
ከ 9 ሰአት በፊት
በእስራኤል እና የፍልስጥኤም ቡድን ሐማስ መካከል የተኩስ አቁም እንዲኖር የሚጠይቁ ዓለም አቀፍ ጥሪዎችን አሜሪካ ውድቅ አደረገች።
“ይህ ትክክለኛው ምላሸ አይደለም” በማለት የአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት ቃለ አቀባይ ጆን ኪርቢ በትናንትናው ዕለት ምላሽ ሰጥተዋል።
በምትኩ በጋዛ ውስጥ ዕርዳታ እንዲገባ ለመርዳት ጦርነቱ “በጊዜያዊነት ገታ እንዲደረግ” ጠቁመዋል።
እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ አስገብቻታለሁ ባለቻት ጋዛ የሚኖሩ 2.2 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ያላቸው ውሃ፣ ነዳጅ እና መድኃኒት አቅርቦቶች በአስከፊ ሁኔታ ተመናምኗል።
እስራኤል ሐማስ “እስኪጠፋ” ድረስ የተኩስ አቁም እንደማይኖር ቃለ ገብታለች።
“የተኩስ አቁም ጥሪ እስራኤል ለሐማስ እንዲሁም ለሽብርተኝነት እጅ እንደመስጠት ነው፤ ይህ አይሆንም” በማለት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መጽሃፍ ቅዱስን ዋቢ በማድረግ “ለጦርነት ጊዜው አሁን ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
ቃለ አቀባዩ ኪርቢ ተጨማሪ የእርዳታ መኪናዎች በግብጽ በኩል ወደ ጋዛ እንደሚገቡ እርግጠኝነታቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
አገራቸው በግብጽ የድንበር ማቋረጫ በኩል የሚገቡ ዕርዳታ የጫኑ መኪናዎች ቁጥር በየቀኑ ወደ 100 ለማሳደግ ከእስራኤል መንግሥት ጋር መነጋገሯንም አስረድተዋል።
እሁድ እለት ወደ 45 የሚጠጉ እርዳታ የጫኑ መኪናዎች በግብጽ የድንበር ማቋረጫ በኩል ወደ ጋዛ መግባቱንም ኪርቢ ተናግረው ነገር ግን የበለጠ እርዳታ እንደሚያስፈልግ አምነዋል።
- የዩኬ ባለሥልጣን ‘በጋዛ ተኩስ አቁም ይደረግ’ በማለታቸው ከሥራ ተባረሩ31 ጥቅምት 2023
- እግረኛ ጦሯን ወደ ጋዛ ያሰማራችው እስራኤል የምትፈልገውን ግብ ማሳካት ትችላለች?31 ጥቅምት 2023
- እስራኤል ዲፕሎማቶቿን ከቱርክ ጠራች29 ጥቅምት 2023
“ከነበርንበት ስናየው አስደናቂ መሻሻሎች አይተናል። ነገር ግን ይህም በቂ እንዳልሆነ እናውቃለን” ሲሉም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጥኤም ስደተኞች የእርዳታ ኤጀንሲ ዋና ኮሚሽነር ፊሊፕ ላዛሪኒ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በየቀኑ 500 የሚጠጉ እርዳታ የጫኑ መኪኖች ወደ ጋዛ ይገቡ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
እስራኤል ሐማስ ላደረሰው መብረቃዊ ጥቃት ምላሽ ነው በሚል በጋዛ ላይ የማያባራ የአየር እና የመሬት ጥቃት እየፈጸመች ትገኛለች።
ሐማስ ባደረሰው ጥቃት 1 ሺህ 400 ሰዎች ተገድለዋል እንዲሁም ከ200 በላይ ሰዎች ታግተዋል።
በእስራኤል ጥቃት ከ8 ሺህ በላይ ፍልስጥኤማውያን የተገደሉ ሲሆን፣ ከእነዚህም አብዛኛዎቹ ሕጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
እስራኤል ጋዛን በሙሉ ከበባ ውስጥ ያስገባቻት ሲሆን በዚህም የነዳጅ፣ የመብራት እና የውሃ አቅርቦት እንዲቋረጥ አድርጋለች።
በአሁኑ ጊዜ አነስተኛ መጠን ያለው እርዳታ በግብፅ በኩል እየገባ ሲሆን፣ የረድዔት ድርጅቶችም ሁኔታው አስከፊ እንደሆነ በመጥቀስ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ።