November 2, 2023 

“የአማራ ክልል አሁናዊ ኹኔታን አስመልክቶ ኢሰመኮ ያወጣው ሪፖርት ሚዛናዊነት የጎደለው ነው” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የአማራ ክልልን አሁናዊ ኹኔታ አስመልክቶ ሰሞኑን ያወጣው ሪፖርት፤ ሚዛናዊነት የጎደለው ነው ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው የትጥቅ ግጭት፤ በአንዳንድ አካባቢዎች በከባድ መሣሪያ እና አልፎ አልፎ በአየር/ድሮን ድብደባ ጭምር የታገዘ ነው ሲል፤ ጥቅምት 19/2016 ባወጣው የምርመራ ሪፖርት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

ኮሚሽኑ በአማራ ክልል ለወራት የቀጠለው የትጥቅ ግጭት ዐውድ እና አሉታዊ የሰብዓዊ አንደምታውን አስመልክቶ ባወጣው በዚህ መግለጫው፤ በትጥቅ ግጭቱ በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱን ገልጿል፡፡

እንዲሁም ግጭቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች የመንግሥት የጸጥታ አካላት በመንገድ ላይ ወይም ቤት ለቤት ፍተሻ በማድረግ ከያዟቸው በርካታ ሲቪል ሰዎች ውስጥ “ፋኖን ትደግፋላችሁ፣ ለፋኖ መረጃ ትሰጣላችሁ፣ መሣሪያ አምጡ፣ የተኩስ ድምጽ ስለተሰማበት አቅጣጫ መረጃ ስጡ” በሚልና ይህንን በመሰሉ ምክንያቶች ከሕግ ውጭ የሆኑ ግድያዎች መፈጸማቸውን የሚያሳዩ ተዓማኒ መረጃዎች ደርሰውኛል ሲል ኮሚሽኑ ማስታወቁም አይዘነጋም፡፡

ይህን ተከትሎ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አግልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በዛሬው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጅን አስፈላጊ ያደረገው የጸጥታ ችግር እና የሕገወጥ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ በተለያየ መልኩ መሰረታዊ የሆኑ የሰብዓዊ መብቶች ላይ አደጋ ላይ በመጣሉ ምክንያት ነው” ብለዋል፡፡

በሕይወት የመኖር መብትን፣ በነጻነት የመንቀሳቀስ መብትን፣ የትምህርት መብትና ሌሎች መብቶችን እንዲሁም፤ ሕግ እና ስርዓትን አደጋ ላይ የጣለ የታጣቂዎች እንቅስቃሴ በመከሰቱ ምክንያት በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

“ይህን ኹኔታ ለመለወጥ መንግሥት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማዕቀፍ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግና አንጻራዊ ሰላም በማስከበር ዜጎች ወደ መደበኛ ሰላማዊ ኑሯቸው መመለስ እንዲችሉ፤ እንዲሁም መሰረታዊ መብታቸው በተሻለ ኹኔታ እንዲጠበቅ የሕግ ማስከበር ሥራ ሰርቷል” ሲሉም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን “በቅርቡ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያወጣው መግለጫ ይህን ዐውድ እና እውነታ ከግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም” ያሉት ሚኒስትሩ፤ “መግለጫው አስተማማኝ በሆነ መረጃ ላይ ያልተመሰረተና ሚዛናዊነት የጎደለው ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

“በሕገ መንግሥቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸምን የመከታተል ስልጣን የተሰጠው መርማሪ ቦርድ ባለበትና ቦርዱ ሃላፊነቱን እየተወጣ ባለበት ወቅት የኮሚሽኑ መግለጫ ገንቢ እና የሰብዓዊ ሁኔታን ለማሻሻል አወንታዊ ሚና የሚኖረው አይደለም” ሲሉ ዶ/ር ለገሰ የኮሚሽኑን ሪፖርት ውድቅ አድርገውታል፡፡

“በመሆኑም ኮሚሽኑ ይሄን ጉዳይ አስመልክቶ ተገቢውን እርምት እንደሚወስድ ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

አክለውም “ኢትዮጵያ ነጸ እና ገለልተኛ ተቋማት እየገነባች ነው ለዚህ አንዱ ማሳያ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ነው” ያሉ ሲሆን፤ ይህ ተቋም አሁንም ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ እንዲሰራ መንግሥት ተግቶ ይሰራል” ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ሚኒስቴሩ በመግለጫቸው፤ በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 3 ሺሕ 200 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው በመጀመሪያው ዙር 1 ሺሕ 51 ተጠርጣሪዎች የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀላቸውን የገለጹ ሲሆን፤ በኹለተኛው ዙር ደግሞ 931 ተጠርጣሪዎች የተሃድሶ ስልጠና እየወሰዱ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አክለውም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተጠርጣሪዎቹ የሰብዓዊ መብት አያያዝ መልካም መሆኑን ማረጋገጡን ገልጸዋል።