ሉዊስ ዲያዝ
የምስሉ መግለጫ,ሉዊስ ዲያዝ

ከ 1 ሰአት በፊት

የኮሎምቢያ ፖሊስ የታገቱትን የሊቨርፑሉን ኮከብ ተጫዋች አባት ለማግኘት ፍለጋውን በአገሪቱ ተራራማ ቦታዎች ማድረጉ ተሰማ።

ከጥቂት ቀናት በፊት የሊቨርፑል የክንፍ መስመር ተጫዋች ሉዊስ ዲያዝ ወላጆች በታጣቂዎች የመታገታቸው ዜና መሰማቱ ይታወሳል።

የአገሪቱ ጦር ከፖሊስ ጋር ተጣምሮ በሰሜናዊ ኮሎምቢያ ባደረገው ክትትል የተጫዋቹን እናት እሁድ ዕለት አግኝቶ ነበር።

የአገሪቱ ጦር የተጫዋቹን ወላጅ አባት ለማግኘት 120 ወታደሮችን በማሰማራት የመንገድ ላይ ፍተሻዎችን እያደረገ መሆኑን፣ ሄሊኮፍተር ጨምሮ በሰው አልባ አውሮፕላን ፍለጋ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

የአገሪቱ መንግሥት የሉዊስ ዲያዝን አባት ለማግኘት የሚያስችል መረጃ ለሰጠ 40ሺህ ፓውንድ ወሮታ እከፍላለሁ ብሏል።

ምንም እንኳ የኮሎምቢያ መንግሥት የተጫዋቹ እናት እና አባት በምን ሁኔታ እንደታገቱት ያለው ነገር ባይኖርም የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ሉዊስ ማኔኤል ዲያዝ እና ሲሌኒስ ማሩላንዳ የተባሉት ወላጆቹ ነዳጅ ማደያ አቅራቢያ ሞተር ሳይክል ላይ በነበሩ የታጠቁ ሰዎች ታፍነው መወሰዳቸውን ዘግበዋል።

የተጫዋቹ ወላጆች የመታገታቸው ዜና እንደተሰማ ክለቡ ሊቨርፑል እና የቡድን አባላት ለዲያዝ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ሲገልጹ ቆይተዋል።

ፊፋም እንዲሁ በፕሬዝዳንቱ ጊያኒ ኢንፋንቲኖ በኩል “በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለተጫዋቹ እና ለቤተሰቡ ድጋፋችንን እንገልጻለን” ብሏል።

የኮሎምቢያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም የተጫዋቹ አባት ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ይለቀቁ ሲል ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።

ከትናንት በስቲያ እሁድ ሊቨርፑል ከኖቲንግሃም ፎረስት በነበረው ጨዋታ ዲያዝ ሳይጨወት ቀርቷል።

የክለቡ ምክትል አሰልጣኝ ትናንት ምሽት ከጨዋታ በፊት በነበረ መግለጫ ላይ ዲያዝን “በጸሎታችን እያሰብነው ነው” ብለዋል። ምክትል አሰልጣኝ ፔፒጀን ሊጀናደርስ “በተቻለን መጠን ልንደግፍ ይገባል፤ አብዛኛዎቹ ነገሮች ከእኛ ቁጥጥር ውጪ ናቸው” ብለዋል።

“ጸጥታ አስከባሪዎች አባቱን ያገኟቸዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤ ያ እንዲሆን ጸሎታችን ነው” ብለዋል።

የኮሎምቢያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፍራንሲስ ባርቦሳ ምርመራውን በተመለከተ ለዲያዝ ማብራሪያዎችን እየሰጡት መሆኑን ገልጸው፤ ምናልባት ወላጅ አባቱ ወደ ቬንዙዌላ ሳይሻገሩ እንደማይቀር ለተጫዋቹ ነግሬዋለሁ ብለዋል።