
ልናገር የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታና ልዩ ትኩረት በአፋር ሦስት ማዕዘናዊ አቀማመጥ
ቀን: November 1, 2023
(የመጨረሻው ክፍል)
በተሾመ ብርሃኑ ከማል
ውድ አንባቢያን በዚህ ጽሑፍ በክፍል አንድና ሁለት የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲክስ ሲባል ምን ማለት እንደሆነና ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ካሉት አገሮች ቀዳሚ ተጠቃሚ መሆኗን ከጥንታዊ ታሪኳ ተነስተን በትንሹም ቢሆን አቅርቤያለሁ፡፡ ኢትዮጵያ የባህር ድንበሯን እንዴት አጣች ለሚለው ጥያቄም መጠነኛ መልስ ተሰጥቷል፡፡ በመጨረሻም በኤርትራ ሪፈረንደም ምክንያት እንዴት ወደቧን እንዳጣች ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ብትሆንም በወደቦች የመጠቀም መብት እንዳላት የሚጠቁመው ጽሑፍና የማጠቃለያ ሐሳብ ይሰጣል፡፡
ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ብትሆንም በወደቦች የመጠቀም መብት አላት
የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ታሪክ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የሚተነተን ቢሆንም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በርካታ አገሮች ወደብ አልባ እንደሆኑት ሁሉ፣ ኢትዮጵያም የዚህ መጥፎ የታሪክ አጋጣሚ ሰለባ ሆናለች፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወደብ የሌላቸውን አገሮች በሚመለከት በጠራው የመጀመርያ ጉባዔ አሥር የነበሩት አገሮች በሦስተኛው ጉባዔ ቁጥራቸው ወደ 42 ከፍ ማለቱም ይህንን እውነታ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ ከእነዚህም ወደብ አልባ አገሮች ውስጥ 15 በአፍሪካ፣ 13 በአውሮፓ፣ 12 በእስያ ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ በደቡብ አሜሪካ ይገኛሉ፡፡
የወደብ አልባ አገሮች ቁጥር ወደፊትም እየጨመረ ይሄዳል የሚል ግምት ሲኖር፣ በጎረቤት አገሮች ወደቦች የመጠቀም መብታቸው እየተጠናከረ ይሄዳል የሚል እምነት አለ፡፡ እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 10 ቀን 1982 ባህርን በሚመለከት የወጣው የተመድ ዓለም አቀፍ ስምምነት የሚያረጋግጠውም ይህንኑ ሀቅ ነው፡፡ ወደብ የሌላቸው አገሮች ለምን በጎረቤት አገሮች ወደብ ያላንዳች ተፅዕኖ መጠቀም እንደሚገባቸው የሚጠቁሙት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ለምሳሌ የአሜሪካ ንግድ ከውጭ ንግድ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው፡፡ ይህም ከውጭ ንግድ ጋር የተያያዘ እንቅስቃሴ ከ80 እስከ 90 በመቶ ያህሉ የተመሠረተው በባህር ላይ ነው፡፡ የእነዚህ አገሮች ንግድ ከባህር በር ተነጥሎ ማየት አይቻልም፡፡
