የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ እና በናይጄሪያ መንግስት መሐል የተፈጠረው ምንድነው?
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በ 300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የናይጄሪያ አየር መንገድ ለማቋቋም የወጣውን ጨረታ በማሸነፍ 49 በመቶ ድርሻ ይዞ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ መሆኑ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ በሁለቱ አካላት መሃከል ስምምነት ከተደረሰ በኋላ የናይጄሪያ አየር መንገድ ኦፕሬተሮች (AON) ስር ያሉ የሀገር ውስጥ አቪዬሽን ድርጅቶች የናይጄሪያ አየር መንገድ አብላጫውን ድርሻ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመስጠት ማቀዱ ሀገሪቱን የሚጎዳ ነው በማለት ተቃውሞ አሰምተዋል።
በመቀጠል በናይጄሪያ ሌጎስ የሚገኘው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የናይጄሪያ ፌደራል መንግስት የናይጄሪያ አየር መንገድ ድርሻን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዳይሸጥ የከለከለ ሲሆን ከወር በፊት የናይጄሪያ የአቪዬሽን ሚኒስትር የሆኑት ፌስቱስ ኬያሞ፥ ፕሮጀክቱ መታገዱን አሳውቀዋል።
ይህን ጉዳይ አስመልክቶ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለረዥም ጊዜ በጉዳዩ ላይ ዝምታን መርጦ የነበረ ሲሆን ከቀናት በፊት የአየር መንገዱ ቡድን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው አስተያየት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ምን አሉ?
ዋና ስራ አስፈፃሚው በመጀመሪያ አየር መንገዱ የናይጄሪያ አየር መንገድን ፕሮጀክት ለመውሰድ ተነሳሽነት እንዳልነበረው የገለፁ ሲሆን የናይጄሪያ መንግስት አየር መንገዱን ለማቋቋም ያደረገውን ግፊት ተከትሎ ወደ ጨረታው እንገደቡ ገልፀዋል።
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ውጪ በጨረታው ሌሎች አየር መንገዶች ይሳተፉ አይሳተፉ መረጃው እንደሌላቸው አቶ መስፍን ሲገልፁ ፥
ጨረታውን ከተወዳደሩ በኋላ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ የናይጄሪያን አየር መንገድ ለማቋቋም አጋር ሆኖ ተመርጧል” የሚል ደብዳቤ ከአቪዬሽን ሚኒስቴር ከደረሳቸው በኋላ የማቋቋሙ እንቅስቃሴ እንደተጀመረ አስረድተዋል።
አቶ ጣሳው ስለ ፕሮጀክቱ ቀጣይነት ሁኔታ ምን አሉ?
አቶ ጣሳው የናይጄሪያ መንግስት የተቋማቸውን እገዛና ስትራቴጂ የሚፈልግ ከሆነ ተቋማቸው አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ገልፀው የናይጄሪያ መንግስት ፕሮጀክቱን የሚሰርዝ ከሆነ ተቋማቸውን የሚያሳስብ እንዳልሆነ በማስረዳት “የናይጄሪያን መንግስት ውሳኔ እናከብራለን” ብለዋል።
