የደልታ አየር መንገድ አውሮፕላኖች

ከ 4 ሰአት በፊት

የደልታ አየር መንገድ አብራሪ የሆነው ግለሰብ ባለፈው ዓመት በራረ ላይ ሳለ ካፕቴኑን በሽጉጥ ለመምታት ዝቷል የሚል ክስ ቀርቦበታል።

ጆናታን ዲ ደን ባለፈው የአውሮፓውያኑ ወር ነው በዩታህ ግዛት የመንገደኞች አውሮፕላን ሠራተኞችን በማወክ የተከሰሰው።

ካፕቴኑ ከመንገደኞች መካከል አንድ ሰው ጤናው በመታወኩ በረራውን ለመቀየስ ሲሞክር ነው ጆናታን ዛቻ የሰነዘረው።

ሰውየው በያዝነው ወር ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሏል።

የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ማክሰኞ ዕለት የፍርድ ቤት ወረቀት ተመልክቶ በሠራው ዘገባ ጆናታን፤ “የበረራ ሠራተኛ አስፈራርቷል እንዲሁም ዛቻ ፈፅሟል፤ አልፎም አደገኛ መሣሮያ ተጠቅሞ ማስፈራራት አድርሷል” ብሏል።

ክስተቱ ተፈፅሞበታል የተባለው በረራ በአውሮፓውያኑ ነሐሴ 2022 የሆነ ነው።

የበረራው ካፕቴን አውሮፕላኑን በደንገተኛ አደጋ ምክንያት ካሳረፈው ተኩሶ እንደሚገድለው “በተደጋጋሚ ዝቷል” ይላል የትራንስፖርት ሚኒስቴር የለቀቀው መግለጫ።

የትራንስፖርት ሚኒስቴር ጠቅላይ ምርመራ ቢሮ ክስተቱን እየመረመረ እንደሆነ ገልጧል።

ምርመራውን ኤፍቢአይ እና የፌዴራል አቪየሽን አስተዳደር በትብብር እያሳለጡት ይገኛሉ።

ባለሥልጣናት ስለተፈጠረው ጉዳይ ከዚህ የበለጠ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጠብዋል።

የደልታ አየር መንገድ ቃል አቀባይ ለሲቢኤስ እንዳረጋገጡት ክስተቱ በተፈጠረ ወቅት ጆናታን የተባለው ግሰለብ አንደኛ መኮንን ሆኖ ሲያገለግል ነበር።

ቃል አቀባዩ አክለው ተጠርጣሪው አሁን ለአየር መንገዱ እየሠራ እንዳልሆነ አረጋግጠዋል።

ጆናታን የሃገር ውስጥ ደኅንነት ቢሮ ከሆነው የትራንስፖርት ደኅንነት አስተዳደር የጦር መሣሪያ እንዲይዝ ፈቃድ ተሰጥቶታል።

የፌዴራል ፍላይት ዴክ ኦፊስ ፕሮግራም በተሰኘው ሕግ መሠረት ብቃት ያላቸው አብራሪዎች ግጭት በሚነሳበት ወቅት የሕግ አስከባሪ ሆነው የማገልገል ሥልጣን አላቸው።

የትራንስፖርት ደኅንነት አስተዳደር እንዳለው ተጠርጣሪው ከዚህ ፕሮግራም እንዲሰረዝ ተደርጓል።

የበረራ ሠራተኞችን ማወክ እስከ 20 ዓመት እሥራት ድረስ የሚያስቀጣ ወንጀል ነው።