October 30, 2023 – Konjit Sitotaw
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሀገሪቱ ያሉ ችግሮች በውይይት እና በስምምነት እንዲፈቱ በድጋሚ ጥሪ አቀረበች።
ይህ ጥሪ የቀረበው ቅዱስ ሲኖዶስ የጥቅምት 2016 ዓ/ም ጉባኤውን ካጠናቀቀ በኃላ ባወጣው መግለጫ ነው።
ቅዱስ ሲኖዶስ ፤ ” ትላንት በሰሜኑ ኢትዮጵያ የሀገራችን ክፍል በተካሄደው ጦርነት በጠፋው የሰው ሕይወትና በወደመው ንብረት ከደረሰብን ሐዘን እኛ ኢትዮጵያውያን ገና ሳንጽናና ዛሬም በሀገራችን ኢትዮጵያ በበርካታ አካባቢዎች የተከሰቱት ጦርነቶች፣ ግጭቶችና አለመግባባቶች እያስከተሉት ያለው የንጹሐን የሰው ሕይወት መጥፍትና የንብረት ውድመት በእጅጉ አሳዝኖናል ” ብሏል።
በመሆኑም ችግሩ በውይይትና በስምምነት እንዲፈታ የፌዴራልን የክልል መንግሥታት፣ እንዲሁም በግጭቱ ተሳትፎና ድርሻ ያላቸው በሁሉም አካባቢ የምሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖች በሙሉ የበኩላቸው ሚና በመወጣት እናት አገራችን ኢትዮጵያ ሰላሟና አንድነቷ ተጠብቆ ይቀጥል ዘንድ ከአደራ ጭምር በድጋሚ ጥሪውን አቅርቧል።
ከዚህ በተጨማሪ ስለ ሀገር ሰላም እና ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት በመላው ዓለም በሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ ከህዳር 15 ቀን 2016 እስከ ታህሣሥ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ጸሎትና ምሕላ እንዲፈጸም ተወስኗል።