
ከ 2 ሰአት በፊት
በእስራኤል እና በጋዛ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ በአሜሪካ ፀረ ሴማዊነት በታሪካዊ ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑን የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ክሪስቶፈር ራይ አስጠነቀቁ።
ዳይሬክተሩ ለአሜሪካ ምክር ቤት እንደተናገሩት 60 በመቶ የሚሆሙ መሠረታቸውን ሃይማኖት ላይ ያደረጉ የጥላቻ ጥቃቶች አይሁዶች ላይ ያነጣጠሩ ናቸው።
በጋዛ እየተካሄደ ባለው ግጭት ሳቢያ ቁጣ በመኖሩ ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችልም አክለዋል።
ፀረ ሴማዊነት አመለካከት ከፍ ማለቱን ተከትሎ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይ ጨምሮ ሌሎች አገራትም በቅርቡ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
- በእስራኤልና ሐማስ ጦርነት የቻይና ፍላጎት እና ሚና ምንድን ነው?ከ 3 ሰአት በፊት
- እግረኛ ጦሯን ወደ ጋዛ ያሰማራችው እስራኤል የምትፈልገውን ግብ ማሳካት ትችላለች?31 ጥቅምት 2023
- አሜሪካ የጋዛ የተኩስ አቁም ጥሪን ውድቅ አደረገች31 ጥቅምት 2023
ራይ ለምክር ቤቱ የአገር ውስጥ ደኅንነት እና የመንግሥት ጉዳዮች ኮሚቴ፤ “ይህ ስጋት ታሪካዊ ወደሚባል ደረጃ እያደገ ነው” ብለዋል።
አክለውም አይሁዶች ከአሜሪካ ሕዝብ 2.4 በመቶ ያህሉን ቢይዙም፣ ከሃይማኖታዊ ጥላቻ ወንጀሎች 60 በመቶ ያህሉ እንደሚገጥማቸው ተናግረዋል።
“ይህ የፍርሃት ጊዜ ሳይሆን የንቃት ጊዜ ነው። ወደ ትምህርት ቤቶች፣ የአምልኮ ቤቶች እና የመሳሰሉትን የዕለት ተዕለት ሕይወታችንን መምራት ማቆም የለብንም ። ንቁ መሆን ግን ይጠበቅብናል” ሲሉ አክለዋል።
በአሜሪካ እና በሌሎች አገራት ያሉ ባለሥልጣናት በአይሁዶች ላይ ከፍተኛ ስጋት መፈጠሩን አስተውለዋል። በኮርኔል ዩኒቨርሲቲ በአይሁድ ተማሪዎች ላይ ዛቻ ከተሰነዘረ በኋላ የኒው ዮርክ ባለሥልጣናት አንድን ግለሰብ ላይ ምርመራ ማድረጋቸው ተነግሯል።
የባይደን አስተዳደር ከአካባቢ፣ ከግዛቶች እና ከፌዴራል ባለሥልጣናት ጋር ግንኙነቶችን በማሳደግ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ፀረ-ሴማዊነትን እንዲሁም ሌሎች የጥላቻ ንግግሮችን ለመዋጋት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።