
2 ህዳር 2023, 18:17 EAT
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰሞኑ በአማራ ክልል ካለው ግጭት ጋር ተያይዞ ያለውን የሰብአዊ መብት ሁኔታ በተመለከተ ያወጣው ሪፖርት “አስተማማኝ በሆነ መረጃ ላይ ያተመሠረት እና ሚዛናዊነት የጎደለው ነው” ሲል መንግሥት አጣጣለው።
ኢሰመኮ ሰኞ ጥቅምት 19/ 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል በቀጠለው የትጥቅ ግጭት ምክንያት ግድያ እና መድፈርን ጨምሮ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን ይፋ አድርጎ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት የኮሚሽኑን መግለጫ ያጣጣለው ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 22/ 2016 ዓ.ም. በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ በኩል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
መግለጫውን የሰጡት ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ የኢሰመኮ “መግለጫ አስተማማኝ በሆነ መረጃ ላይ ያልተመሠረተ እና ሚዛናዊነት የጎደለው ነው” በማለት፣ ይህንኑ ለማስተካከል ኮሚሽኑ “እርምት” ይወስዳል ብሎ መንግሥት እንደሚጠብቅ ተናግረዋል።
ነገር ግን ኮሚሽኑ በዚሁ መግለጫው ሪፖርቱን ለማዘጋጀት መንግሥታዊ ኃላፊዎችን፣ በግጭቱ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን፣ የዐይን ምስክሮችን፣ ተጎጂዎችን እና የተጎጂዎች ቤተሰቦችን በማነጋገር መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን አመልክቷል።
አክሎም በመንግሥት የፀጥታ ኃይል አባላት የሚፈጸሙ ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች ስለመቀጠላቸው “ተዓማኒ መረጃዎችን እየተቀበለ” መሆኑን ይፋ አድርጓል።
ኮሚሽኑ ይህን ቢልም ዶ/ር ለገሰ በበኩላቸው መንግሥት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማዕቀፍ ስር “ዜጎች ወደ መደበኛ ኑሯቸው መመልስ እንዲችሉ” እና “መሠረታዊ መብታቸው በተሻለ ሁኔታ እንዲጠበቅ” የሕግ ማስከበር ሥራ መሠራቱን አብራርተዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም “በቅርቡ [የኢትዮጵያ] የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያወጣው መግለጫ ይህንን አውድ እና እውነታ ከግምት ያስገባ አይደለም” ሲሉ ወቅሰዋል።
“የኮሚሽኑ መግለጫ ገንቢ እና የሰብአዊ መብት ሁኔታን ለማሻሻል አዎንታዊ ሚና የሚኖረው አይደለም” ያሉት ዶ/ር ለገሰ “ስለሆነም ኮሚሽኑ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ተገቢውን እርምት እንደሚወስድ ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።
- በምሥራቅ ሸዋ የሰባት ልጆች እናትን ጨምሮ አራት ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች ተገደሉ2 ህዳር 2023
- በአማራ እና በኦሮሚያ የሚካሄዱት ግጭቶች እንዳሳሰቧቸው ምዕራባውያን አገራት ገለጹ2 ህዳር 2023
- በአማራ ክልል ግድያ እና መድፈርን ጨምሮ መጠነ ሰፊ የመብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል፡ ኢሰመኮ30 ጥቅምት 2023
ኢትዮጵያ ነጻ እና ገለልተኛ ተቋማትን እየገነባች መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ለገሰ ለዚህ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋሙን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በምሳሌነት አንስተዋል።
“ይህ ተቋም አሁንም ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ እንዲሰራ መንግሥት አበክሮ ተግቶ ይሠራል” ያሉት ሚኒስትሩ፤ “ነገር ግን ነጻ እና ገለልተኛ መሆን ማለት ከመንግሥት ብቻ አይደለም፤ ከባዕዳን አካላት ጭምርም ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ዶ/ር ለገሰ አክለውም “ነጻነት የሚባለው ከአስፈጻሚ አካል ብቻ ሳይሆን ከባዕዳንም፣ ከውስጥ ሰርጎ ገቦችም፣ ከተለያዩ ወገኖችም ጭምር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል” ሲሉ አጽንኦተ ሰጥተዋል።
የኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫቸው “እነዚህ[ን] ተቋማት መንግሥት ነጻ ነው ብሎ ቢያደራጅም የሚያቀርቡት ሪፖርት ሁሉ ነጻ እና ትክክለኛ ነው ብሎ መውሰድ አይገባም” ሲሉ ተደምጠዋል።
ኢሰመኮ ባለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ፤ በአማራ ክልል በሁሉም ዞኖች ውስጥ በተለያየ ደረጃ እና ጊዜ የትጥቅ ግጭት መካሄዱን አመልክቶ፣ “የትጥቅ ግጭቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በከባድ መሣሪያ እና አልፎ አልፎ በአየር/ድሮን ድብደባ ጭምር የታገዘ ነው” ነው ሲል ገልጿል።
በዚህም ሳቢያ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ጨቅላ ሕጻንን ጨምሮ በርካታ ሲቪል ሰዎች እንደተገደሉ እና የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የመደፈር ጥቃት እንደተፈጸባቸው አመልክቷል። የዐይን እማኞችን ዋቢ አድርጎ ቦታዎችን እና ቀናትን በመጥቀስ በሪፖርቱ ውስጥ አካቷል።
ኢሰመኮ ባወጣው ባለ አራት ገጽ መግለጫ ከመንግሥት ኃይሎች ባሻገር የመብት ጥሰቶች በታጣቂዎችም ጭምር መፈጸማቸውንም መጠቆሙ ይታወሳል።
በኮሚሽኑ “በየደረጃው የሚገኙ ሲቪል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች፣ ግድያዎች እና እገታዎች በታጠቁ ኃይሎች ተፈጽመዋል” ሲል በመግለጫው አስፍሯል።
ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ የፌደራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎችን በማፍረስ መልሶ ለማደራጀት እንዲሁም ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በአማራ ክልል ተቃውሞ እንደገጠመው ይታወሳል።
በዚህም ምክንያት በክልሉ ውስጥ ያሉ ታጣቂዎች ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር ተደጋጋሚ ግጭት አካሂደው በርካታ ትላልቅ ከተሞችን መቆጣጠር ችለው ነበር።
ሁኔታው ከክልሉ አቅም በላይ በመሆኑ የክልሉ መስተዳደር የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ጠይቆ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ የፌደራሉ መንግሥት ኃይሎች በክልሉ ውስጥ ተሰማርተው ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ለወራት የዘለቀ ግጭት እየተካሄደ ነው።
በዚህም ሳቢያ በበርካታ የአማራ ክልል አካባቢዎች ያለው መደበኛ እንቅስቃሴ ከተስተጓጎለ ወራት እንደተቆጠሩ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ባለፈው ሳምንት ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።