የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

31 ጥቅምት 2023, 08:55 EAT

እሁድ ዕለት ከእስራኤል ቴልአቪቭ የተነሳው አውሮፕላን በሩሲያ አየር ማረፊያ በሚደርስበት ወቅት ጸረ- ሴማዊ ተቃውሞዎች መነሳታቸውን ተከትሎ ሩሲያ በዩክሬን እና በምዕራባውያን የተቀነባበረ ነው ስትል ወቀሰች።

አሜሪካ በምላሹ “የማይረባ” በማለት አጣጥላዋለች።

የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቴሌቭዥን በተካሄደ ስብሰባ ላይ እንደገለጹት ክስተቱ “ሁከትን” ለማስፋፋት የተደረገ ሙከራ ነው።

ከእስራኤል መዲና ቴል አቪቭ የተነሳ አውሮፕላን ማካችካላ ከመድረሱ በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አየር ማረፊያውን ወረዋል።

ብዙዎች የፍልስጥኤም ሰንደቅ ዓላማ ከማውለብለብ ባለፈ ጸረ ሴማዊ መፈክሮችን አስምተዋል።

ዳግስታን በምትባለው የሩስያ ግዛት የሚኖሩ አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ሙስሊሞች ናቸው። አጋጣሚው በጋዛ የተነሳው ግጭት የወለደው ንዴት የቀሰቀሰው ነው ተብሏል።

የጸጥታ ሃይሎች ሁኔታውን በቁጥጥር ስር አውለዋል። ከ60 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ገልጸዋል።

ፑቲን በሩሲያ የፀጥታ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ “የማካችካላው ክስተት ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ዩክሬን ብቻ ሳትሆን የምዕራባዊያን የስለላ እጅ ያለበት ነው” ብለዋል።

“ህይወት የሚቀጥፈውን ትርምስ ማን እያደራጀ ነው? ማንስ ይጠቀማል? በኔ እምነት ጉዳዩ ግልጽ ነው።”

“በዓለም አለመረጋጋት ዋነኛ ተጠቃሚ የሆኑት የአሜሪካ መሪዎች እና ተላላኪዎቻቸው ናቸው” ብለዋል።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “በጋዛ ሰርጥ ውስጥ እየተፈጸመ ያለውን አሰቃቂ ድርጊት የሚያሳዩ የቴሌቭዥን ምስሎች ምክንያት በማድረግ ጠላቶች አጋጣሚውን ተጠቅመው ለማነሳሳት በጣም ቀሏቸዋል።”

የዳግስታን ገዥ ሰርጌይ ሜሊኮቭ በበኩላቸው ሁከቱ የተቀሰቀሰው “በዩክሬን ግዛት ባሉ ከዳተኞች” ሞርኒንግ ዳግስታን የተባለውን የቴሌግራም ቻናል በመጠቀም መሆኑን ገልጸዋል።

ሞርኒንግ ዳግስታን እስላማዊ ቻናል ሲሆን ሩሲያን ክልሉን መቆጣጠሯን የሚቃወም ነው። በ2016 ከድቶ ወደ ዩክሬን በመግባት ዜግነት ካገኘው ከቀድሞው የሩሲያ የፓርላማ አባል ኢሊያ ፖኖማሬቭ ጋር ግንኙነት አለው።

እሑድ ዕለት ቻናሉ ከቴል አቪቭ ወደ ማካችካላ የተደረገውን በረራ ዝርዝር መረጃ አውጥቶ ተከታዮቹ “ጎብኝዎቹን እንዲያገኙ” መልዕክት አስተላልፏል።

የሜሊኮቭን አስተያየት ተከትሎ ቻናሉ ከፖኖማሬቭም ሆነ ከዩክሬን ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው መግለጫ አውጥቷል። ፖኖማሬቭ ባለፈው ዓመት ቻናሉን መደገፍ እንዳቆመ ተናግሯል። ምንም እንኳን በቅርብ ወራት የሰጣቸው መግለጫዎች ይህንን የሚቃረኑ ሆነዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ የአየር ማረፊያውን ሁከት አውግዘዋል።

የአሜሪካ ብሔራዊ የጸጥታ ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ስለ ሩሲያ ክስ ለቀረበላቸው ጥያቄ “የሩሲያ የምናቃቸው ትርክቶች ናቸው” ሲሉ መልሰዋል።

“በአገራችሁ መጥፎ ነገር ሲከሰት ሌላን ወገን ትወቅሳላችሁ” ብለዋል።

“ምዕራባውያን ከዚህ ጋር ምንም ግንኙነት አልነበራቸውም። በቀላሉ ይህ ጥላቻ፣ ጭፍን ጥላቻ እና ማስፈራራት ነው።”

የአውሮፕላን ማረፊያው ሁኔታ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የነበሩ ፖጎም ተብለው የሚጠሩት የእስራኤላውያን ጭፍጨፋ ምስሎች ጋር መነጻጸሩ “ትክክለኛ” ነው ብለዋል።

በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ በስፋት የተሰራጨው ተንቀሳቃሽ ምስል በርካታ ሰዎች ወደ አውሮፕላን ማረፊያው በሃይል ገብተው በሮች ከፍተው ወደ አውሮፕላን መንደርደሪያው ሲያቀኑ ያሳያል።

የተወሰኑት ደግሞ የእስራኤልን ፓስፖርት የያዙ ሰዎችን ለመፈለግ በሚመስል መልኩ መኪናዎችን ሲያቆሙ እና የተሳፋሪዎቹን ሰነዶች ሲጠይቁ ታይተዋል።

የሩስያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የፖሊስ አባላትን ጨምሮ 20 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው እና ሁለቱ በአስጊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ገልጿል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ የእስራኤል መንግሥት “በየትኛውም ቦታ የሚገኙ የእስራኤል ዜጎችን እና አይሁዶችን ለመጉዳት የሚደረጉ ሙከራዎችን እንደ ጸብ አጫሪነት ይመለከታል” ብሏል።

“የሩስያ ባለስልጣናት የሁሉም የእስራኤል ዜጎች እና አይሁዶች ደህንነታቸው እንዲጠብቅ እና ሁከት ፈጣሪዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወስዱ እስራኤል ትጠይቃለች” ሲል አክሏል።