ወ/ሮ ኩሊ
የምስሉ መግለጫ,ወ/ሮ ኩሊ ሃዋስ

2 ህዳር 2023, 16:15 EAT

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ቦረሰት ወረዳ ውስጥ የሰባት ልጆች እናትን ጨምሮ ሦስት ሰዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን እና አንድ ተጨማሪ ሰው እንደቆሰሉ ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ።

በቦሰት ወረዳ ገሪ ቀበሌ ነዋሪ ዕድሜያቸው በግምት ከ50 ዓመት በላይ የሚሆኑት ኩሊ ሃዋስ እና ሌሎች ሁለት ሰዎች የተገደሉት ባለፍነው ሰኞ ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም. መሆኑን አንድ የቤተሰብ አባል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለደኅንነታቸው ሲባል ስሜ አይጠቀስ ያሉት የወ/ሮ ኩሊ ሃዋስ ቤተሰብ፣ ሦስቱ ሰዎች የተገደሉት ልጆቻቸው በመንግሥት በአሸባሪነት የተፈረጀው የታጣቂ ቡድን አባል ናቸው የሚል ክስ ከቀረበባቸው በኋላ መሆኑን ይገልጻሉ።

የወ/ሮ ኩሊ እና የሦስቱ ሰዎች ልጆች መንግሥት ‘ሸኔ’ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባል ናቸው በሚል ጥቅምት 14/2016 ዓ.ም. የአገር መከላከያ ሠራዊት በቁጥጥር ሥር ካዋላቸው በኋላ ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም. ምሽት ላይ በአንድ ቦታ በጥይት ከተመቱ በኋላ ሦስቱ ሕይወታቸው ሲያልፍ አንዱ በሕይወት መትረፉን የቤተሰብ አባሉ ጨምረው ተናግረዋል።

ከወ/ሮ ኩሊ ጋር በአንድ ቦታ ሰኞ ከምሽቱ 2 ሰዓት አካባቢ በጥይት የተመቱት ሦስቱ ሰዎች ወንዶች መሆናቸውን የገለጺ ሲሆን ሕይወታቸው ያለፈው ገዳ ጎዳና እና በቀለ ቦሩ ሲሆኑ ቱፋ ኢደኦ ደግሞ በሕይወት ቢተርፉም በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት በሆስፒታል እንደሚገኙ ቢቢሲ ከሟቾቹ ቤተሰብ ካገኘው መረጃ ለማወቅ ችሏል።

“ከሰሞኑ በመከላከያ እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች መካከል ገሪ አካባቢ ውጊያ ነበር። ከዚያ በኋላም ጥቅምት 14 ላይ ወ/ሮ ኩሊ እና ሌሎቹ ሰዎች በመከላከያ አባላት ተይዘው ተወሰዱ” በማለት የወ/ሮ ገሪ ቤተሰብ ተናግረዋል።

እንደ የቤተሰብ አባሉ ከሆነ ጥቅምት 14/2016 ዓ.ም. ላይ ከወ/ሮ ኩሊ ጋር ከገሪ ከተማ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ስድስት ነበር።

ከስድስቱ ሰዎች መካከል ሳሮ ጎባ የሚባሉት ከእነባለቤታቸው ሲለቀቁ የተቀሩት አራቱ ቢርካ በሚባል ቦታ ሦስቱ ተገድለው፤ አንዱ ደግሞ ቆስሎ መገኘታቸውን ገልጿል።

የገሪ ቀበሌ ነዋሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት “ልጆቻችሁን [ታታቂዎችን] እየቀለባችሁ የምታስገድሉን እናንተ ናችሁ” ተብለው መሆኑን የቤተሰብ አባሉ የገለጹ ሲሆን፣ “የመከላከያ አባላት ‘ልጅሽ ነው የሚገድለን። እንቺ ነሽ ቀልበሽ የምታስገድይን’ ብለው ወ/ሮ ኩሊን ይዘዋት ሄዱ” ብለዋል።

የወረዳው ፖሊስ ግን ስለሰዎቹ ግድያ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ የቦሰት ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ሞሐመድ ሱፋ “ይህ ክስተት ለእኛም አዲስ ነው” በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ከዚህ ቀደም በአገር መከላከያ የሚያዙ ሰዎችን እኛ እንደ ፖሊስ ተቀብለን ሕጋዊ አካሄዱን እናስቀጥላለን። ስለሰሞኑ ግድያ ግን መረጃው የለኝም። ወደኛም አልመጡም” ብለዋል።

“ተገድለዋል የተባሉት ሰዎች እኛ ጋር አልታሰሩም፤ አላየናቸውምም። ስለመገደላቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየሄደ ያለውን አይተናል። ግድያው በሌላ አካል ተፈጽሞ ከሆነ የምናቀው ነገር የለም” ሲሉ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል።

የፖሊስ አዛዡ አካባቢያቸው የታጣቂዎች እንቅስቃሴ የሚካሄድበት እና የተለያዩ ዘረፋዎች የሚፈጸሙበት በመሆኑ የተለያዩ የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች መሰማራቸውን አስታውሰው ይህ ግድያ በማን እንደተፈጸመ ወደፊት ካልተጣራ በቀር አሁን ላይ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

አራቱም የገሪ ቀበሌ ነዋሪዎች አርሶ አደር እንደነበሩ እና የተገደሉት ተይዘው ከነበሩበት የአገር መካላከያ ሠራዊት ካምፕ እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ መሆኑን የሚናገሩት የቤተሰብ አባሎቻቸው፣ አስክሬናቸው ማክሰኞች ዕለት ተነስቶ በተመሳሳይ ቀን በኦለንጪቲ ከተማ ሥርዓተ ቀብራቸው መፈጸሙን ተናግረዋል።

ወ/ሮ ኩሊ የአምስት ሴቶች እና የሁለት ወንዶች እናት የነበሩ ሲሆን፣ ከእርሳቸው ጋር አብረው መገደላቸው የተነገረው አርሶ አደሮች እና የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ነበሩ።

የሦስቱ የገሪ ቀበሌ ነዋሪዎች ግድያ በመኖሪያ አካባቢያቸው ከፍተኛ ድንጋጤን መፍጠሩን እና የግድያው ዜና ከተሰማ በኋላ መኖሪያቸውን ለቀው የሸሹ ነዋሪዎች ስለመኖራቸው ቢቢሲ ያናገራቸው የሟች ቤተሰብ ገልጸዋል።

የሰዎቹን ግድያ በተመለከተ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና የአገር መከላከያ ሠራዊትን አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።