ይህም ሆኖ በአፍሪካና በእስያ አገሮች መካከል ያለው ሁኔታ ሲታይ ወደብ የመጠቀም ዓለም አቀፍ መብታቸውም ከፖለቲካ ጋር እየተያያዘ ችግር ሲፈጠርባቸው ይታያል፡፡ በዚህም የተነሳ የፖለቲካ ውዝግብ ሲኖር ወደብ አልባ የሆኑ አገሮች በቅርብ ባለ ወደብ ለመጠቀም ባመቸላቸው ሩቅ በሆነ ወደብ ሲጠቀሙ ይታያሉ፡፡ እንዲህ ያለው ችግር በአወሮፓ ሲኖር የመንገድና የትራንስፖርት አገልግሎቱን በማፋጠን ወይም ተራራና ገደል ሰርስረው በማሳጠር የሚደርስባቸውን ኢኮኖሚያዊ ችግር ለማቃለል ይሞክራሉ፡፡ በአፍሪካና በእስያ አገሮች ግን ተራራ ሰርስሮ መንገድ በማሳጠር ወይም የመጓጓዣ መሣሪያዎችን በማዘመን፣ ወይም በአውሮፕላን የመጠቀም አቅማቸው ደካማ በመሆኑ በዚህ ረገድ የሚገጥማቸው ፈተና በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ አቅም ቢኖራት ኖሮ ከጂቡቲ መንግሥት ጋር በመስማማት የጂቡቲን ተራሮች ፈልፍላ ቀይ ባህርን አመቺ እስከሆነ የአፋር ክልል ወረዳ ድረስ ወደ ውስጥ በማስገባት ባለወደብ መሆን ትችል ነበር፡፡ ዳሩ ግን ይህ ምኞት በመሆኑ በአካባቢው የሚገኙ የወደብ ርቀትን በሚመለከተው በኪሎ ሜትር ሒሳብ እንመልከት፡፡
ድሬዳዋ ከጂቡቲ ወደብ 1‚163 ኪሎ ሜትር፣ አዲስ አበባ ከአሰብ ወደብ 869 ኪሎ ሜትር፣ ጂቡቲ መንገድ 91ዐ ኪሎ ሜትር፣ በጋላፊ 847 ኪሎ ሜትር፣ በድሬዳዋ በርበራ 964 ኪሎ ሜትር፣ ከድሬዳዋ ቦሳሶ 2‚231 ኪሎ ሜትር፣ በጋሩዌ፣ በበይራ፣ በዋርዴር፣ በዓለማያና በሞቃዲሾ 1‚451 ኪሎ ሜትር፣ በበለደዌ፣ በፌርፌር፣ በሻሸመኔ፣ በሞያሌ፣ በሞምባሳ 2‚077 ኪሎ ሜትር ነው፡፡
ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በፖርት ሱዳን፣ በበርበራ፣ በቦሳሶ፣ በሞቃዲሾ፣ በኪሲማዩና በሞምባሳ፣ እንዲሁም በሌሎች አገሮች የውጭ ዕቃ በማስገባትና የአገር ውስጥን ዕቃ ለማስወጣት ለመጠቀም የምትችል ቢሆንም ለሁሉም ዋና ዋና ከተሞች ከምፅዋ፣ ከአሰብና ከጂቡቲ የቀረበ የሌለ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ በእነዚህ አገሮች የመጠቀም መብቷ በማንኛውም ዓይነት ፖለቲካ ተፅዕኖ ሥር መውደቅ የሌለበት መሆኑን ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1997 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የባህር ትራንስፖርትን የሚመለከተው አካልም ከዚህ አኳያ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡ ይልቁንም በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ በመራመድ ላይ ለምትገኘውና ሕዝቧን ከድህነት ለማላቀቅ ጥረት በማድረግ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ በጎረቤት ወደቦች የመጠቀም መብት በማንኛውም ሁኔታ የሚገሰስ አይደለም፡፡
በዚህም መሠረት፣ ኤርትራ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ ሕጎችን በመፃረር መሬት ቆርሳችሁ ካልሰጣችሁኝ፣ ወይም እኔ እንደፈለግሁ ካልፈነጨሁባችሁ በወደቤ መጠቀም አትችሉም ለማለት የምትችልበት ምክንያት መኖር የለበትም፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ይህንን በዝምታ ሊመለከተው አይገባም፡፡
