
በምስሉ ላይ ስለምትመለከቷቸው 3 ሰዎች እንዲሁም ሌሎች ፎቶ ግራፋቸው ለጊዜው ስላልተገኘ 3 በአጠቃላይ 6 ሰዎች ጉዳይ እንነግራችኋለን። እነዚህ 6 ወጣቶች ከሌሎች 10 ወጣቶች ጋር በባህርዳር ከተማ ከታሰሩ በኋላ በሄሊኮፕተር ተጭነው በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ የመጡ ነበሩ። ከአዲስ አበባ በኋላም ወደ አዋሽ አርባ ማጎሪያ ተወስደው በሰንሰለት ታስረው እንደነበር የዘ-ሐበሻ ምንጮች ይናገራሉ። ከዛ በኋላ ምን ሆኑ?… ይህን መረጃ ከመግለጻችን በፊት እነዚህ በሄሊኮፕተር ተጭነው ከባህርዳር አዲስ አበባ ገብተው ከዛም በሰንሰለት እንዲታሰሩ የተደረጉት በባህርዳር ተይዘው የነበሩት ወጣቶች እነማን ናቸው?
በምስሉ ላይ የምትመለከቱት ታደለ አሰፋ ይባላል። የዘመነ ካሴ ዘመድ ነው ተብሎ ነው ከባህርዳር የተያዘው። የዘመነ ካሴ ዘመድ ስለሆነ ብቻ መረጃ ይኖረዋል በሚል በአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ እና የኮማንድ ፖስቱ አባል ዶ/ር መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) ጠቋሚነት እንደታሰረ ተገልጿል።
ሁለተኛው በምስሉ ላይ የምትመለከቱት በአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ እና የኮማንድ ፖስቱ አባል በዶ/ር መንገሻ ጥቆማ የተያዘው ደግሞ ቴዎድሮስ ይባላል። ይህ ወጣት የካሜራ ባለሙያ እንደሆነ የሚናገሩት ምንጮች የፋኖን እንቅስቃሴዎች በቪዲዮ ይቀርጻል በሚል ከባህርዳር በሂሎኮፕተር ተወስዶ አዲስ አበባ ከዚያም በአዋሽ አርባ በሰንሰለት ታስሮ ሲሰቃይ እንደነበር ቤተሰብ ለዘ-ሐበሻ ገልጿል።
ይህኛው በምስሉ ላይ የምትመለከቱት ደግሞ ወተቱ አድማሱ ይባላል። የአባይ ባንክ ጥበቃ ነበር። ይህም እንዲሁ በተመሳሳይ ባለስልጣን ከተጠቆመባቸውና ከታሰሩት 16 ሰዎች መካከል አንዱ ነው። ባለቤቱ ከ2 ሳምንት በፊት የልጅ እናት ሆናለች። በተመሳሳይም ፎቷቸው እጃችን ያልገባ የባህርዳር ድባንቄ መድሃኔዓለም ቤተክርስቲያን መሪጌታ፣ ዮሐንስ የተባለ ወጣትን ጨምሮ 6 ሰዎች በፋኖ ጉዳይ ተጠርጥረው በሰንሰለት እጅግ እና እግራቸው ከታሰሩበት አዋሽ አርባ ድንገት ተጠርተው ባልታወቁ ኃይሎች ከተወሰዱ በኋላ የት እንደደረሱ እስካሁን አይታወቅም።
ከባህርዳር ከሄሊኮፕተር ከተወሰዱት 16 ታሳሪዎች መካከል 6ቱ ከአዋሽ አርባ ባልታወቀና ታርጋ በሌለው መኪና እንደተወሰዱ የሚናገሩት ቤተሰቦቻቸው በአሁኑ ሰዓት በየትኛውም እስር ቤት ሊያገኟቸው እንዳልቻሉ ገልጸዋል። ገድለዋቸው ከሆነም ይንገሩን እና እርማችንን እናውጣ የሚሉት ቤተሰቦች በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንዳሉ ለዘ-ሐበሻ ገልጸዋል።
እንደ ቤተሰብ ከሆነ 6ቱ ተመርጠው በሰንሰለት መታሰራቸው ሳያንስ፣ የአዋሽ አርባ አስተዳዳሪዎች ላልታወቀ ኃይል ታርጋ በሌለው መኪና ተጭነው እንዲሄዱ መፍቀዱ እንዳሳዘናቸውና አሁን ደግሞ የት እንዳሉ አለማወቃቸው በሕይወት ይኖሩ ይሆን አይኖሩ ይሆን የሚል ጥያቄ እንዳስነሳብቸው ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ለዚህም እነዚህ ወጣቶች እንዲታሰሩ ያደረገው በአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ እና የኮማንድ ፖስቱ አባል ዶ/ር መንገሻ ኃላፊነቱን ይወስዳል ሲሉ የቤተሰብ አካላት ይናገራሉ።
ለዘ-ሐበሻ የደረሰው መረጃ እንደሚያመልከተው ዶ/ር መንገሻ ከዚህ ቀደም ከሕወሓት አገዛዝ ጀምሮ የቆቦ ከተማ ከንቲባ ሆኖ ያገለገለ ከመሆኑም በላይ የከተማዋን መሬት ቸብችቦ ሸጧል በሚል ክስ ሲቀርብበት ነበር። ዶ/ር መንገሻ እነዚህ 16 ወጣቶች ከባህርዳር በሄሊኮፕተር ተጭነው እንዲሄዱ ካስደረገ በኋላ ለሕይወቴ ሰግቻለሁ፤ ልጆቼንም ማስተማር አልቻልኩም፤ ማስፈራሪያም እየደረሰኝ ነው በማለት ወደ አዲስ አበባ እንዲቀየር ለብልጽግና ጽህፈት ቤት ደበዳቤ ማስገባቱን የዘ-ሐበሻ ምንጮች ገልጸዋል።
እኔ እዚህ ቦታ የተሾምኩት ለጥቂት ጊዜ ዶ/ር ዐብይ አገልግል ብሎኝ ነው የሚለው ዶክተር መንገሻ በቻይና ለ4 ዓመት ከ5 ወር ተምሮ ዶክትሬቱን እንደያዘ የሚናገሩት የዘ-ሐበሻ ምንጮች በአስቸኳይ ወደ አዲስ አበባ ካልቀየሩት የሱም ሆነ የቤተሰቡ ሕይወት አደጋ ላይ መውደቁን በየቀኑ ውትወታ እያደረገ ነው ብለዋል።
ከአዋሽ አርባ በሰንሰለት ታስረው የነበሩና የደረሱበት ያልታወቀው የሥድስቱ ወጣቶች ጉዳይ ላይ ከምንግስት በኩል ያለውን ምላሽ ለማስተናገድ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ወደ ዶ/ር መንገሻ ስልክም በተደጋጋሚ ደውለን ስልኩ ባለመነሳቱ የሱንም አስተያየት ማካተት አልቻልንም። ቤተሰብ ግን የአማራ ሕዝብ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረደን እያለ ነው። ዘ-ሐበሻ