
ከ 2 ሰአት በፊት
ፈረንሳይ የሚገኝ አንድ ደላላ 150 ዩሮ የገዛውን ጥንታዊ ጭምብል በ4.2 ሚሊዮን ዩሮ በመሸጡ ሕግ ፊት ቀርቧል።
ሰውዬው ጭምብሉን የገዛው ከሁለት ጡረተኛ ጥንዶች ነው።
ጥንዶቹ ከአንድ የቅኝ ግዛት ጊዜ አገረ ገዥ ቤት ያገኙትን ከጋቦን የመጣ ጭምብል ነው ለደላላው የሸጡለት።
በአውሮፓውያኑ 2021 ለግለሰቡ ከሸጡት ከስድስት ወራት በኋላ ጭምብሉ ለጨረታ ቀርቦ ሲመለከቱ ነው ጉዳዩ ይፋ የሆነው።
ማክሰኞ ዕለት የተከፈተውን ችሎት ተከትሎ የጋቦን መንግሥት ጉዳዩ እንዲቆምና ጭምብሉ እንዲመለስ ጠይቋል።
ማዕከላዊ ፈረንሳይ የሚኖሩት በ80ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙት የዕድሜ ባለፀጋ ጥንዶች ከግለሰቡ ጋር የተገናኙት ቤታቸውን እንዲያፀዳላቸው ከተስማሙ በኋላ ነው።
ቤቱ ሬኔ-ቪክተር ፎርኒዬ የተሰኘ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ቅኝ ገዢ የነበረ ግለሰብ ቤት ነው።
ከእንጨት የተሠራው ጭምብል የተገኘው አንድ መደርደሪያ ውስጥ ነው።
ሰውዬው በ150 ዩሮ የገዛው ጭምብል ይህን ያህል ዋጋ እንዳለው አላውቅም ነበር ሲል ይከራከራል።
- ዝናቸው ከኬንያ እስከ ኒው ዮርክ የተሻገረው የ84 ዓመቱ የ1ኛ ክፍል ተማሪከ 5 ሰአት በፊት
- አሜሪካ የጋዛ የተኩስ አቁም ጥሪን ውድቅ አደረገች31 ጥቅምት 2023
- የንጉሥ ቻርለስ የኬንያ ጉብኝትና የማኦ ማኦ አርበኞች ቅሬታ31 ጥቅምት 2023
በፈረንሳይዋ ሞንፒዬሌ ከተማ ጨረታው በተከፈተ ወቅት የተነበበው ፅሑፍ እንደሚጠቁመው ጭምብሉ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ፋንግ የተባሉት የጋቦን ብሔረሰቦች የሠሩት ነው።
አክሎ ፎርኒዬ የተባለው ግለሰብ በ1917 ጭምብሉ ባልታወቀ ምክንያት እጁ እንደገባ ያስነብባል።
አንድ አጥኚ እንደሚሉት በወቅቱ የፋንግ ብሔረሰብ 10 መሰል ጭምብሎችን ብቻ ነው የሠሩት።
“ይህ ጭምብል ከሊዮናርዶ ዳ ቪንቺ ሥዕል የበለጠ ዋጋ አለው” ሲሉ ባለሙያው ለፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
ጨረታው ሲከፈት ጭምብሉ የወጣለት ዋጋ 300 ሺህ ዩሮ ቢሆንም አንድ ስሙ ያልተጠቀሰ ግለሰብ በ4.2 ሚሊዮን ዩሮ ገዝቶታል።
ይሄኔ ነው ጥንዶቹ ሽያጩን እንዲቆም በመጠየቅ ክስ ያቀረቡት።
የጋቦን መንግሥት ደግሞ ጭምብሉ ተሰርቆ በመሄዱ ሊመለስ ይገባል የሚል ቅሬታውን ገልጾ ችሎቱ ጉዳዩን ገታ እንዲያደርገው ጥያቄ አቅርቧል።
በአውሮፓውያኑ 2020 የፈረንሳይ ፓርላማ በቅኝ ግዛት ጊዜ የተዘረፉ የሴኔጋል እና የቤኒን ጥንታዊ ንብረቶች እንዲመለሱ መወሰኑ ይታወሳል።
ፈረንሳይ 90 ሺህ ገደማ ከአፍሪካ በተለይ ደግሞ ከሰሃራ በታች አፍሪካ አገራት የተወሰዱ ጥንታዊ ቁሳቁሶች አሏት።