ታጣቂዎች

2 ህዳር 2023, 13:34 EAT

ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ እና ሌሎች አገራት በአማራ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ የቀጠሉት ግጭቶች እንዳሳሰቧቸው እና እንዲቆሙ ጥሪ አቀረቡ።

አስር አገራት አንድ ዓመት የሆነውን በትግራይ ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን የእርስ በርስ ጦርነት ያስቆመውን ስምምነት አንደኛ ዓመት በማስመልከት ባወጡት መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት በሁለቱ ክልሎች ውስጥ የሚካሄደው ግጭት “የሚረብሽ” ነው ብለውታል።

ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 22/2016 ዓ.ም. አገራቱ በጋራ ባወጡት መግለጫ ከአንድ ዓመት በፊት በፌደራሉ መንግሥት እና በህወሓት መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት ደም መፋሰሱ መቆሙ እና በትግራይ መደበኛ ሕይወት እየተመለሰ ለመሆኑ እየታየ ያለው ውጤትን አድንቀዋል።

ነገር ግን ከኢትዮጵያ ክልሎች ትላልቆቹ በሆኑት እና ሁለት ሦስተኛው የአገሪቱ ሕዝብ በሚገኝባቸው በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ የቀጠለው ግጭት “በሚረብሽ ሁኔታ ላይ” እንዳለ አገራቱ በመግለጫቸው ላይ ኣመልክተዋል።

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው መንግሥት በሽብርተኛ ቡድንነት ፈርጆ ‘ሸኔ’ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ባለፉት ዓመታት ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ሲዋጋ እና ጥቃቶችን ሲፈጽም መቆየቱ ይታወቃል።

በተለይ በምዕራብ የኦሮሚያ አካባቢዎች በስፋት የሚንቀሳቀሰው ይህ ቡድን በአካባቢው ሰፊ ተጽእኖ የፈጠረ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ከአካባቢው ለመፈናቀል ተገደዋል።

ባለፉት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች ባጋጠሙ ግጭቶች እና በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው የተዘገበ ሲሆን፣ መንግሥት ጥቃቶቹን የፈጸመው የኦሮሞ ነጻናት ሠራዊት ታጣቂዎች እንደሆኑ ሲከስ ቡድኑ ግን ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት እንደማይፈጽም ሲያስተባብል ቆይቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ መንግሥት በአማራ ክልል ያሉ ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት በወሰደው እርምጃ እና የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደረጃት ባሳለፈው ውሳኔ ምክንያት ካለፈው ዓመት አጋማሽ ወዲህ በአማራ ክልል ውስጥ ከባድ ግጭቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ።

መንግሥት በአማራ ክልል ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጎ ሠራዊቱን በማሰማራት ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ግጭት ውስጥ ከገባ አራት ወራት ሊሞላው የተቃረበ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያን ጨምሮ ሰፊ የመብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በዚህ ሳምንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በሁለቱ ክልሉች ውስጥ እየተባባሰ ባለው ግጭት ምክንያት በበርካታ አካባቢዎች መደበኛ ሕይወት የተስተጓጎለ ሲሆን፣ በሰዎች ላይ ከደረሰው ጉዳት ባሻገር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው ለመፈናቀል ተዳርገዋል።

ደም አፋሳሹ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በሰላም ስምምነት ካበቃ በኋላ በሁለቱ ክልሎች ውስጥ እየተካሄደ ያለው ግጭት ያሳሰባቸው ምዕራባውያን አገራት ባወጡት መግለጫ ላይ፣ የግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ እንዲያደርጉ እና ልዩነቶቻቸውን አካታች በሆነ ውይይት እንዲፈቱም ጠይቀዋል።

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. ተቀስቅሶ ለሁለት ኣመት የቆየው እና በአፍሪካ ደም አፋሳሽ ከተባሉ ግጭቶች መካከል አንዱ በሆነው የእርስ በርስ ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው ይነገራል።

ባለፈው ዓመት ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ በትግራይ ክልል ይካሄድ የነበረው ጦርነት ቢቆምም፣ በአማራ እና በኤርትራ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ካሉ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ወደ ቀያቸው አለመመለሳቸውን የክልሉ አስተዳደር ገልጿል።

ምንም እንኳን የኤርትራ ሠራዊት እና የአማራ ክልል ኃይሎች በጦርነቱ ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ጎን ቆመው የተዋጉት ቢሆንም በስምምነቱ ውስጥ ተሳታፊ አልነበሩም።

በፌደራሉ ሠራዊት እና በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት አሁንም የቀጠለ ሲሆን፣ በኦሮሚያ ክልል ውስጥም በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ባለፉት ሳምንታት ግጭቶች እየተካሄዱ መሆናቸው ተዘግቧል።