እ.ኤ.አ. በ1997 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የባኅር ትራንስፖርትን የሚመለከተው አካልም፣ ከዚህ አኳያ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡ ይልቁንም ከዕዝ ኢኮኖሚ ተላቃ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ በመራመድ ላይ ለምትገኘውና ሕዝቧን ከድህነት ለማላቀቅ ጥረት በማድረግ ላይ ያለችው ኢትዮጵያ፣ በጎረቤት ወደቦች የመጠቀም መብት በማንኛውም ሁኔታ የሚገሰስ መሆን ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ አንድ ሊለው ይገባል፡፡
የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ በሰላም መኖርና ወደቦችን በዓለም አቀፍ የባህር ወደብ አጠቃቀም ሕግ መሠረት መብት መረጋገጥ፣ በተለይም እ.ኤ.አ. በ1993 በጋራ የተስማሙበት ውል የሚጠቅመው ለሁለቱም አገሮች ዕድገት መሆኑ ምንጊዜም መዘንጋት የሌለበት ነው፡፡ በተለይም የዓለም አቀፍ ማሪታይምን ስምምነትን ያልፈረመችው ወይም ያልተቀበለችው ኤርትራ እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካልነቷ መገንዘብ ይኖርባታል፡፡
በመሠረቱ ወደብ ባላቸውና በሌላቸው አገሮች መልካም ግንኙነት የመመሥረት ጥቅሙን በብዙ ምሳሌዎች ማሳየት ይቻላል፡፡ አንደኛው ምሳሌ በአፍጋኒስታንና በፓኪስታን መካከል ያለው ግንኙነት ነው፡፡ በፓኪስታን ውስጥ የአፍጋኒስታን ነፃ ትራንዚት ሥፍራ ተብሎ መሰጠቱም በሁለት ጎረቤት አገሮች ሊኖር የሚገባውን መተሳሰብ የሚያመለክት ነው፡፡ በቻይናና በሞንጎሊያ፣ እንዲሁም በሩሲያ ፌዴሬሽን መካከል ያለው ግንኙነትም ነፃ የትራንዚት አገልግሎት መኖሩን ያረጋግጣል፡፡ እርግጥ ነው በሁሉም አገሮች ተመሳሳይ የሆነ አሠራር ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያና በኤርትራ ሕዝቦች ያለው የቆየ ሁለንተናዊ ትስስር ቀደም ሲል ከተጠቀሱት አገሮች በተሻለ ሁኔታ ቢገኝ እንጂ አይብስም፡፡
የበርበራ ወደብ
እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በበርበራ ወደብ ስትጠቀም ነበር፡፡ “ፐሪፕለስ ኦፍ ዘ ኤርትራን ሲ” የተሰኘው የታሪክ መረጃ እንደሚጠቅሰው ጥንታዊ አክሱማውያን በአዶሊስ ብቻ ሳይሆን በዘይላ፣ በማላካና በበርበራ ወጪና ገቢ ዕቃዎችን በማጓጓዝ ይገለገሉባቸው ነበር፡፡ አልቫሬዝ የተባለው ፖርቱጋላዊ የታሪክ ጸሐፊም ኢትዮጵያ በ15ኛው ክፍለ ዘመንና ከዚያ በፊት ተመሳሳይ አገልግሎት ታገኝ እንደነበር አሥፍሯል፡፡ ይልቁንም ሐረር በምሥራቅ ኢትዮጵያ ዋነኛዋ የገበያ ማዕከል በነበረችበት ጊዜ በዘይላና በበርበራ ወይም በአውሳ ወደብ የንግድ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ነበር፡፡
በ1808 ዓ.ም. ወደ ምሥራቅ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው ተጓዥና የታሪክ ጸሐፊው ሔንሪ ሶልት የሐረር ኢማሞች ዘይላንና በርበራን በከፍተኛ ደረጃ ይጠቀሙ እንደነበርና በዚያም በኩል ወደ ሸዋ፣ ይፋትና ወደ ቀሩት የኢትዮጵያ ግዛቶች ጭነቶች ይተላለፉ እንደነበርም አሥፍሯል፡፡ ግንኙነቱ በንግድ ብቻ ሳይወሰን በማኀበራዊ ኑሮ፣ በባህልና በእምነት ላይ የተጠናከረ ስለነበርም የምሥራቅና የደቡብ ኢትዮጵያን ሙስሊሞች ለሐጅና ለዑምራ ወደ መካና መዲና በመርከብ የሚጓዙት በዘይላና በበርበራ በኩል እንደነበር ይታወቃል፡፡ የባህር