የአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር በከፊል
የምስሉ መግለጫ,የአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር በከፊል

30 ጥቅምት 2023

በአማራ ክልል ለወራት በቀጠለው የትጥቅ ግጭት ምክንያት መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም. ባወጣው ዝርዝር መግለጫ ይፋ አደረገ።

ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ግጭቶች እየተካሄዱ ሲሆን፣ በክልሉ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉ ይታወቃል።

ኢሰመኮ እንዳለው ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. እስካሁን ድረስ በአማራ ክልል በሁሉም ዞኖች ውስጥ በተለያየ ደረጃ እና ጊዜ የትጥቅ ግጭት መካሄዱን አመልክቶ፣ “የትጥቅ ግጭቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በከባድ መሣሪያ እና አልፎ አልፎ በአየር/ድሮን ድብደባ ጭምር የታገዘ ነው” ሲል ገልጿል።

በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች በተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች የአንድ ዓመት ከሰባት ወር ሕፃንን ጨምሮ በርካታ ሲቪል ሰዎች እንደተገደሉ እና የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው የዐይን እማኞችን ዋቢ አድርጎ ቦታዎችን እና ቀናትን በመጥቀስ በሪፖርቱ ውስጥ አካቷል።

በዚህም ሳቢያ በአየር እና በከባድ መሣሪያዎች ጥቃት የተነሳ በአካባቢዎቹ ሲቪል ነዋሪዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱን እንዲሁም ነዋሪዎች ጥቃትን አልያም ግጭትን በመፍራት ቤታቸውን ትተው ከመኖሪያ አካባቢያቸው ለመሸሽ ተገደዋል ብሏል – ኢሰመኮ።

ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችም በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የጠቀሰው ኮሚሽኑ፣ “ከምንጃር ወረዳ የአውራ ጎዳና ጎጥ የተፈናቀሉ ቢያንስ 3000 የሚሆኑት ሰዎች በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ እና ሜዳ ላይ ከዛፍ ሥር ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ወደ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ሄደዋል” ብሏል።

ጨምሮም የነዋሪዎችን መፈናቀል ተከትሎ ሰብላቸው እንደወደመ፣ ንብረታቸው እንደተዘረፈ፣ የቤቶቻቸው ጣሪያ እና በር እየተነቀለ እንደተወሰደ፣ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ቤቶቻቸውን ከአጎራባች ክልል በመጡ ኃይሎች” በኮንስትራክሽን መሣሪያዎች ጭምር ማፍረስ እንደተጀመረ ኢሰመኮ የአካባቢውን ነዋሪዎች እና የመንግሥት ኃላፊዎችን ጠቅሶ ገልጿል።

በአማራ ክልል አብዛኞቹ አካባቢዎች ተግባራዊ በተደረገው የእንቅስቃሴ ገደብ እና የሰዓት እላፊ እንዲሁም በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት የተለያዩ ወረዳዎችን የሚያገናኙ የመንገድ መጓጓዣዎች በመቋረጣቸው፣ አልያም ውስን በመሆናቸው ምክንያት የንግድ እና የማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በፈጠረው ተጽዕኖ ነዋሪዎች ለአቅርቦት እጥረት እና ለዋጋ ንረት እንዲሁም ለተያያዥ ችግሮች መዳረጋቸውን ኢሰመኮ ጠቅሷል።

በአማራ ክልል በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት አንዳንድ ጊዜ ጋብ እያለ ሌላ ጊዜ ደግሞ እየተባባሰ ሲካሄድ ወደ ሦስት ወራት ተጠግቷል።

በግጭቶቹ ሳቢያም በተለያዩ የክልሉ አካባቢ መደበኛ እንቅስቃሴዎች እና የመሠረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት መስተጓጎሉን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ባለፈው ሳምንት ገልጸው ነበር።

እየተካሄዱ ካሉ ግጭቶች ጋር እና ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ያለመከሰስ መብት ያላቸው የፌደራል እና የክልል ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ከአማራ ክልል ባሻገር ባሉ አካባቢዎች ጭምር በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው በእስር ላይ ይገኛሉ።

በአማራ ክልል ካለው ግጭት ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ከሕግ ውጭ የሆኑ ግድያዎች አሳሳቢ መሆናቸውን ኮሚሽኑ መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ መግለጫ አውጥቶ የነበረ ሲሆን፣ ሆኖም በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የሚፈጸሙ ከሕግ ውጪ ግድያዎች ስለመቀጠላቸው “ተዓማኒ መረጃዎችን እየተቀበለ” መሆኑን ገልጿል።

