው ምን ይሆን?

ከ 5 ሰአት በፊት

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ “መካከለኛው ምሥራቅን እንቀይረዋለን” ሲሉ ዝተዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን “ከእንግዲህ ወደ ኋላ ማለት የለም” ብለዋል።

ፍልስጤማውያን መሄጃ ባይኖራቸውም ከሰሜናዊ ጋዛ ዘወር በሉ፣ ከባድ ጥቃት ልናደርስ ነው እየተባሉ ይሸበራሉ፤ ይመከራሉ።

የጦርነቱ መጨረሻው ምን ይሆን?

ሐማስ መብረቃዊ እና አሰቃቂ ጥቃት ከፈጸመ ወዲህ የእስራኤል ባለሥልጣናት ሐማስን ከሥሩ መንግለን እንጥለዋለን ብለዋል። በዚህም የቡድኑ ወታደራዊም ሆነ በፖለቲካዊ ሕልውናው ያከትምለታል ማለት ነው።

ይህ የእስራኤል ሕልም ግን እንዴት ነው ሊሳካ የሚችለው? ሐማስ ከጠፋ በኋላስ ጋዛ እንዴት ነው የምትቀጥለው?

“እንዲህ ዓይነት ግብ ይዘህ ተነስተህ ግቡ ሲሳካ ምን ይፈጠራል የሚለውን ሳታቅድ ዘመቻ አትጀምርም” ይላሉ ዶ/ር ማይክል ሚልሽቴን።

ዶ/ር ማይክል እዚያው እስራኤል ውስጥ ባለው የቴል አቪቭ ዩኒቨርስቲ ሞሼ ዳያን ማዕከል ተመራማሪ ናቸው።

ዶ/ር ማይክል ቀድሞ በእስራኤል ወታደራዊ ደኅንነት የፍልስጥኤም ጉዳዮች መሪ ነበሩ። ከሐማስ በኋላ ስለጋዛ ተጨባጭ ዕቅድ ስለመውጣቱ ይጠራጠራሉ።

“አሁኑኑ መጀመር ነው ያለበት” ይላሉ።

የምዕራብ ዲፕሎማቶች በዚህ ጉዳይ ላይ ጥልቅ ውይይት ከእስራኤል ጋር እያደረግን ነው ይላሉ። እስከ አሁን ግን የተጨበጠ ነገር ስለማያዛቸው የተባለ ነገር የለም።

አንድ ዲፕሎማት ለቢቢሲ ሲናገሩ፣ “በዚህ ደረጃ ተጨባጭ ዕቅድ ሊኖርህ አይችልም፤ የተወሰኑ የተሞነጫጨሩ ሐሳቦች ሊኖሩ ይችላሉ። ሐሳቦቹን መልክ ማስያዝ እና ተግባር ላይ ማዋል ግን ረዥም የዲፕሎማሲ ጥረት እና ጊዜ ይሻል” ይላሉ።

አሁን ባለው ደረጃ ያለው ዕቅድ የሐማስን የወታደራዊ አቅም ማንኮታኮት ነው። ከዚያ የሚከተለው አብዛኛውን ጋዛን ከሐማስ እጅ ፈልቅቆ ማውጣት ነው።

ሐማስን ከጋዛ ማስወገድ በቂ ነው?

በዚህ ጉዳይ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች በጭራሽ ይህ በቂ አይደለም ይላሉ።

ሐይም ቶመር አንዱ ናቸው። ቀድሞ በእስራኤል የውጭ አገራት የስለላ እና የደኅንነት ተቋም (ሞሳድ) ውስጥ አገልግለዋል። “ወታደራዊ ሥራ አልቆ ጋዛን ለቀን በወጣን ማግስት ለጋዛ የሚሰራ መፍትሄ ከወዲሁ ያለን አይመስለኝም” ይላሉ።

እስራኤላውያን ሐማስን በማሸነፍ ውስጥ አንድ አቋም ነው ያላቸው። ከሦስት ሳምንት በፊት የተፈጸመው አሰቃቂ የሐማስ ጥቃት አንድ አድርጓቸዋል። ከዚህ በኋላ ሐማስ ጋዛ ሰርጥን እንዲያስተዳድር በፍጹም የሚፈቀድለት አይመስልም።

ነገር ግን ዶ/ር ማይክል ሚልሽቴን ሐማስን ማሸነፍ ቢቻልም፣ ከሕዝብ ልብ ማውጣት አስቸጋሪ እንደሚሆን ይጠቁማሉ።

“ሐማስ እሳቤ ነው። እንጂ እስራኤል መጥታ በአንድ ጊዜ ፋቅ አድርጋ የምታጠፋው ነገር አይደለም”

ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ይላሉ ዶ/ር ማይክል፣ የ2003 (እአአ) አሜሪካ መራሹ የኢራቅ ጦርነት ነው። ሳዳምን ማስወገድ ነበር ግቡ፤ ያን አሳካ። ቀጥሎ የአገሪቱን ገዢ ፓርቲ ባዝን ሙልጭ አድርጎ አጠፋ። ነገር ግን ያ ትልቅ ስህተት ነበር።

ያ ውሳኔ በመቶ ሺዎች የመንግሥት ሠራተኞችን ከሥራ ውጪ አደረጋቸው። ወታደሩን አፈናቀለ። ይህ ምንን ፈጠረ፤ ከፍተኛ የሽብር ጥቃትን።

የአሜሪካ ፈተና እስራኤልን ይገጥማት ይሆን?

ኢራቅ ያን ወታደራዊ ዘመቻ የመሩ አሜሪካውያን አሁን እስራኤል ነው ያሉት። ልምዳቸውን ለእስራኤል ወታደራዊ ባለሥልጣናት እያጋሩ ነው። በተለይም በኢራቅ ፋሉጃ እና ሞሱል ውስጥ የገጠማቸውን እየነገሯቸው ነው።

“አሜሪካኖች ኢራቅ ውስጥ ስለሰሩት ቀይ ስህተት ለእስራኤሎች በስፋት ያስረዷቸዋል ብዬ አስባለሁ” ይላሉ ዶ/ር ማይክል ሚሊሽቴን።

“ለምሳሌ የሰውን አስተሳሰብ መቀየር እንደማይችሉ።”

በዚህ ሐሳብ ፍልስጤማውያንም ይስማማሉ።

“ሐማስ ጥልቅ የሕዝብ ድጋፍ እና መሠረት ያለው ድርጅት ነው” ይላሉ ሙስጣፋ ባርጎቲ።

ባርጎቲ የፍልስጤማውያን ብሔራዊ ኢንሺያቲቭ ኃላፊ ናቸው።

“እስራኤል ሐማስን ከሥር መሠረቱ መንቀል ከፈለገች የጋዛን ሕዝብ በሙሉ መፍጀት ይኖርባታል” ይላሉ ነገሩ እንዴት ፈታኝ እንደሆነ ለማስረዳት።

የእስራኤል ታንኮች ወደ ጋዛ ሲገቡ
የምስሉ መግለጫ,የእስራኤል ታንኮች ወደ ጋዛ ሲገቡ

የፍልስጤማውያን መፈናቀል

ፍልስጤማውያን ወደ ግብፅ ሲናይ በረሃ መሸሽ አለባቸው የሚለው የእስራኤል ሐሳብ ለፍልስጤማውያን ሞት ነው፤ ሕመም ነው፤ ቁስል ነው።

ፍልስጤማውያን ሕይወታቸውን የፈጁት በስደት ነው። እስራኤል አገር ስትሆን ከርስታቸው የተፈናቀሉ እስከ አሁን ለመሬታቸው አልበቁም።

ሌላ ዙር መፈናቀልን በፍጹም አይሞክሩትም። የ1948ቱን ቁስል ይቀሰቅስባቸዋል።

“ፍልስጤማውያንን ከጋዛ ውጡ ማለት መመለሻ የሌለው የአንድ ጉዞ ትኬት ማለት ነው” ይላሉ ዳያና ቡቱ። ቡቱ የቀድሞ የፍልስጥኤም ነጻነት ድርጅት (ፒኤልኦ) ቃል አቀባይ ናቸው።

የእስራኤል ባለሥልጣናት አሁንም ደጋግመው የሚሉት አንድ ነገር ነው። የጋዛ ነዋሪዎች ከጋዛ ይውጡና በጊዜያዊነት በሲናይ ድንበር አካባቢ ይቆዩ።

ጊዮራ ኤይላንድ የቀድሞ የእስራኤል ደኅንነት ካውንስል መሪ የነበሩ ሰው ናቸው።

“እስራኤል ሐማስን ለማጥፋት ብቸኛው መንገድ ፍልስጤማውያኑን ከጋዛ ማስወጣት ነው” ይላሉ።

ወዴት ይሂዱ ሲባሉ፤ “ወደ ግብፅ ድንበር” ብለው ይመልሳሉ። “ወይ በጊዜያዊነት ወይም በቋሚነት እዚያ ነው መወሰድ ያለባቸው።”

