November 2, 2023 

“ፖሊስ ለፍርድ ቤቶች ዉሳኔ ተገዢ አለመሆኑን አሳይቷል” ጎጎት ፓርቲ

ሐሙስ ጥቅምት 22 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትህ ፓርቲ የአለም ዓቀፍ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ የሆኑት መላኩ ሳህሌ ፍርድ ቤት በአምስት ሺሕ ብር ዋስትና እንዲወጡ ቢፈቅድም ፖሊስ የተሰጠውን ውሳኔ አሻፈረኝ በማለት ለፍርድ ቤቶች ውሳኔ ተገዢ አለመሆኑ አሳይቷል ሲል ፓርቲው ገለጸ፡፡

“ይህም ፖሊስ በሦስት የተለያዩ ፍርድ ቤቶች የተሰጠውን ውሳኔ አሻፈረኝ በማለት ለፍርድ ቤቶች ውሳኔ ተገዢ አለመሆኑ በአደባባይ ያሳየበት አሳፋሪ ክስተት ነው” ሲል ፓርቲው ጉዳዩን አስመልክቶ ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ጥቅምት 16/2016 አዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ጉለሌ ምድብ ችሎት የቀረቡት መላኩ ላይ ፖሊስ “ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር እና ከጠላት ጋር በማበር” የሚል ክስ ያቀረበባቸው ሲሆን፤ ችሎቱ በ5 ሺሕ ብር ዋስትና ከእሰር እንዲለቀቁ ትዕዛዝ መስጠቱ ተገልጿል።

ሆኖም ያለምንም ተጨባጭ ማስረጃ አመራሩን ያሰረው ፖሊስ፤ በዚያው ዕለት መላኩን ወደ አዲስ አበባ ከተማ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በመውሰድ ይግባኝ መጠየቁን ፓርቲው አመላክቷል።

በድጋሚ “የአዲስ አበባ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የታችኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ በማፅናት በዋስ እንዲወጡ ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ የዋስትና ብር ተከፍሎ ከፖሊስ ጣቢያ ይወጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም፤ ፖሊስ ምክንያቱ ባልታወቀ ኹኔታ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን አዛውሮአቸው እስካሁኑ ሰአት ድረስ በእገታ ላይ ይገኛሉ” ሲልም ፓርቲው ገልጿል።

የሚመለከታቸውን መርማሪዎች እና የፖሊስ ኃላፊዎች አመራሩ እንዲለቁ ወይም ፍርድ ቤት እንዲያቀርቧቸው መጠየቁ የገለጸው ፓርቲው፤ “ከላይ መመሪያ እየጠበቅን ነው” በማለት ማክሰኞ ጥቅምት 20/2016 በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት መቅረባቸውንም አመላክቷል።

የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም እንደ የአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ እና ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች በተመሳሳይ በአምስት ሺሕ ብር ዋስ እንዲወጡ ቢወሰንም፤ ፖሊስ አሁንም “ከበላይ አካል መመሪያ አልተሰጠኝም” በሚል ምክንያት የፓርቲውን አመራር ከእስር አለመልቀቁ ተጠቁሟል።

“ይሄ ሁሉ ሂደት የእስሩ ፖለቲካዊነት ግልጽ የሚያደርግ ነው” ያለው ፓርቲው፤ መላኩ ላይ የተፈጸመው ሕገ ወጥ እገታ የግለሰቡን መሰረታዊ የሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የገፈፈ ፖለቲካዊ እስር ብቻ ሳይሆን፤ በአገራችን የፍትህ ስርዓት ላይ የተደቀነው አደጋ በግልፅ የሚያመላክት ነው” ሲልም ገልጿል።

የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትህ ፓርቲ የአለም ዓቀፍ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ የሆኑት መላኩ ሳህሌ፤ ጥቅምት 14/2016 ከቤታቸው አቅራቢያ በጸጥታ ኃይሎች ታፍነው መወሰዳቸውን ፓርቲው ማስታወቁን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።