
ከ 5 ሰአት በፊት
ኻሊል ጎልማሳ አባት ነው። ከቢቢሲ ዘጋቢ ጋር ወደ ፍርስራሽነት የተቀየረው ቤቱን ሊያሳይ ሄደ።
ከፍርስራሹ ክምር ላይ እየወጣ የእሱ የመኖር ስሜት ግን እየወረደ ነበር።
እርሱ ወደ ሥራ ሲሄድ ከልጆቹ አንዷ የምትለብሰውን የልብስ ብጣቂ ከፍርስራሹ ክምር ውስጥ ተመለከተ።
የትንሿ ልጁ ፒጃማ ነበረች። ከፍርስራሹ ስር ጎትቶ አወጣት። ልጁ በዐይነ ሕሊናው መጣችበት። ትንሿ ልጁ። ገና 18 ወር ያልሞላት ልጁ። ጢኒጧ ሮዛ። የእሷ ልብስ ነው ይሄ።
አውቆታል። ለይቶታል።
ስልኩን አውጥቶ ለቢቢሲ ጋዜጠኛ ሮዛን ማሳየት ጀመረ። ትክክል ነው። ያንን ሰማያዊ ፒጃማ ነበር ሮዛ የለበሰችው። በስልኩ ላይ ባለው ተንቀሳቃሽ ምሥል ላይ እንደሚታየው ያንን ፒጃማ ለብሳዋለች።
ሁለት የአክስቶቿን ልጆች እጅ ይዛ ትቦርቃለች። ሦስቱም ክብ ሠርተው ይደንሳሉ። በስልኩ ላይ ያለው ቪዲዮ ያንን ነው የሚያሳየው።
ይስቃሉ። አሁን ግን ከፍርስራሹ ሥር ናት። ጦርነቱ በልቷታል።
የሮዛ አባት ኻሊል ካድር 36 ዓመቱ ነው። የኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ ባለሙያ ነው። በራፋህ አል ናጃር ሆስፒታል ነው የሚሠራው። አራት ልጆች አሉት። ትልቁ ልጁ ኢብራሂም 9፣ አማል 5፣ ኪናን 2 ተኩል እና ሮዛ 18 ወሯ ነበሩ።
ኻሊል ከፍርስራሹ ላይ በጥንቃቄ ይራመዳል። አልሞቱ ይመስል። እንዳይረግጣቸው የፈራ ይመስል። ቤቱ ከሚሠራበት ሆስፒታል በቅርብ ርቀት ነው ያለው።
እየተራመደ የሚያየው የልጆችን መጫወቻ ነው። ከፍርስራሽ ውስጥ ፒያኖ፣ አሻንጉሊቶች ብጣቂ ልብሶች እዚም እዚያም ወዳድቀው ይታያሉ።
ከሳምንት በፊት አንድ ምሽት ቤቱ ላይ ሚሳኤል ሲወድቅ እሱ ሥራ ቦታ ነበር። ሆስፒታል ነው የሚሠራው። በአቅራቢያው ከባድ ሲፈነዳ ሰምቷል። ነገር ግን የእርሱን ቤት ያቀደመ፣ ቤተሰቡን የነጠቀው መዓት ይሆናል ብሎ በጭራሽ አላሰበም።
- እስራኤል ሐማስን ማስወገድ ከቻለች በጋዛ ላይ ምን የያዘችው ዕቅድ አለ?30 ጥቅምት 2023
- ከሐማስ እና ከሒዝቦላህ ማን ጠንካራ ጦር አለው? አሜሪካ እና ኢራንስ ወደ ግጭቱ ይገቡ ይሆን?23 ጥቅምት 2023
- ሊባኖስ የሚገኘው የእስራኤል ጠላት ሄዝቦላህ ማን ነው? እንዴትስ ተመሠረተ?19 ጥቅምት 2023

ይልቅ ሆስፒታል ተጎድተው የመጡ ጎረቤቶቹን በአጋጣሚ ያገኝና “ፍንዳታው የቱ ጋ ነው በትክክል የደረሰው?” ብሎ ይጠይቃቸዋል።
ነገሩት። ከእርሱ ቤት አጠገብ መሆኑን አረዱት። እየበረረ ወደ ቤት ሄደ። እየሮጠም ስልክ መደወል አላቆመም። ቢቀጠቅጥ ቢቀጠቅጥ የሚያነሳለት የለም።
“እንደምታየው ወደ ፍርስራሽነት ነው የተቀየረው” ሲል ለቢቢሲ ዘጋቢ ቤቱን አስጎበኘ።
እንዳለመታደል ሆኖ በዚያ ጥቃት 11 የቤተሰቡ አባላት በሙሉ ነው ያለቁት።
አራቱ ልጆቹ፣ ሁለቱ እህቶቹ፣ የ70 ዓመት አባቱ፣ አንድ ወንድሙ እና የባለቤቱ እህት እንዲሁም የባለቤቱ እህት ሁለት ልጆች፤ በድምሩ 11 ሰው በአንድ ጥቃት ተገደለበት።
ባለቤቱ ለጊዜው አልሞተችም። በተአምር ተርፋ ከፍተኛ የመቁሰል አደጋ ደርሶባት ሕክምና ላይ ናት።
ኻሊል ጦርነትን የሚያውቀው አሁን አይደለም። በዚህ ግጭት በማያጣው ጦርነት ቀጠና ልጆችን ማሳደግ ልክ ነው ወይ? ብሎ ራሱን ጠይቆም ያውቃል።
“አስታውሳለሁ (እአአ) በ2014ቱ ጦርነት ጊዜ ባለቤቴ ነፍሰ ጡር ነበረች” ሲል በትካዜ ያስታውሳል። “እና ጎረቤቶቻችን ቤት ላይ ፍንዳታ ደረሰ። ባለቤቴ 7ኛ ወሯ ነበር። በጥቃቱ ከደረጃ ተፈጥፍጣ ከመሞት በተአምር ነበር የተረፈችው። ያን ቀን ‘ምን ነክቶኝ ነው ግን ወደዚህ ምድር የሰው ፍጡር የማመጣው?’ ስል ራሴን ጠይቄ ነበር” ይላል።
ከዚያ ግን በጨለምተኛ ሐሳቡ ተጸጸተ። ወደፊት ማን ያውቃል? የተሻለ ዓለም ይኖር ይሆናል ሲል ተስፋ አደረገ።
“ስለሁሉም ልጆቼ የወደፊት ተስፋ ሕልም አልም ነበር። ኢብራሒም ሲያድግ ዶክተር ይሆናል፣ አማል ምንም ጥያቄ የለውም ሠዓሊ ነው የምትሆነው ምክንያቱም ሥዕሎቿን ሁልጊዜ ታሳየኛለች፤ አብረን ሁሉ ሥዕል እንስላለን።
“ኪናን ተጫዋች ነው ሁሉም ቤተሰብ ይወደዋል። ትንሽ እህቱን በጣም ነው የሚንከባከባት። በተለይ ሮዛን በጣም ይንከባከባታል። እሷን ማንም እንዳይነካበት-‘ሮዛ የኔ ልጅ ናት’ ይለን ነበር።”
ነበር እንዲህ ቅርብ ሆኖ – ሁሉም አሁን የሉም።
ኻሊል አሁንም ከፍርስራሹ ሥር ሰው ይፈልጋል። አንድ እህቱ ጠፍታለች። ደግሞም ሆስፒታል ባለቤቱን ማስታመም አለበት። ልጆቹ ግን ላይመለሱ ሄደዋል። አሁንም ከፍርስራሹ ሰው ይፈልጋል።