ንግዱ በሰሜንና በምሥራቅ አቅጣጫ ብቻ ሳይገደብ የደቡብና የማዕከላዊው ኢትዮጵያ የንግዱ ኀብረተሰብ ሞቃዲሾንና ሞምባሳን በመጠቀም ወደ ሩቅ ምሥራቅ አገሮች በተለይም ወደ ፋርስ፣ ህንድና ቻይና፣ እንዲሁም ወደ ደቡብ አፍሪካ አገሮች በተለይም ወደ ታንዛኒያና ዛንዚባር በመጓዝ የንግድ ልውውጥ ያደርጉ ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ከ53 ዓመታት በፊት ዘመናዊ የባህር የንግድ መስመር ከዘረጋች ወዲህ ደግሞ ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ፣ የአገሪቱን ወጪና ገቢ ዕቃዎች ከሰሜን አውሮፓ፣ ከሜዲትራንያን፣ ከአድሪያቲክና ከቀይ ባህሮች፣ ከገልፍና ከሩቅ ምሥራቅ አገሮች፣ እንዲሁም ከምሥራቅና ከደቡባዊ የአፍሪካ አገሮች በማጓጓዝ ኢኮኖሚያዊ አቅሟን በመገንባት ላይ ትገኛለች፡፡ የአንድ ወደብ መሠረታዊ አገልግሎት በዓለም አቀፍ ባህር ሕግ መሠረት ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ አገር የሚገባውን ዕቃ ለማራገፍና ለመጫን፣ እንዲሁም እስኪጫንና እስኪራገፍ ድረስ ተገቢውን ጥንቃቄ ወስዶ መጠበቅ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ዙሪያቸው ወደብ ባላቸው አገሮች የተከበቡ አገሮች ደግሞ አጭርና አፋጣኝ ወደብ በመጠቀም ረገድ አማራጭ እንደሚኖራቸው የታወቀ ነው፡፡
ዛሬ ዓለማችን በደረሰችበት በግሎባላይዜሽን ዘመን ውስጥ ሆነን ዕድሉ ካለ የንግድ እንቅስቃሴ በአንድ በተወሰነ ወደብ ብቻ መጠቀም ብልህነት ሊሆን አይችልም፡፡ አማራጮቻችን ብቃት፣ ቅልጥፍናና ታማኝነት የሰፈነባቸው መሆናቸውን ካረጋገጠ ከባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ጋር የሚገባቸው ነገሮች እንዲኖሩ ግፊትም ዕገዛም እያደረግን በጎረቤቶቻችን ወደቦች መጠቀም ካልቻልን፣ በፈጣን ዕድገት በመጓዝ ላይ በሚገኘው የምሥራቅና የምዕራብ አገሮች ኢኮኖሚ ጋር አብረን መንቀሳቀስ እንደሚቸግረን አያጠያይቅም፡፡
ስለዚህም ዓለም አቀፍ የባህር ሕጎችን አክብሮ ዕቃዎችን በማጓጓዝ መልካም ስምንና ዝናን ያተረፈው አገር በቀል ኩባንያችን የአገልግሎት አድማሱን ከዓመት ዓመት እያሰፋ በማጓጓዝ ላይ ሲሆን፣ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ የሚገለገልባቸውን ወደቦች ቁጥር በመጨመር የገበያ ሁኔታን ለመፍጠር የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ቀደም ሲል ሲጠቀምባቸው ከነበሩት የምሥራቅ አፍሪካ ወደቦች በተጨማሪ፣ በፖርት ሱዳን ወደብ ለሰሜንና ለሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ በጂቡቲና በበርበራ ወደቦች ለምሥራቅ፣ የሞምባሳን ወደቦች በመጠቀም የደቡብና የማዕከላዊ ኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚቻልበት ሁኔታ ሲመረምር ቆይቷል፡፡