ግጭት በተካሄደባቸው አካባቢዎች የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በመንገድ ላይ ወይም ቤት ለቤት ፍተሻ በማድረግ ከያዟቸው በርካታ ሲቪሎች ውስጥ “ፋኖን ትደግፋላችሁ፣ ለፋኖ መረጃ ትሰጣላችሁ፣ መሣሪያ አምጡ፣ የተኩስ ድምጽ ስለተሰማበት ስፍራ መረጃ ስጡ” በሚል እና በሌሎች ምክንያቶች ግድያዎች መፈጸማቸውን መረጃ እንደደረሰው ቦታዎችን እና የተገደሉ ሰዎች አሃዝን በማቅረብ ኮሚሽኑ አመልክቷል።

በክልሉ ውስጥ በሚገኙ የሕክምና ተቋማት ውስጥ በግጭቱ ቆስለው ሕክምና ሲከታተሉ የነበሩ የተወሰኑ ሲቪል ሰዎች እና በታጣቂ ቡድን አባልነት በመንግሥት የፀጥታ አካላት የተጠረጠሩ ሰዎች ሕክምናቸው እንዲቋረጥ ተደርጎ ወዳልታወቀ ስፍራ የተወሰዱ እና የደረሱበት ያልታወቁ ሰዎች እንዳሉ ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም ኮሚሽኑ ከመንግሥት ተቋማት ጭምር ባገኛቸው መረጃዎች መሠረት ከግጭቱ ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ የመድፈር ድርጊቶች በጣም አሳሳቢ እና በአፋጣኝ ተገቢው ምርመራ ተደርጎ እርምጃ ሊወሰድበት እንደሚገባ አሳስቧል።

ኮሚሽኑ የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት በተለያዩ የጤና ተቋማት መድረስ የቻሉትን ተጎጂዎች ቁጥር ብቻ መሠረት አድርጎ ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ቢያንስ 200 የመድፈር ተጎጂዎች በጤና ተቋማት ተመዝግበዋል፤ ከተጎጂዎች መካከልም ተፈናቃይ ሴቶች እና የጤና ባለሞያ ሴቶች ጭምር ይገኙበታል።

ኢሰመኮ ባወጣው ሪፖርት ላይ የመብት ጥሰቶች በታጣቂ ኃይሎችም መፈጸማቸውን ጠቅሶ፤ በዚህም በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ ሲቪል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች፣ ግድያዎች እና እገታዎች ተፈጽመዋል ብሏል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በአማራ ክልል ያለውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት ሰላማዊ አማራጮች ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ጠይቀው፣ የግጭቱ ተሳታፊዎችም ሲቪሎችን እና ንብረቶችን፣ የሕዝብ አገልግሎቶችን እና መሠረተ ልማቶችን በማናቸውም ሁኔታ ዒላማ እንዳያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም “በቁጥጥር ሥር የዋሉ የታጠቁ ኃይሎች አባላት እና ሌሎች ተጠርጣሪዎች ሁኔታ በሕጋዊ አግባብ ብቻ እንዲስተናገድ፤ በተለይም የመድፈር ወንጀል እና ከሕግ ውጪ የተፈጸም ግድያን በአስቸኳይ በማጣራት ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ” በማለት ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ይህንን ሪፖርት ለማዘጋጀት የመንግሥታዊ ኃላፊዎችን፣ በግጭቱ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን፣ የዐይን ምስክሮችን፣ ተጎጂዎችን እና የተጎጂዎች ቤተሰቦችን በማነጋገር መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን አመልክቷል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎችን በማፍረስ መልሶ ለማደራጀት እንዲሁም ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በአማራ ክልል ተቃውሞ ገጥሞታል።

በዚህም ምክንያት በክልሉ ውስጥ ያሉ ታጣቂዎች ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር ተደጋጋሚ ግጭት አካሂደው በርካታ ትላልቅ ከተሞችን መቆጣጠር ችለው ነበር።

ይህም ሁኔታ ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑን በመግለጽ የክልሉ መስተዳደር የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ በጠየቀው መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ የመከላከያ ሠራዊት ተሰማርቶ ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ለወራት የዘለቀ ግጭት እየተካሄደ ነው።