
31 ጥቅምት 2023, 08:00 EAT
በዩናይትድ ኪንግደም አንድ የሚኒስትር ረዳት እና የተወካዮች ምክር ቤት አባል ከሥራ ተባረሩ። ፖል ብሪስቶ ሥራቸውን ያጡት በጋዛ ተኩስ አቁም ይደረግ ብለው በይፋ መናገራቸውን ተከትሎ ነው።
ፖል ብሪስቶ ባለፈው ሳምንት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪሺ ሱናክ በጻፉት ደብዳቤ ነበር በጋዛ ተኩስ አቁም እንዲደረግ የጠየቁት።
“ዘላቂ ተኩስ አቁም ቢደረግ በጋዛ የሰብአዊ ረድኤት ለማድረግ ያግዛል፤ የሚሞቱ ንጹሐንም ቁጥር ይገታል’ ብለው ነበር በደብዳቤያቸው።
የዩኬ መንግሥት ይህ ደብዳቤ አስቆጥቶት ባለሥልጣኑን ከሥራ አሰናብተዋል።
ዩኬ በጋዛ ጊዝያዊ ተኩስ አቁም እንጂ ዘላቂ ተኩስ አቁም መደረግ የለበትም የሚል አቋም አላት።
ባለፈው ሳምንት በነበረ የምክር ቤት ስብሰባ ሪሺ ሱናክ ‘ጊዝያዊ ተኩስ አቁም እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ ያስችላል’’ ካሉ በኋላ ”ዘላቂ ተኩስ አቁም ማድረግ እስራኤል ራሷን የመከላከል መብቷን መጋፋት” እንደሆነ አስረድተው ነበር።
ፖል ብሪስቶ የወግ አጥባዊው ፓርቲ አባል ሲሆኑ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ረዳት ሆነው ሲሠሩ ነበር።
ፖል ብሪስቶ በጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ከተባረሩ በኋላ ለቢቢሲ በሰጡት አስተያየት “የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ እረዳለሁ፤ የምወደውን ሥራ በመልቀቄ አዝናለሁ። አሁን ግን በጉዳዩ ላይ በነጻነትና በግልጽ እናገራለሁ። የመረጠኝ ሕዝብ ስለጉዳዩ ያሳስበዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
- እግረኛ ጦሯን ወደ ጋዛ ያሰማራችው እስራኤል የምትፈልገውን ግብ ማሳካት ትችላለች?31 ጥቅምት 2023
- ሕገወጥ የተባለው የህወሓት ካድሬዎች ስብሰባ ዋነኛ አጀንዳ ምን ነበረ?30 ጥቅምት 2023
- በውሰት ጫማ ከመወዳደር የዓለም ክብረ ወሰን እስከመስበር31 ጥቅምት 2023
“አሁን በመንግሥት ሥልጣን ሳልሆን፣ በምክር ቤት ሆኜ በጋዛ ተኩስ አቁም እንዲደረግ እሟገታለሁ” ሲሉም ተናግረዋል።
በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ የምክር ቤት አባላት በጋዛ ዘላቂ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ቢፈልጉም፣ የወግ አጥባቂው ምክር ቤት አባላት ግን በብዛት ይህን ሐሳብ አይደግፉም።
የሌበር ፓርቲ መሪ ሰር ኪር ስታመር ተኩስ አቁም እንዲደረግ እንዲደግፉ ጫናው በርትቶባቸዋል። የለንደን ከንቲባ ሳዲቅ ካን፣ የስኮቲሽ ሌበር መሪ አናስ ሳርዋር እና ሌሎች በርካታ የሌበር ቁልፍ የምክር ቤት አባላት በጋዛ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ይሻሉ።
የሚኒስትር ረዳት የነበሩትና አሁን ከሥራቸው የተባረሩት ብሪስቶው ከዚህ ቀደም ብሎ በፌስቡክ ገጻቸው፣ “ንጹሓን ፍልስጤማዊያን ሐማስ ለፈጸመው ጥቃት ለምን በደቦ ይቀጣሉ?” ሲሉ በእስራኤል እርምጃ ያላቸውን ቅሬታ ገልጸው ነበር።
የደቦ ቅጣት በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከለ ነው።
ብሪስቶው ከሚወክሉት የፒተርቦረው አውራጃ 18 ከመቶ የሚሆኑት ነዋሪዎች ሙስሊሞች ናቸው።
ይህ በእንዲህ እያለ የሌበር ፓርቲ አባል አንዲ ማክዶናልድ ከምክር ቤት አባልነታቸው ለጊዜው መታገዳቸው ተዘግቧል። አንዲ የታገዱት ለፍልስጥኤማውያን ድጋፍ በተጠራ ሰልፍ ላይ ‘የሚያስቀይም ንግግር’ ተናግረዋል በሚል ነው።
እስራኤል በሐማስ 1ሺህ 400 ሰዎች ከተገደሉባት በኋላ እንዲሁም 239 ሰዎች ከታገቱ ወዲህ በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ ከ8ሺህ ፍልስጥኤማውያን በላይ ተገድለዋል። አሐዙ ግን በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስትር ነው።