የሞምባሳ ወደብ የመጠቀሙ የቅርብ ጊዜ ዕቅድ ሆኖ በአሁኑ ጊዜ ከአዲስ አበባ 937 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የበርበራ ወደብ ለመጠቀም አስፈላጊዎቹ ቅድመ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡ የበርበራ ወደብ ከአዲስ አበባ ሐረር 535 ኪሎ ሜትር፣ ሐረር በጅጅጋ እስከ ቶጎ ውጫሌ 16ዐ ኪሎ ሜትር፣ ከቶጎ ውጫሌ በርበራ አስፋልት መንገድ በመሆኑ ዕቃን ከአገር ለማስወጣትና ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት አመቺ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከጂቡቲ ይልቅ በርበራ ለባህረ ሰላጤውና ለሩቅ ምሥራቅ አገሮች የቀረበች ናት፡፡ ለመሀል አገር ደግሞ ከጂቡቲ የምትርቀው በሃያና በሰላሳ ኪሎ ሜትሮች ብቻ ሲሆን ከወደብ ክፍያም አንፃር የተሻለ ሁኔታ አለ፡፡
ስለሆነም መንግሥታዊ አካላት በተደጋጋሚ በመገናኘት እንዴት የበርበራ ወደብን መጠቀም እንደሚቻል፣ የበርበራ ወደብ የባህር ጥልቀት፣ ስለሚያስተናግዳቸው መርከቦች የዕቃ ማውረጃ ክሬኖች አቅምና የዕቃ ማቆያ መጋዘኖች፣ ስለነዳጅ፣ ኤሌክትሪክና ሌሎች ጉዳዮች ውይይት ተካሂዷል፡፡ በዚህ ረገድ ሌሎች የሚመለከታቸው ጉዳዮች ላይ በመንቀሳቀስ ላይ ሲሆኑ በተለይም በኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ በኩል በበርበራ ወደብና በሐርጌሳ ጠለቅ ያለ የባለሙያዎች ጥናት የተደረገ ሲሆን፣ በጥናቱም የሶማሌላንድ ባለሙያዎች የበኩላቸውን አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ በዚህም መሠረት ለጋራ ልማት የሚጠቅም ውል ተፈርሟል፡፡ ይህም ማለት የሶማሊያን የግዛት አንድነት የሚነካ አለመሆኑንና ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ ዕውቅና ካልሰጡት አገሮች መካከል አንዷ ከመሆኗም በላይ፣ በሶማሊያ ሰላም እንዲሰፍን የበኩሏን ጥረት የምታደርግ መሆኗን በተደጋጋሚ ይፋ አድርጋለች፡፡
በተደረገው ጥናት፣ ውይይትና ድርድር የሁለቱን ሕዝቦች ጥቅም የሚያስጠብቅ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ሲሆኑ፣ ከእነዚህም መካከል የቢል ኦፍ ላዲንግና የቀጥታ ዕቃ የመርከብ ሥርዓት (Through Bill of Lading and Direct Delivery System) ተግባራዊ ማድረግ ይገኝበታል፡፡ በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች እንደገለጽነው ሁሉ ድርጅቱ በፈጣን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እየታገዘ የአገር ድንበር ሳያግደው ንግድ፣ ካፒታልንና ሕዝብን አቀናጅቶ የሚጓዘውን ግሎባላይዜሽንን መሠረት አድርጎ በርበራ ወደብን እንደ ተጨማሪ አማራጭ መጠቀሙ ለነገ የሚባል ሊሆን አይችልም፡፡
ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ከሶማሌላንድ ሕዝብ ጋር በታሪክ የተሳሰረና የተዋሀደ ግንኙነት እንዳለን የታወቀ ሲሆን፣ ጸሐፊው በወደቡ ለመጠቀም መጀመራችን የሁለቱን ሕዝቦች ወዳጅነትና አንድነት የበለጠ ለማጠናከር ይረዳል የሚል እምነት አለው፡፡
መደምደሚያ
