
ከ 1 ሰአት በፊት
በቴህራን ባቡር ጣቢያ ራሷን ስታ የወደቀችው ኢራናዊት ወጣት ሕይወቷ ማለፉን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እና አንቂዎች ይፋ ካደረጉ በኋላ በርካታ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ተፈጥረዋል።
የ17 ዓመቷ አርሚታ ጌራቫንድ በአንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ላይ “ምክንያቶቼን ሳታውቁ ስለምርጫዎቼ አትፍረዱ” ስትል በእንግሊዘኛ ጽፋለች።
ከሳምንታት በፊት ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ የወሰነችው ያለ ሂጃብ ነበር። በጉዞ ላይ እያለችም ቴህራን በሚገኘው ሾሃዳ ባቡር ጣቢያ ውስጥ ራሷን ስታ ወደቀች። በወቅቱ ሁለት ጓደኞቿ አብረዋት ነበሩ።
አንቂዎች በኢራን ሃይማኖታዊ ሥነ ምግባርን የሚያስከብሩ ፖሊሶች ጉዳት አድርሰውባታል ብለው ይከሳሉ።
ባለሥልጣናት ደግሞ “በደም ማነስ” ምክንያት ራሷን ስታ ስትወድቅ የመንገድ ጠርዝ ጭንቅላቷን በመምታቱ አንጎሏ ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።
ወጣቷ ሕይወቷ ከማለፉ በፊት ለ28 ቀናት ራሷን ስታ በሆስፒታል ቆይታለች።
- የኢራን የሂጃብ ተቆጣጣሪ ፖሊስ አንዲት ታዳጊን ራሷን እስክትስት በመደብደብ ተከሰሰ5 ጥቅምት 2023
- እስራኤል የጋዛን ጦርነት ካላቆመች ቀጠናው ከቁጥጥር ውጭ ሊወጣ እንደሚችል ኢራን አስጠነቀቀች23 ጥቅምት 2023
- አሜሪካ የኢራን ናቸው ያለቻቸውን በሶሪያ የሚገኙ ወታደራዊ ተቋማትን በአየር ደበደበች27 ጥቅምት 2023
አርሚታ ጌራቫንድ ማን ናት?
ስለአርሚታ ሕይወት የሚታወቀው ነገር አነስተኛ ነው። ቤተሰቦቿ ሎሬስታን በምትባል በምዕራብ ኢራን ግዛት ውስጥ ይኖሩ ነበር። ቴህራን መኖር የጀመሩት በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው።
አርሚታን የሚያውቋት ወጣት እና ስለሕይወት ልዩ ፍላጎት እንደነበራት ይገልጻሉ። በሌላ ጊዜ ደግሞ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጎህ ሊቀድ ሲል ውጪውን በመስኮቷ በኩል ፎቶ አንስታ “የጨለማው ሌሊት ጊዜው አብቅቶ ፀሐይ ትወጣለች” የሚል ጽሑፍ ለጥፋዋለች።
ድመቶች፣ ሥዕል፣ ቢቲኤስ፣ የካርቶን ፊልም እና ፋሽን ላይ ፍላጎት ነበራት። የተለመደውን አይነት የኢራን ማኅበረሰብ አካሄድን አልተከተለችም።
ከ2013 (እአአ) ጀምሮ ቴክዋንዶ ትሠራ ነበር። የአናሂድ ራዝም ቴክዋንዶ ክለብን ነበር የተቀላቀለችው። ጓደኛዋ ጎበዝ ስፖርተኛ መሆኗን መሰክራለች።

ለኮሪያ ባህል፣ ቋንቋ እና ሙዚቃ ትልቅ ፍላጎት እንደነበራት አንዳንዴ በኮርያኛ የምትጽፋቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፎች ያሳያሉ። የኮሪያው የሙዚቃ ቡድን ቢቲኤስም ቀንደኛ ተከታይ ናት። አንዳንዴ ልብሶቿ እና የፀጉር አሰራሯ ይህንን ይመሰክራሉ።
አንድ ጓደኛዋ ለቢቢሲ ፐርሺያ እንደገለጸችው አርሚታን ለሥዕል ትልቅ ፍቅር ነበራት። ከሁለት ዓመት በፊት ለመማር ተመዝግባም ነበር።
ክፍሏ በሥዕል ሥራዎቿ አሸብርቋል። ጠረጴዛዋ በሥዕሎች፣ በእርሳሶች እና በወረቀቶች የተሞሉ ናቸው። ድመት እና የምትወዳቸውን ዘፋኞች መሳል ትወዳለች። ልብስ ዲዛይንም ቀልቧን ከሚስቡት መካከል ነው።
አርሚታ ጌራቫንድ ምን ገጠማት?
መንግሥት ቤተሰቦቿን ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት በመገደቡ ጋዜጠኞች እና ገልልተኛ አጣሪዎች በሾሃዳ ባቡር ጣቢያ የተፈጠረውን በጥልቅት እንዳይመረምሩ እንቅፋት ሆኖባቸዋል።
የኢራን መንግሥት የለቀቀው ደብዛዛ ተንቀሳቃሽ ምስል ፀጉሯን አልሸፈነችም አርሚታ ከሁለት ሴት ጓደኞቿ ጋር ባቡር ሲሳፈሩ ያሳያል። በቅጽበት አንዷ ጓደኛዋ ከባቡሩ ትወጣ እና ታጎነብሳለች። እሷ እና ሌሎች ተሳፋሪዎች ራሷን የሳተችውን አርሚታን እጅ እና እግሯን ይዘው በማውጣት ያስተኟታል።

በመንግሥት የተለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስል አርሚታ ራሷን የሳተችበትን ሁኔታ አያሳይም። ባቡሩ ውስጥ የነበረውን ሁኔታ የሚያሳይ ምስል ይፋ አልተደረገም።
የቴህራን ሜትሮ ማኔጂንግ ዳይሬክተር በአርሚታ እና “በተሳፋሪዎች ወይም በሜትሮ ሠራተኞች” መካከል “ምንም የቃል ወይም አካላዊ ግጭት” አለመከሰቱን አሳውቀው ነበር።
አርሚታ በባቡሩ ውስጥ የሕክምና ሠራተኞች ሲረባረቡላት የሚያሳየው ፎቶ ላይ ወጣቷ የምትወደውን ጥቁር እና ነጭ ናይኪ ተጫምታ ትታያለች።
አርሚታ ገራቫንድን በ2022 ቴህራን ሂጃብ “በትክክል” አለበሽም በሚል በሥነ ምግባር ፖሊሶች ከታሰረች በኋላ ሕይወቷ ካለፈው ማህሳ አሚኒ ጋር እያመሳሰሏት ነው።
ማህሳ አሚኒ ኮማ ውስጥ ለሦስት ቀናት ቆይታ ሕይወቷ ሲያልፍ ፀረ-መንግሥት ተቃውሞዎች በመላ አገሪቱ ተቀስቅሰው ነበር። የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት የኃይል እርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ታስረዋል።