October 31, 2023 – Konjit Sitotaw
በፓርቲያችን አባል ሕልፈት የተሠማንን ሐዘን እየገለፅን አፋጣኝ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ እንጠይቃለን!! ሲል ኢዜማ ተደብድበው በአብይ ወታደሮች የተገደሉትን አባሉን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

በደቡብ ኢትዮድያ ክልል በጋሞ ዞን በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ በዛይሴ ልዩ ወረዳ የምርጫ ክልል ከ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የፓርቲያችን አባል ሆነው በንቃት ሲሳተፉ የነበሩት ወጣት ጋሻው ላጼ በግለሰቦች መሃል በተነሳ አለመግባባት በተፈጠረ ግጭት የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ግጭቱን በማስቆም ወደሚመለከተው የህግ አካል ማድረስ ሲገባቸው አድሎአዊነት በተሞላው መልኩ ግለሰቡ ላይ ባደረሱት ኢሰብዓዊ እና አሰቃቂ ድብደባ ምክንያት ጥቅምት 10/ 2016 ዓ.ም. ህይወቱ አልፏል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሟችን ጉዳይ በትኩረት ሲከታተሉ የነበሩ በሟች አከባቢ የሚገኙ የኢዜማ አባላትን የቀበሌ አጥር ደብድባቹሃል በሚል ምክንያት 28 የፓርቲያችን አባላት ለእስር ተዳርገዋል።
በአሰቃቂ ሁኔታ የአባላችንን ህይወት የነጠቁት እነኚህ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ መሆናቸውን እያሳወቅን ተገቢው የህግ ሂደት ተከትሎ ተጠያቂነት እንደሚሰፍን እንጠብቃለን። ከዚህ በተጨማሪ ህግን በመተላለፍ አባላችንን ከመግደል ባለፈ ሌሎች አባላቶቻችንን ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ለእስር መዳረግ መንግሥት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት ያለውን ግዴለሽነት አመላካች መሆኑን እየገለጽን አባሎቻችን ተገቢው የህግ ማጣሪያ ተደርጎ ከእስር እንዲፈቱ እንጠይቃለን።
ማንኛውም የመንግሥት የጸጥታ ኃይል በአከባቢው ላይ ለሚፈጠር ችግር የችግሩ ምክንያት የሆኑ ግለሰቦችን ወደ ህግ ቦታ ማቅረብ ሲገባው እንዲህ አይነት አድሎአዊነት የተሞላት ተግባራት ሲፈጽሙ እና ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ አካል ሲያጎድሉ እና ህይወት ሲነጥቁ መመልከት እንደ ባህል ያደገ ህገወጥነት መሆኑን እና በጽኑ የምናወግዘው መሆኑ በጥብቅ እንገልጻለን።
መንግሥት በሥራ ላይ የሚያሰማራቸውን የጸጥታ ኃይሎች በሥነምግባር እና ሙያዊ ችሎታ የታነጹ ሆነው ወደማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የማድረግ ኃላፊነቱን በቅጡ እንዲወጣ እንዲሁም ይህንን ጥሰው በሚገኙ አባላቱ ላይ ተገቢውን የህግ እርምጃ እየወሰደ የህግ የበላይነትን እንዲያረጋግጥ እንጠይቃለን።
በአባላችን ወጣት ጋሻው ላፄ ሞት የተሠማንን መሪር ሐዘን እየገለጸን ለአባላት ለቤተሰብ ለወዳጅ እና ዘመዶቹ ፈጣሪ ቶሎ መፅናናቱን እንዲሠጥ እንመኛለን።