ብዙዎቻችን እስካሁን ድረስ ስለቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካ ጉዳይ ሳናውቅ ቆይተናል፡፡ በመሠረቱ የባህር ጂኦ ፖለቲካ ጉዳይ በቀይ ባህር ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በክፍል አንድ እንደተጠቀሰው ሁሉ በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም ከሚስተጋቡት ቃላት አንዱ ‹‹ጂኦ ፖለቲካ›› መሠረታዊ ወይም ዕሳቤያዊ ሐረግ ነው፡፡ ‹‹ጂኦ ፖለቲካ›› አንድ የተወሰነ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ያለው አካባቢ በሚገኝበት ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለውና የአካባቢው፣ የአውሮፓ፣ የእስያና የአሜሪካ አገሮች በባህር መስመሩ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ኃይላቸውን የሚያሠልፉበት፣ አንዱ የሌላው ሥጋት በመሆኑ በዓይነ ቁራኛ የሚተያይበት፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የጦር መሣሪያ የሚማዘዝበት፣ እንዲሁም የፖለቲካዊ ውዝግብ ዓውድማ ሊባል የሚችል ነው፡፡
በሜዲትራንያን፣ በቀይ ባህርና በህንድ ውቅያኖስ አካባቢ የሚገኙ የንግድ መስመሮች ወደ ሀብት ምንጭ አገሮች ስለሚወስዱ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የዓለምን ትኩረት እንደሳቡ ነው፡፡ በዓለም ላይ በርካታ በከፍተኛ የወታደር ኃይል የሚጠበቁና እንደ ዓይን ብሌን የሚታዩ የባህር በሮች ሲገኙ ዓላማቸውም የንግድ፣ የሰውና የጦር መሣሪያ መርከብ መተላለፊያ መስመር ሆኖ ማገልገል ነው፡፡ ከሚታወቁት የንግድ መስመሮች መካከል ውስጥ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡
ጂብራተር መተላለፊያ አትላንቲክ ውቅይኖስንና ሜዲትራኒያን ባህርን ያገናኛል፣ ሆርሙዝ ‹‹HORMUZ›› የባህር መተላለፊያ መስመር ፐርሺያ ባህረ ሰላጤንና ኦማን ባህረ ሰላጤን የሚያገናኝ ሲሆን ሆርሙዝ በዓለም ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ካላቸው የባህር መስመሮች ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ባብኤል መንደብ ‹‹BAB-EL-MANDAB›› ቀይ ባህርንና የኤደን ባህረ ሰላጤን፣ እንዲሁም አፍሪካንና እስያን የሚያገናኝ ዋና መስመር ስለሆነ የሚጠበቀው በከፍተኛ ዓይነ ቁራኛ ነው፡፡ በእነዚህ የባህር መስመሮች አካባቢ የሚገኙ አገሮች ሁሉ ራሳቸውን ለመከላከል ካልቻሉ አደጋ ላይ ናቸው፡፡ ይልቁንም ኢትዮጵያ ከወደቦች በቅርብ ርቀት የምትገኝ አገር ከመሆኗም በላይ ታላቅ አገር በመሆኗ ኃይላንና ባለሀብት አገሮች ሁሉ የሚመለከቷት እጅግ በጥንቃቄ ነው፡፡ ለአንዳንዶቹም በጣም ከፍተኛ ሥጋት ናት፡፡
በሌላ አነጋገር በጀዳና፣ ያንቡና ሁደይዳ (ሳዑዲ ዓረቢያ)፣ ሳጋፋ (ግብፅ)፣ ኤየላት (እስራኤል)፣ ፖርት ሱዳን፣ ጂቡቲ፣ ምፅዋና አሰብ፣ ኤደን ወደቦች እሳት ቢነድ ኢትዮጵያ መለብለቧ እንደማይቀር ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ በመጨረሻም ይህን መሠረታዊ እውነታ ጨብጠን የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካ ሲባል በቀላሉ የምንመለከተው አለመሆኑን በመጠቆም፣ በተለይ የፖለቲካ መሪዎች በዚህ መስክ ያላቸውን ግንዛቤ ማስፋት የሚገባቸው መሆኑንና ጋዜጠኞችም፣ አክቲቪስቶችም፣ የኪነ ጥበብ ሰዎችም አውቀው ማሳወቅ እንደሚጠበቅባቸው ጸሐፊው ለማስታወስ ይወዳል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡
