
31 ጥቅምት 2023, 07:02 EAT
የእስራኤል አመራሮች ሐማስ ከምድረ ገጽ እንደሚጠፋ እና ጋዛ የቀድሞው ይዞታዋ እንደማይቀጥል ዝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “ሁሉም የሐማስ አባል ሟች ነው” ብለዋል።
ሐማስ በፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት 1,400 እስራኤላውያን በሐማስ ተገድለዋል። በአጸፋው እስራኤል በጋዛ ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ከ8 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።
ከቀናት በፊት ደግሞ እስራኤልም እግረኛ ወታደሮቿን በማሰማራት ጋዛ ላይ ወረራ ፈጽማለች።
ሐማስ “የሽብር ቡድን” ነው ብላለች እስራኤል።
እስራኤል ወረራውን በእግረኛ ጦር ወደ ጋዛ እንደምታስፋፋ አስታውቃለች።
መከላከያ ሚኒስትሩ ዮአቭ ጋላንት በጋዛ “አዲስ የደኅንት መዋቅር” እንደሚዘረጋ ተናግረዋል።
እስራኤል በጋዛ ላይ የምታካሂደው ዘመቻ ‘ስዎርድስ ኦፍ አይረን’ [የብረት ጎራዴዎች] የተሰኘ ስያሜ ነው የተሰጠው። ለወራት የሚቀጥል ይሆናል ተብሎ ተገምቷል።
ይህ ወታደራዊ ዘመቻ ግቡን ይመታል? የሚለው በተደጋጋሚ እየተነሳ ያለ ጥያቄ ነው።
ወደ ጋዛ በእግረኛ ጦር ከተገባ የቤት ለቤት ወይም የከተማ ውጊያ ነው የሚሆነው። ለንጹሃን ዜጎች አስጊ ነው።
በጋዛ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ይኖራሉ።
እስካሁን ከ8,000 በላይ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቁጥራቸው 230 ገደማ የሚሆኑ ታጋቾችን ከጋዛ እንደሚያስፈታ ተናግሯል።
- እስራኤል ሐማስን ማስወገድ ከቻለች በጋዛ ላይ ምን የያዘችው ዕቅድ አለ?30 ጥቅምት 2023
- እስራኤል የጋዛ ሰርጥ ወረራን ጀምራለች?29 ጥቅምት 2023
- የእስራኤል እግረኛ ጦር ጋዛ ሲገባ ከሐማስ ምን ሊገጥመው ይችላል?26 ጥቅምት 2023
እግረኛ ጦር ጋዛ ማስገባት
ወታደራዊ ተንታኝ አሚር ባር ሻሎም “እስራኤል እያንዳንዱን የሐማስ አባል ትገድላለች ብዬ አላስብም። ሐሳቡ ጽንፈኛ የእስልምና አስተምሮት ነው። መዳከም ግን ይችላል። ዘመቻ የማካሄድ አቅም እንዳይኖረው ማድረግ ይቻላል” ይላል።
ከማጥፋት ይልቅ ማዳከም ሊሳካ የሚችል ግብ ይመስላል።
እስራኤል ከሐማስ ጋር አራት ጊዜ ግጭት ውስጥ ገብታ ሐማስ የሚተኩሰውን ሮኬት ማስቆም ግን አልተቻለም።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ እንደሚሉት፣ ግባቸው ሐማስ “እስራኤላውያንን የማስፈራራት ወይም የመግደል” አቅም እንዳይኖው ማድረግ ነው።
በቴል አቪቭ ዩኒቨርስቲ የፍልስጥኤም ጥናት ክፍል ኃላፊ ማይክል ሚልስቲን፣ ሐማስን ማጥፋት የማቻል ነው ይላል።
ሐማስ ከ25,000 በላይ ወታደራዊ ክንፎች አሉት። በእነዚህ ውስጥም ከ80,000 እስከ 90,000 አባላት አሉት።
የዚህ ጦርነት ውጤት እስራኤል ለቀጣይ 75 ዓመታት የሚኖራትን ዕጣ ፈንታ እንደሚወስን መከላከያ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ አል-ቃሳም ብርጌድ፣ እስራኤል ለምታደርሰው ጥቃት ተዘጋጅቶ ነው የሚጠብቀው።
