የቻይናና አሜሪካ ልዑክ

ከ 3 ሰአት በፊት

ቻይና እየተባባሰ ለመጣው የእስራኤልና ሐማስ ጦርነት መፍትሄ ለመስጠት የሰላም አደራዳሪ የመሆን ፍላጎት አሳይታለች።

የቻይና ከፍተኛ ዲፕሎማት ዋንግ ይ፣ ዋሽንግተን ካሉ ባለሥልጣኖች ጋር ከሰሞኑ ውይይት አድርገዋል።

አሜሪካ ከቻይና ጋር ለመሥራት ፍላጎት አሳይታለች።

ዲፕሎማቱ ከእስራኤል እና ፍልስጤም አቻዎቻቸው ጋር ተነጋግረዋል።

የቻይና የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ ልዑክ ዛይ ጁን የአረብ አገራት መሪዎችን አግኝተዋል።

ቻይና በተባበሩት መንግሥታት ውይይት የተኩስ አቁምን በከፍተኛ ሁኔታ ስትደግፍ ነበር።

ቻይና ከኢራን ጋር ባላት ግንኙነት መሠረት ሐማስ ላይ ጫና ማሳደርና ሁኔታውን ማርገብ ይቻላል የሚል ተስፋ አለ።

የአሜሪካ ባለሥልጣኖች የቻይናው ከፍተኛ ዲፕሎማት መረጋጋት እንዲሰፍን እንዲጠይቁ መንገራቸው ተዘግቧል።

በሌላ በኩል ቻይና የኢራን ዋነኛ የንግድ አጋር ናት።

ዘንድሮ በኢራን እና ሳዑዲ አረቢያ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻሻል ቻይና አደራዳሪ ሆናለች።

ኢራን ከቻይና ጋር ያላትን “ግንኙነት በማጠናከር” ለጋዛ መፍትሄ ለመፈለግ ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች።

የቻይና መንግሥት በግጭቱ ካሉት አጠቃላይ ባለድርሻ አካላት ጋር ጤናማ ግንኙነት አለው።

በአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሥር በሚገኘው ናሽናል ዋር ኮሌጅ የቻይና የውጭ ጉዳይ የሚያጠኑት ዳውን መርፊ እንደሚሉት፣ ቻይና እንደ ታማኝ አደራዳሪ ልትታይ ትችላለች።

ቻይና ከፍልስጤም፣ ከአረብ አገራት፣ ከቱርክ፣ ከኢራን ጋር ጤናማ ግንኙነት ነው ያላት።

“ከእስራኤል ጋር ጥሩ ግንኙነት ካላት አሜሪካ ጋር በመሆን ሁሉንም አካላት ወደ ውይይት ጠረጴዛ ማምጣት ይቻላል” ይላሉ ተንታኙ።

የአትላንቲክ ካውንስል ባለሙያ ጆናታን ፉልቶን በበኩላቸው “ቻይና በቁም ነገር የምትወሰድ አይደለችም። ከቀጠናው አካላት ጋር ተነጋግራ መፍትሄ እንድታመጣ ማንም አይጠብቅም” ይላሉ።

ቻይና ግጭቱ እንደተነሳ የሰጠችው አስተያየት እስራኤልን አስቆጥቷል። ሐማስን አለመኮነኗ እና እስራኤል ራሷን መከላከል መብቷ ነው አለማለቷ “በጣም ያሳዝናል” በማለት ተችታለች።

በሐማስ ጥቃት 1,400 ሰዎች ሲገደሉ ቢያንስ 239 ታጋቾች ተወስደዋል።

እስራኤል በፈጸመችው የአየር ድብደባ እስካሁን ከ8,000 በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።

የቻይናው ከፍተኛ ዲፕሎማት “ሁሉም አገራት ራሳቸውን የመከላከል መብት አላቸው” ሲሉ ለእስራኤል ነግረዋል።

“የእስራኤል ድርጊት ራስን ከመከላከል ያለፈ ነው” ሲሉም በሌላ ጊዜ ተናግረዋል።

ቻይና ለፍልስጤማውያን ተቆርቋሪነቷን ስታሳይ እንደመቆየቷ፣ አሁን ለሰላም ድርድር ሚዛናዊነት መጠበቅ ይጠበቅባታል።

የቻይና ኮምኒስት ፓርቲ መሥራች ማኦ ዘዶንግ በመላው ዓለም የፍልስጤም “ብሔራዊ የነጻነት ንቅናቄ” ለመደገፍ መሣሪያ ልከው ነበር።

እስራኤልን ከታይዋን በማነጻጸርም ንግግር አድርገዋል።

ሁለቱንም በአሜሪካ የሚደግፉ የምዕራባውያን ኢምፔሪያሊዝም መቀመጫ አድርገው ነው የገለጿቸው።

ቻይና ከማኦ ዘዶንግ በኋላ ባሉ ዓመታት ከእስራኤል ጋር ግንኙነት በማደስ የምጣኔ ሀብት ትስስር ፈጥረዋል።

በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር የንግድ ግንኙነት ነው በአሁን ወቅት ያላቸው።

