ፕሬዝደንት ባይደን

ከ 4 ሰአት በፊት

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ኡጋንዳ፣ ጋቦን፣ ኒጀር እና ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክን ከአጎዋ ስምምነት ሊሰርዙ እንዳቀዱ ይፋ አደረጉ።

ፕሬዝደንቱ እንደገለጡት አገራቱ አንድ “ጅምላ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል” አሊያም ዴሞክራሲያዊ ዕድገታቸው የዘገመ ነው።

አፍሪካ ግሮውዝ ኤንድ ኦፖርቹኒቲ አክት የተሰኘ መጠሪያ ያለው አጎዋ፤ በአውሮፓውያኑ 2000 ነው የተቋቋመው።

በዚህ ማዕቀፍ መሠረት ፈቃድ የተሰጣቸው ከሰሃራ በታች ያሉ አገራት ከ1800 በላይ ምርቶችን ከቀረጥ ነፃ ወደ አሜሪካ መላክ ይችላሉ።

ፕሬዝደንት ባይደን በአሁኑ ወቅት በወታደራዊ አመራር እየተዳደሩ ያሉት ኒጀር እና ጋቦን ከአጎዋ ማዕቀፍ ሊሰረዙ የሚችሉት “ፖለቲካዊ ብዝሃነት እና የሕግ የላይነትን ማስከበር ባለመቻላቸው ነው።”

ጋቦን እና ኒጀር በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት በመፈንቅለ መንግሥት ሲታመሱ እንደነበር ይታወሳል።

ባይደን አክለው ኡጋንዳ ከአጎዋ ማዕቀፍ ልትሰረዝና ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጣልባት የታሰበው ሃገሪቱ አከራካሪውን ፀረ-ተመሳሳይ ፆታ ሕግ በማውጣቷ ነው።

የተማሳሳይ ፆታ ወሲብ ሲፈፅሙ የተያዙ ግለሰቦች እስሞከት ድረስ ሊቀጡ ይችላሉ የሚለው ሕግ ዓለም አቀፍ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር።

ፕሬዝደንት ባይደን ለአሜሪካ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ በላኩት ደብዳቤ ነው ይህን ዕቅዳቸውን የገለጡት።

“ምንም እንኳ ዩናይትድስ ስቴትስ ከማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ጋቦን፣ ኒጀር፣ እና ኡጋንዳ ጋር ውይይት ብታደርግም ሃገራቱ የአጎዋን መተባበር የሚለውን ሐሳብ መጣሳቸው ዩኤስን አሳስቧታል” ብለዋል።

አራቱ የአፍሪካ አገራት እስካሁን ያሉት ነገር የለም።

20ኛው የአጎዋ ፎረም ከሚመጣው ሐሙስ ጀምሮ በደቡብ አፍሪካ ይካሄዳል።

አገራቱ ከአጎዋ ማዕቀፍ የሚሰረዙት ከሚቀጥለው የአውሮፓውያኑ ዓመት መባቻ ጀምሮ ሲሆን ምጣኔ ሃብታቸውን ሊጎዳቸው እንደሚችል ይታመናል።

አጎዋ የተሳታፊ አገራትን የውጭ ገበያ፣ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት እና የሥራ ፈጠራ በማሳደግ ይወደሳል።

አጎዋ

የአሜሪካ መንግሥት መረጃ እንደሚጠቁመው ከአራቱ አገራት መካከል ማዕከላዊ አፍሪካ ሪብሊክ ባለፈው ዓመት ወደ አሜሪካ የላከችው ዕቃ ዋጋ 881 ሺህ ዶላር ብቻ ሲሆን ከሌሎቹ ዝቅ ያለ ነው።

በተቃራኒው ከአሜሪካ ወደ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የገቢ ንግድ መጠኑ 23 ሚሊዮን ዶላር መሆኑ በገቢና በወጭ ንግድ መካከል ያለውን ልዩነት ሰፊ አድርጎታል።

ኡጋንዳ ባለፈው ዓመት 174 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ዕቃ ወደ ውጭ ስትልክ፣ ጋቦን 220 ሚሊዮን ዶላር፣ ኒጀር ደግሞ 73 ሚሊዮን ዶላር አስመዝግበዋል።

ባለፈው ወር የኡጋንዳው ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በፀረ-የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ሕግ ምክንያት በርካታ የአሜሪካ ኩባንያዎች ጨርቃጨርቅ ማስመጣት ማቆማቸውን ተናግረዋል።

“የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት አቀንቃኞች የጨርቃጨርቅ የወጭ ንግዳችን ውስጥ ጣልቃ ገብተዋል። ትዕዛዝ የፈፀሙ ሁሉ መሰረዝ ጀምረዋል” ብለዋል ሲል ዴይሊ ሞኒተር ጋዜጣ ዘግቧል።

ባለፈው ነሐሴ ሙሴቬኒ የተለበሱ ልብሶች [ሰልባጅ] ወደ ሃገር ቤት እንዳይገቡ ያገዱ ሲሆን፤ ይህ እርምጃ ወደ ኡጋንዳና ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት የተለበሱ ጨርቆች የምትልከው አሜሪካን ለመንካት የታሰበ ነው ተብሏል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ለጋቦን የሚደረገው እርዳታ ከሞላ ጎደል መቋረጡን ገልጦ ሃገሪቱ የሽግግር መንግሥት ካቋቋመች ብቻ እርዳታ ሊቀጥል እንደሚችል አሳውቋል።

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ባለፈው ነሐሴ ኒጀር ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ጠቁመዋል።

ዩኤስ “የኒጀር መንግሥትን ሊጠቅሙ የሚችሉ የውጭ እርዳታዎችን ገታ ለማድረግ አስባለች” ብለው ነበር።

ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ እና ጊኒ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደባቸው በኋላ ከዚህ ቀደም ከአጎዋ ማዕቀፍ የተሰረዙ ሃገራት ናቸው።