የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው እና የህወሓት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረ ጽዮን
የምስሉ መግለጫ,የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው እና የህወሓት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረ ጽዮን

30 ጥቅምት 2023, 17:09 EAT

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ “ያለ መንግሥት እውቅና” የተጠራ ባሉት ስብሰባ የህወሓት ካድሬዎች ቀደም ብለው በተያዙ አጀንዳዎች ላይ ሳይወያዩ መበተናቸው ተሰምቷል።

ነገር ግን ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በተካሄደው ስብሰባ ማብቂያ ላይ የፓርቲው ካድሬዎች ባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ ማውጣታቸውን ህወሓት በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ አሳውቋል።

ይህ በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል የሃሳብ ልዩነት ያስከተለ ሲሆን፣ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ስብሰባው እንዳይካሄድ የወሰዱትን እርምጃ “ተቋማዊ አሰራርን ያልተከተለ ነው” ሲል ፓርቲው ተችቶታል።

አቶ ጌታቸው ቅዳሜ በሰጡት መግለጫ ስብሰባው መንግሥት የማያውቀው እና ሕገ ወጥ ነው ያሉት ሲሆን፣ አንዳንድ የዞን አመራሮች ላይም እርምጃ እንደተወሰደ ተናግረው ነበር።

ይህ ሁኔታ በክልሉ ያልተለመደ ክስተት በመሆኑ በርካቶች ‘ምን ተፈጠረ?’ ብለው ሲጠይቁ፣ ሌሎች ደግሞ በህወሓት ውስጥ መከፋፈል እንዳለ ሲጠቁሙ ነበር።

ህወሓት ትላንት በፌስቡክ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ስብሰባው ይሁንታን ባያገኝም ከፓርቲው ከፍተኛ ካድሬዎቹ 82 በመቶ የሚሆኑት ስብሰባው “በተቋማዊ አሰራር በሕጋዊ መንገድ የተጠራ ነው” ባለው ስብሰባ ላይ መሳተፋቸውን አመልክቷል።

አቶ ጌታቸው ረዳ ግን ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በሰጡት መግለጫ ክልሉ የገጠመውን ችግር ለመፍታት ጥረት ከማድረግ ይልቅ ለስብሰባ ወደ መቀለ በመምጣት የክልሉ መስተዳደር የማያውቀውን ስብሰባ ማካሄድ ዓላማው ግልፅ አይደለም በማለት የመንግሥትን አሰራር የጣሱ ናቸው ባሏቸው ኃላፊዎች ላይ እርምጃ ተመወሰዱን ገልጸዋል።

“የሰብሰባው ዋና ተሳታፊዎች በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ የሕዝብ አደረጃጀት ኃላፊዎች ሲሆኑ፣ በሕዝብ እና በመንግሥት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ያልተወጡት ላይ እርምጃ ተወስዷል።”

አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ ለሁለት ዓመታት የተካሄደው ደም አፋሳሹ ጦርነትን እንዲያበቃ ባደረገው የፕሪቶሪያ ስምምነት አማካይነት የተቋቋመውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን እየመሩ ይገኛሉ።

ስድስት ወራትን ያስቆጠረው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ ከሚገኙ ከተለያዩ አካላት እና ከከፍተኛ የህወሓት ካድሬዎች ፈታኝ ተቃውሞ እየገጠመው እንደሆነ ይነገራል።

የስብሰባው ዓላማ ምን ነበር?

በቅርብ ጊዜ የታዩ አለመግባባቶች በከፍተኛ አመራሮች መካከል የሥልጣን ሽኩቻ እንዳለ የክልሉን ፖለቲካዊ ሁኔታ በቅርበት የሚያመለክታሉ ወገኖች ይናገራሉ።

አቶ ጌታቸው በተለያዩ መድረኮች ላይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከተካሄደው ጦርነት እና ከደረሰው ጉዳት አንጻር አመራሩ እራሱን በመገምገም ኃላፊነት እና ተጠያቂነት መኖር እንዳለበት “ንሰሐ መግባት” አስፈላጊ መሆኑን በቅርቡ በተካሄደ በጦርነቱ የሞቱ የሠራዊት አባላት የመታሰቢያ መረሃ ግብር ላይ መናገራቸው ይታወሳል።

ይህም በዋነኝነት ክልሉን ሲመሩ እና በጦርነቱ ሂደት በአመራርነት የተሳተፉ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በፌደራል እና በክልል ደረጃ የህወሓት መሪዎችም የሚመለከት ነው።