ተቀጣጣይ ፍንጂዎች በየቦታው ይቀበራሉ። ድንገተኛ ከበባም ይደረጋል። ከመሬት በታች ያሉትን የውስጥ ለውስጥ መተላለፊያ ዋሻዎችን በመጠቀም ጥቃቶች ሊፈጸሙ ይችላሉ።
እአአ በ2014 የእስራኤል ወታደሮች በተቀበሩ ቦንቦች እና ድንገተኛ የከበባ ጥቃት ጉዳት ደርሶባቸዋል። በሰሜናዊ ክፍል ንጹሃን ዜጎችም ሞተዋል።

እስራኤል አሁን ከሰሜናዊ የጋዛ ክፍል ሰላማዊ ሰዎች እንዲወጡ ያሳሰበችው ለዚህ ይሆናል።
ከሰሜናዊ ክፍል ወጥተው ወደ ደቡባዊው የዋዲ ጋዛ ወንዝ እንዲሄዱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።
እስራኤላውያን ለረዥም ጦርነት ተዘጋጁ ተብለዋል። 360,000 የተጠባባቂ ጦር አባላት ተዘጋጅተዋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ጫና እያሳደረ ሳለ እስራኤል ለምን ያህል ጊዜ መግፋት ትችላለች? የሚለው ጥያቄ ያጭራል።
ጋዛ ውስጥ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። ውሃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እና ነዳጅም የለም። የተባበሩት መንግሥታት ሰብአዊ ቀውስ እንደሚባባስ አስጠንቅቋል።
እስራኤላዊው የደኅንነት እና ስለላ ጋዜጠኛ ዮሲ ማልማን “መንግሥት እና መከላከያው ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንዳላቸው ያምናሉ። ቢያንስ ምዕራባውያን ይደግፏቸዋል። ጊዜ ስላለን ወደፊት እንገፋለን ብለው ነው የሚያስቡት” ይላል።
ሆኖም ግን የተራቡ ሰዎች ሲታዩ እስራኤል ድጋፏን ታጣለች ብሎ ያምናል።
ንጹሃን መሞታቸው በቀጠሉ ቁጥር እስራኤል ላይ የሚደረገው ጫና ይበረታል።
አሜሪካ እስራኤል በጋዛ ዓመት እና ሁለት ዓመት እንድትቆይ አለመፍቀዷ ሌላው ጉዳይ ነው።
አብዛኞቹ ታጋቾች እስራኤላውያን ቢሆኑም ከመካከላቸው አሜሪካውያን፣ ፈረንሳውያን እና ብሪታኒያውያን መኖራቸው ኦፕሬሽኑ የብዙ አገሮች ጉዳይ እንዲሆን ምክንያት ነው።
የፈረንሳይ ስትራቴጂክ ባለሙያ ኮሎኔል ሚኬል ጎያ እንደሚሉት፣ እስራኤል ታጋቾችን በሕይወት የማቆየት ወይም በቻለችው አቅም ሐማስን የመጉዳት አማራጮች አሏት።
በ2011 (እአአ) ጊላድ ሻሊት የተባለ እስራኤላዊን ከአምስት ዓመት የሐማስ እገታ ለማስለቀቅ 1,000 ፍልስጤማውያን ተፈተዋል።
ያኔ ከተፈቱት መካከል ያህያ ሲንዋር የተባለውና አሁን የሐማስ የፖለቲካ መሪ የሆነው ፍልስጤማዊ ይገኝበታል።
እስራኤል የእስረኛ ልውውጥን አሁን በቀላሉ ላትቀበለው የምትችለውም ለዚህ ነው።
ጎረቤት አገራት
የእስራኤል ጎረቤት አገራት ጉዳይም ይነሳል።
ከግብፅ ወደ ጋዛ የድንበር መግቢያ የሆነው ራፋ ሰብአዊ እርዳታ መተላለፊያ ሆኗል። ወደ ጋዛ የሚያሻግር ነው።
የሚገባው እርዳታ ግን ውስን ነው።
የውጭ አገር ዜጎች እና ፍልስጤማውያንም ለመውጣት እየተጠባበቁ ነው።
የእስራኤል ብሔራዊ ደኅንነት ጥናት ባለሙያው ኦፊር ዊንተር እንደሚለው፣ ጋዛ ውስጥ በእስራኤል ጥቃት ንጹሃን የበለጠ በተጎዱ ቁጥር ግብፅ ላይ ጫናው ይበረታል።
ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል-ሲሲ የጋዛ ነዋሪዎችን ወደ ሲናይ በረሃ ለማስገባት ሙከራ እንዳይደረግ አስጠንቅቀዋል።
“በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ግብፃውያን ወጥተው ይቃወማሉ” ብለዋል።
የዮርዳኖስ ንጉሥ አብዱላህም ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
“በዩርዳኖስ ስደተኞች አይኖሩም። በግብፅም ስደተኞች አይኖሩም” ብለዋል።
ፍልስጤማውያንን ከጋዛ ለማስወጣት መሞከርን “ቀይ መስመር” ብለውታል።
የእስራኤል እና ሊባኖስ ድንበርም በጥብቅ ጥበቃ ሥር ነው።
ሒዝቦላህ ከድንበር አሻግሮ በተደጋጋሚ ጥቃቶች ሰንዝሯል።
የሒዝቦላህ ዋነኛ ደጋፊ ኢራም ከእስራኤል ጋር “አዲስ የግጭት ግንባሮች” ለመክፈት አስፈራርታለች።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን “ማንኛውም አገር እና ተቋም በዚህ አጋጣሚ ለመጠም እንዳይሞክር” ሲሉ አንድም ኢራንን ለማስፈራራት ነው።
የአሜሪካ ሁለት አየር ጦር መሣሪያዎች ወደ ምሥራቃዊ ሜዲትራኒያን ከማስጠጋቷ ባሻገር 2,000 ወታደሮቿ በተጠንቀቅ እየተጠባበቁ ነው።

እስራኤል በጋዛ ያሰበችው ምንድን ነው?
ሐማስን በከፍተኛ ሁኔታ ማዳከም ቢቻል እንኳን ማን ይተካዋል? የሚለው ጥያቄ ቀጣይ ጉዳይ ነው።
እስራኤል በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን እና ሰፋሪዎቿን በ2005 ከጋዛ አስወጥታለች።
ወራሪ ኃይል ሆኖ ጋዛ የመመለስ ዕቅድም የላትም።
ይህ “ትልቅ ስህተት ይሆናል” ይላሉ ባይደን።
በቦታው የሚፈጠረው ክፍተት አስጊ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። አንዱ ችግር ቢፈታ እንኳን በምትኩ ሌሎች ተጨማሪ ችግሮች መፈጠራቸው ያሰጋል።
ኦፊር ዊንተር እንደሚለው፣ በቦታው የሚፈጠረው የኃይል ክፍተት የፍልጤኤም አመራር እንዲመለስ መንገድ ሊከፍት ይችላል። ይህ አመራር በሐማስ በ2007 ነው ከጋዛ እንዲወጣ የተደረገው።
የፍልስጥኤም አመራር አሁን ላይ የዌስንት ባንክን የተወሰነ ክፍል የሚቆጣጠር ቢሆንም ደካማ ነው።
ወደ ጋዛ እንዲመለስ ማሳመንም ቀላል አይሆንም።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለሽግግር የሚሆን መፍትሄ ሊያመጣ ይችላል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰርቢያ ኃይሎች በ1999 ከኮሶቮ ከወጡ በኋላ የሽግግር አካሄድን አዘጋጅቷል።
እስራኤል ግን በድርጅቱ ላይ ጥርጣሬ አላት።
ሌላው አማራጭ ጋዛ በከንቲባዎች፣ ጎሳዎች፣ ብሔረሰቦች እና ሌሎች አረብ አገራት የሚመራ አስተዳደር ማዋቀር ነው።
የግብፁ ፕሬዝዳንት ጋዛን ለማስተዳደር ፍላጎት ባያሳዩም “ከዚህ ቀደም ከወታደራዊ መዋቅር ነጻ የወጣ ቀጠና በንግግር እንደተገኘው ሁሉ አሁንም ያንን ማድረግ ይቻላል” ብለዋል።
የጋዛንየወደመ መሠረተ ልማት መልሶ ግንባታ ያስፍልጋል።
እስራኤል ቁሳቁሶች ላይ የበለጠ ቁጥጥር ማድረጓ አይቀርም። በተለይም ወታደራዊ አገልግሎት በሚኖራቸው ወደ ጋዛ የሚገቡ ቁሳቁሶች ላይ።
በጋዛ ድንበር ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ውጪ የሆነ ቦታ እንዲኖር ሲጠየቅ ቆይቷል። ይህም ለእስራኤላውያን ጥበቃ ለማድረግ ነው።
እስራኤል የጦርነቱ ውጤት ምንም ይሁን ምን እንዲህ ያለ ጥቃት ተመልሶ እንዳይደገም ማድረግ ትሻለች።