በትግራይ ክልል ከሰላም ስምምነቱ በኃላ ወደቀደመ ኑሯቸው መመለስ እንዳልቻሉ ነዋሪዎች ገለጹ
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተካሄደው አስከፊ ጦርነት እንዲያበቃ የፌደራል መንግሥትና የህወሓት አመራሮች መካከል የሰላም ስምምነት የተፈረመ ቢሆንም ወደቀደመው ኑሯችን መመለስ አልቻልንም ሲሉ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
ነዋሪዎቹ የሰላም ስምምነቱ በመደረጉ እና ጦርነቱ በመቆሙ ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ቀደመ ኑሯቸው መመለስ እንዳልቻሉ መግለጻቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል።
በትግራይ ክልል አክቲቪስት እና የሰብዓዊ ድጋፍ ሠራተኛ ለዜና ወኪሉ በሰጡት ቃል፤ ጦርነቱ በመላው ትግራይ መካሄዱን ገልጸው፤ በአሁኑ ሰዓት 90 በመቶ የሚሆነው የትግራይ ሕዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡
አክለውም “አብዛኛው ነዋሪ ወርሃዊ ደሞዝ አይከፈለውም” ያሉ ሲሆን፤ “ይሄን መመልከት በጣም ከባድ ነው” ሲሉም ገልጸዋል።
“በመቀሌ ሕይወት እጅግ ከባድ ነው” ያሉት ደግሞ፤ በከተማዋ ቀድሞ በሕክምና ሙያ የተሰማሩ ግለሰብ ናቸው።
ብዙ የሕክምና ባለሙያዎች ለዓመታት ደሞዝ ስላልተከፈላቸው ሥራቸውን ለማቆም መገደዳቸው የገለጹት ባለሙያው፤ ለመኖር ሲሉ በሌላ ዘርፍ ላይ ለመሰማራት መገደዳቸውም ጨምረው ነው ተናረዋል።
በጦርነቱ ወቅት ከምዕራብ ትግራይ ከሚገኘው ቤታቸው ተፈናቅለው መውጣታቸውን የተናገሩ አንዲት እናት በበኩላቸው፤ “እርዳታ ለስድስት ወራት ያህል ቆሟል፡፡ እዚ ያለነው ተፈናቃዮች ያለንበት ኹኔታ ተቀምጦ ሞትን ከመጠበቅ ጋር ይመሳሰላል” ሲሉ ከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።
እንዲሁም “በገበያዎች ላይ ያሉ ምርቶች ተደራሽ ካለመሆናቸው በላይ፤ ዋጋቸው ውድ በመሆኑ ቤተሰባቸውን መመገብ እንዳልቻሉ ገልጸው፤ “ወደ ቤታችን የመመለስ ተስፋ የለንም” በማለት ተናግረዋል።
በክልሉ አንድ ሚሊየን ሕዝብ የተፈናቀለ ሲሆን፤ ከዚህም ዉስጥ 234 ሺሕ የሚሆኑ በትግራይ ዋና ከተማ መቀሌ እንደሚገኙ የአለም ዓቀፍ የስደተኞች ድርጅት ማስታወቁን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።
ከዓለም የምግብ ፕሮግራም እና ዩኤስኤአይዲ ለክልሉ የሚሰጠው እርዳት “ለተጠቃሚዎች እየደረሰ አይደለም” በሚል የምግብ እርዳታ ማቆማቸውን ተከትሎ፤ ነዋሪው የዕለት ጉርሱን ለማግኘት ሲል ለልመና መዳረጉም ተገልጿል።
እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚስተዋለው የዋጋ ንረት እና የሥራ አለመኖር የበርካታ አባወራዎችን ምግብን ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊ ፍጆታዎችን ለመግዛት መቸገራቸው ተጠቁሟል።
በተጨማሪም የኤርትራ ወታደሮች በድንበር አካባቢ አሁንም መኖራቸው ስጋት መፍጠሩ የሚገለጽ ሲሆን፤ በተመሳሳይም በአንዳንድ አካባቢዎች በአማራ ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር በመሆናቸው ሙሉ በሙሉ መረጋጋት እንዳይቻል ማድረጉም በዘገባው ተመላክቷል፡፡