November 2, 2023 – Konjit Sitotaw

በሰላም መደፍረስ ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጪ የኾኑ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ በትኩረት መሥራታ እንደሚገባ የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ አሳሰበ።

ከመስከረም ጀምሮ የትምህርት ዘመኑ የመማር ማስተማር ሂደቱ መጀመሩ ይታወቃል። የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ታደሰ ሸዋፈራው በሰጡን መረጃ “በጸጥታ ችግር ምክንያት በዞኑ 310 ሺህ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ኾነዋል” ብለዋል።

በአንደኛ ደረጃ ትምህር ቤት መማር የነበረባቸው 219 ሺህ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው። በተመሳሳይ በሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች መማር የነበረባቸው 57 ሺህ ተማሪዎች የመማር እድል አላገኙም።

33 ሺህ የቅድመ መደበኛ ተማሪዎችም ወደ ትምህት ቤት አልሄዱም። በአጠቃላይ በዘንድሮው የመማር ማስተማር ጅማሮ 500 ትምህርት ቤቶች ከመማር ማስተማር ተግባር ውጪ ናቸው። አንድ ትምህርት ቤት ደግሞ የተማሪዎች ምዝገባ እንኳን አላደረገም።

የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ በርካታ ውስንነቶች መኖራቸው ይታወቃል። ከነዚህ ውስንነቶች መካከል የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ አናሳ መኾን፣ በሽፋንም ይሁን በጥራት የትምህርት መሠረተ ልማት በሚፈለገው ደረጃ አለመሟላት፣ የግብዓት እጥረት እንዲሁም በልዩ ልዩ መልኩ ሊገለጽ የሚችል የፍላጎት ማነስ ተጠቃሽ ናቸው።

በተጠቀሱት እና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት በየትምህርት ክፍሎቹ የሚመዘገበው ውጤት አመርቂ አይደለም። ወደ ቀጣዩ የትምህርት ደረጃ የማለፍ ምጣኔው አናሳ እየኾነ ስለመምጣቱም ከሰሞኑ ይፋ በተደረገው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት መረዳት ይቻላል።

አሁን ላይ በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ታዳጊዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸው ደግሞ ችግሩን ‘በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ’ አድርጎታል። ባለሙያዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው የትምህርት ዘርፉን መደገፍ አለመቻላቸውንም አቶ ታደሰ ነግረውናል።

“የሁሉም ነገር መሰረቱ ሰላም ነው” ያሉት ኀላፊው ሰላም የጠፋበት አካባቢ ከልማት እና ከእድገት የተነጠለ መኾኑ አይቀሬ ስለመኾኑ አስገንዝበዋል። ስለዚህ ከምንም ነገር ቅድሚያ ለሰላም መስራት ይገባል ነው ያሉት።

የሰላምን ዋጋ በውል በመገንዘብ ስለሰላም እንሥራ፤ ተሻጋሪ አስተሳሰብ ያላቸውን ሀገር ተረካቢ ልጆች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱም ሁላችንም ጥረት እናድርግ ሲሉ ኀላፊው ጥሪ አቅርበዋል።