የአቶ ጌታቸው ጊዜያዊ አስተዳደር ባለፉት ወራት የሚጠበቅበትን ሥራ ለማከናወን እንቅፋቶች እንደነበሩበት የገለጸ ሲሆን፣ እራሳቸውም አስተዳደራቸው በዞኖች እና በወረዳዎች ውስጥ እግሩን መትከል አለመቻሉን እና አንዳንድ ወረዳዎች የጊዜያዊ አስተዳደሩ አካል መሆናቸውን እንዳይቀበሉ የሚያደርግ “የተደራጀ እንቅስቃሴ” መኖሩን ተናገረው ነበር።

አቶ ጌታቸው አባል የሆኑበት እና በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ህወሓት ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በጠራው ስብሰባ ላይ የአቶ ጌታቸው ጊዜያዊ አስተዳደር ዋነኛ አጀንዳ ለማድረግ ታስቦ እንደነበር ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ውስጥ አዋቂ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“የተጠራው የካድሬዎች ስብሰባ የጊዜያዊ አስተዳደሩን እና በተለይም የአቶ ጌታቸው ረዳን አመራር ለመገምገም ያነጣጠረ እና ህወሓት የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥልጣን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ያለመ ነበር” ብለዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ በበኩሉ ራሱን እና የክልሉን የፀጥታ አመራር ጨምሮ በክልሉ ያለው ሁኔታ መገምገም አለበት የሚል አቋም የወሰደ ሲሆን፣ ሌላኛው የህወሓት የካድሬ ቡድን ግን ይህንን አልተቀበለም።

ከአቶ ጌታቸው ጋር ውዝግብ ውስጥ የገባው የህወሓት አንድ ቡድን ህወሓት የክልሉ ገዢ ፓርቲ እንደሆነ እና ጊዜያዊ አስተዳደሩን ከላይ ሆኖ መገምገም እና መቆጣጠር እንደሚፈልግ ምንጮቻችን ገልጸዋል።

በፓርቲው አመራሮች መካከል ያለውን የአቋም ልዩነቶች ለማስወገድ በአንዳንድ ወገኖች ጥረት የተደረገ ቢሆንም፣ ካድሬዎቹ በስብሰባው የተያዙ አጀንዳዎች ላይ ሳይወያዩ እንደተበተኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በታሰበለት ሁኔታ በሳምንቱ ማብቂያ ላይ ያልተካሄደው የህወሓት ካድሬዎች ስብሰባ ላይ በግልጽ ያልተነሱትን እነዚህን ሁለት አጀንዳዎች እና ሌሎችንም ጉዳዮች ከ10 እስከ 15 ቀናት ውስጥ በሚኖር ሌላ ስብሰባ ላይ እንደሚወያይባቸው ቀጠሮ ይዟል።

ስብሰባ ካካሄዱት ከህወሓት ካድሬዎች የተሰጠው መግለጫ በፓርቲው ውስጥ ብዙ ድክመቶች እንዳሉ እና በግምገማ ማጥራት እንደሚያስፈልጋቸው ያመለክታል።

ይህ ውዝግብ የፈጠረው ድንገተኛ ስብሰባን በተመለከተ ካለፈው ሳምንት ረቡዕ ሌሊት አንስቶ ለካድሬዎች ጥሪ መደረጉ አነጋጋሪ የነበረ ሲሆን፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ “ሕገወጥ” ያለውን ስብሰባ በማደራጀት ተሳትፈዋል የተባሉ የዞን ባለሥልጣናት ካለፈው ሐሙስ ጥቅምት 15 ጀምሮ በአቶ ጌታቸው ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተነግሯል።

አቶ ጌታቸው እርምጃው እንደሚቀጥል ያስጠነቀቁ ሲሆን፣ የቢቢሲ ምንጭ እንደገለጹት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች ከሥልጣናቸው ሳይነሱ አይቀሩም ብለዋል።

“እነዚህ ቀስቃሾች መሬት ላይ እያጋጠሙን ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ሕዝብ አደራጅተው ከመዝመት ይልቅ ወደ መቀለ መጥተው የሚሰበሰቡበት አላማው ግልፅ አይደለም” ሲሉ አቶ አቶ ጌታቸው ባለፈው አርብ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተችተዋል።

የትግራይን ከ32 ዓመታት በላይ በበላይነት ሲመራ የቆየው ህወሓት ለሁለት ዓመታት በተካሄደው አውዳሚ ጦርነት ምክንያት ከብዙ የትግራይ ተወላጆች በኩል ከባድ ተቃውሞ እየገጠመው ነው።