ቻይና ፍልስጤማውያንን መደገፍ እንደምትቀጥል አስታውቃለች።

ፕሬዝዳንት ዢ ዢፒንግን ጨምሮ የቻይና ባለሥልጣኖች ነጻ የፍልስጥኤም አገር መመሥረት እንዳለበት ሲናገሩ ተደምጧል።

ጋዛ

የእስራኤልን ድርጊት ከናዚ ጋር የሚያነጻጽሩ ጽሑፎች በቻይና ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተሰራጭተዋል።

ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ጭፍጨፋ እየፈጸሙ ነው የሚሉ ጽሑፎችም ተነበዋል።

በቤጂንግ የጀርመን ኤምባሲ ይህንን ኮንኗል።

በቤጂንግ የእስራኤል ኤምባሲ ሠራተኛ ቤተሰብ በስለት መወጋት ሌላው ጉዳይ ነው።

ቻይና እነዚህ ነገሮች ሁሉ እንዳሉ ሆነው ነው የሰላም ስምምነት ለመስጠት ፍላጎት ያሳየችው።

ቻይና በዚህ ጉዳይ ጣልቃ ከምትገባበት ምክንያት አንዱ በመካከለኛው ምሥራቅ ያላት የንግድ ፍላጎት ነው።

ይህም ጦርነቱ ከተስፋፋ አደጋ ውስጥ ይወድቃል።

ቻይና ነዳጅ የምታስገባው ከገልፍ አገራት መሆኑም ሌላው ነጥብ ነው።

የቻይና ቤልት ኤንድ ሮድ ዋነኛ ተዋናዮች የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ናቸው።

ቻይና በዚህ ጦርነት ሰላም በማውረድ ስሟን መገንባት ትሻለች።

ከፍልስጤማውያን ጎን መቆም ከፍተኛ የሙስሊም ቁጥር ባላቸው በአረብ አገራት የተሻለ ዕይታ እንድታገኝ እንደሚረዳት ታምናለች።

ቻይና ከአሜሪካ የተሻለች አማራጭ መሆኗን ዓለም እንዲያውቃላት በምትሻበት ወቅት ነው ይህ ጦርነት የተነሳው።

ቻይና-መር አካሄድ በዓለም እንዲሰፍን ቻይና እየገፋች ትገኛለች።

ዢ እና አባስ

አሜሪካ እስራኤልን በመደገፏ ቻይና በይፋ አልወቀሰችም።

ግን በብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን በመካከለኛው ምሥራቅ የሚፈጠረውን ነገር አሜሪካ ለእስራኤል ካላት ድጋፋ ጋር ለማስተሳሰር ሙከራዎች እንዳሉ ይገለጻል።

የቻይና ወታደራዊ ጋዜጣ ፒኤልኤ ዴይሊ፣ አሜሪካ ነገሩን እንዳባባሰች ከሷል።

ቻይና በምዕራባውያን ዘንድ ያላትን ዕይታ የምትለውጥበት አካሄድም እንደሆነ ተንታኞች ይናገራሉ።

ሐማስን አለማውገዟ ምናልባትም ከያዘችው አቋም ጋር የሚቃረን ሊሆንም ይችላል።

ቻይና ያሰበችውን እንዳታደርግ መሰናክል ከሚሆኑ መካከል የአገሪቷ የቀደመ ታሪክ አንደኛው ነው።

ሙስሊሞች በብዛት የሚኖሩበትን አገር በመደገፍ የእስራኤልን አስገዳጅ ይዞታ ቻይና ትኮንናለች። ግን ደግሞ በቻይና የኡግሁር ሙስሊሞች ላይ የሚደርሰው የሰብአዊ መብት ጥሰትና ቲቤትን በግዳጅ የግዛት አካል የማድረግ አካሄድ ከዚህ ተጻራሪ ነው።

ቻይና ከአራብ አገራት ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረቷ ይሄ ችግር እንዳይሆን ሊረዳ እንደሚችል ተንታኞች ይናገራሉ።

ቻይና የሐማስ እና እስራኤልን ጦርነት የራሷን ገጽታ ለመገንባት እየሞከረች ወይም የታይታ ጥረት እያደረገች ነው ተብሎ መታሰቡ ሌላው መሰናክል ይሆናል።

የቻይናው ከፍተኛ ዲፕሎማት እንደሚሉት የቻይብ ብቸኛ ግብ በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ማስፈን ነው።

“በፍልስጤም ጥያቄ ውስጥ ራስ ወዳድ የሆነ ፍላጎት የለንም” ብለዋል።

ፈተናው የሚሆነው ይህንን አቋን ለዓለም ማሳመን ነው።