ጆ ባይደን ከሳምንት በፊት ለእስራኤል ወደ 14 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አጸድቀዋል። ይህም ለፍልስጤማውያኑ ድንጋጤን ፈጥሯል።

ይህ ነገር ከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ የሚፈጥር እንደሆነ ይጠበቃል።

እስራኤል እስከ አሁን በግልጽ ወይም በይፋ ፍልስጤማውያን የግብፅን ድንበር አቋርጡ አላለችም። ነገር ግን የእስራኤል መከላከያ በተደጋጋሚ በሚሰጣቸው ማሳሰቢያዎች ይህን ጠቆም ያደርጋል። “ደኅነነታችሁ ወደሚጠበቅበት ቦታ ሂዱ” ይላል። ይህ ቦታ ግን የት እንደሆነ አይገልጽም።

የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ እስራኤል በጦርነቱ ፍልስጤማውያንን ወደ ግብፅ እንዲሰደዱ ለመግፋት እየሞከሩ እንደሆነ አንስተው ተችተዋል።

ጋዛ ከሐማስ በኋላ በማን ስር ትሆናለች?

የሆነው ሆኖ የጋዛ ነዋሪ የሆኑ ፍልስጤማውያን ጦርነቱ አልቆ በጋዛ መኖራቸው አይቀርም። ያን ጊዜ ምንድነው የሚሆኑት? ማንስ ነው የሚያስተዳድራቸው?

“ይህ የሚሊየን ዶላር ጥያቄ ነው” ይላሉ ዶ/ር ማይክል ማሊሽቴይን።

በእርሳቸው አመለካከት እስራኤል አዲስ አስተዳደር በጋዛ እንዲመሠረት ማገዝ አለባት። በራሳቸው በጋዛዊያን የሚመራ አስተዳደር። ምናልባት ከአሜሪካ፣ ግብፅ እና ከሳዑዲ አረቢያ የአካባቢው ሰዎች የተውጣጣ አስተዳደር።

ምናልባት የፋታህ መሪዎች ጋዛን እንዲያስተዳድሩ መስጠትም ሌላው አማራጭ ነው። ፋታህ እና ጋዛ ተቀናቃኞች ናቸው።

ፋታህ የፍልስጤም ባለሥልጣንን ይመራል። መቀመጫው በኃይል በእስራኤል በተያዘችው ሌላኛዋ የፍልስጤም ግዛት ዌስት ባንክ ውስጥ ባለችው ራማላህ ውስጥ ነው።

የፍልስጤማውያን አስተዳደር እና ፋታህ በመሐመድ አባስ ነው የሚመሩት። ፕሬዝዳንት መህሙድ አባስ ዕድሜያቸው ገፍቷል። በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ የሚባሉም አይደሉም።

ዳያና ቡቱ፣ የፍልስጤም አስተዳደር ወደ ጋዛ መመለሱን ውስጥ ውስጡን ይሻል፤ ነገር ግን ከእስራኤል ታንኮች ኋላ ሆኖ አይደለም መመለስ የሚሻው ይላሉ።

የቀድሞው የሞሳድ ኃላፊ ሐይም ቶመር “እኔ ብሆን ለወር ያህል ማንኛውንም ወታደራዊ ጥቃት አቆም ነበር። መጀመሪያ የታገቱትን አስለቅቃለሁ” ይላሉ።

በግብፅ አማካኝነት ድርድር ተደርጎ የሚከፈለው ዋጋ ተከፍሎ ታጋቾቹ መለቀቅ እንዳለባቸው ያሳስባሉ።

“የታገቱት ዜጎቻችን እስከተመለሱልን ድረስ፤ በሺህ የሚቆጠሩ የሐማስ እስረኞችን መልቀቅ ምንም ማለት አይደለም።”

“ከዚያ በኋላ” ይላሉ የቀድሞው የሞሳድ አለቃ፤ “ከዚያ በኋላ እስራኤል ወታደራዊ ዘመቻዋን ማጧጧፍ ትችላለች።”

ይሁንና ይላሉ ሐይም ቶመር፣ የጋዛ ጉዳይ ለዘመናት የሚቀጥል ይሆናል።

“ጋዛ ማለት እስራኤል ጉሮሮ ላይ የተሰነቀረ አጥንት ነው።”