
ከ 3 ሰአት በፊት
በትግራይ ለሁለት ዓመታት የቆየውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ በዘላቂነት ከተገታ አንድ ዓመት ሆነው።
ሁለቱ ወገኖች ባለ 12 ነጥብ የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርጓል፤ ጦርነቱም ቆሟል።
ከአንድ ዓመት በኋላ የስምምነት አፈፃፀም ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
የሰላም ስምምነቱ በተለይ ለሁለት ዓመታት ያህል በከበባ ስር በከባድ ጦርነት ስር ሆኖ ለቆየው ለትግራይ ሕዝብ ታላቅ ተስፋን ፈጥሯል። ከዚያም በኋላ በክልሉ ጦርነት እና የጦርነትን ወሬ ሳይሰማ አንድ ዓመት ሆኗል።
በክልሉ ለረጅም ጊዜ ተቋርጠው የነበሩት የስልክ፣ የባንክ እና የመብራት አገልግሎቶች ሥራቸውን ቀጥለዋል። ባለፈው አንድ ዓመት በትግራይ ውስጥ መደበኛ ሕይወት እና እንቅስቃሴ እንዲመለስ ጥረት እየተደረገ ነው።
የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ ሽብርተኛ ድርጅት ተብሎ የተፈረጀው የክልሉ ዋነኛ የፖለቲካ ፓርቲ ህወሓት ከሽብርተኛ መዝገብ ውስጥ ስሙ የተፋቀ ሲሆን፣ ከፌዴራል መንግሥት ጋር መደበኛ ግንኙነት ተጀምሮ ጊዜያዊ አስተዳደርም ተቋቁሟል።
በዚህም በአሜሪካ እና በተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ እና በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት የተደረሰው የፕሪቶሪያው ስምምነት የተለያየ መልክ እና የተደበላለቀ ስሜት ይዞ ለአንድ ዓመት ቆይቷል።
በተለይም ከአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ውጪ ያሉ ኃይሎች ከክልሉ መውጣት፣ የትግራይ ሕገ-መንግሥታዊ አስተዳደር ወደነበረበት መመለስ፣ አከራካሪ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች እልባት ማግኘት፣ በጦርነቱ ሳቢያ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ነበሩበት መመለስ የሚሉ ነጥቦች አሁንም አነጋጋሪ ናቸው።
- “ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጠብ ከሚያጭሩ ድርጊቶች መቆጠብ አለባቸው” አንቶኒ ብሊንከንከ 5 ሰአት በፊት
- ከሰላም ስምምነቱ አንድ ዓመት በኋላ በትግራይ የሚገኙ ተፈናቃዮች ሁኔታከ 5 ሰአት በፊት
- በአማራ እና በኦሮሚያ የሚካሄዱት ግጭቶች እንዳሳሰቧቸው ምዕራባውያን አገራት ገለጹ2 ህዳር 2023
የአንድ ዓመት የደፈነው የፕሪቶሪያው ስምምነት
ባለ 12 አንቀፁ የፕሪቶሪያው ስምምነት ጦርነቱን ከማስቆም ባለፈ የዜጎች ደኅንነት እንዲረጋገጥ፣ መልሶ ግንባታ እንዲካሄድ፣ ተጠያቂነት እንዲሰፍን እና በጦርነት እና በረሃብ የተጎዱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ ያለመ ነው።
በጦርነቱ ወቅት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በጅምላ ግድያ፣ በረሃብ እና በመድኃኒት እጦት ሕይወታቸውን እንዳጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮችም በችግር ውስጥ ይገኛሉ።
“ጦርነቱ ቆሟል፤ ግን ሰላም ምንድን ነው? ጦርነትስ ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ ማንሳት አስፈላጊ እንደሆ በመቀለ ዩኒቨርሲቲ የሰብአዊ መብት እና የዓለም አቀፍ ሕግ ምሁር ረዳት ፕሮፌሰር መኮንን ፍስሃ ይገልጻሉ።
“ጦርነት በድሮን እና በሚሳይል ብቻ አይደለም፤ ሰላም ማለት የሰው ልጅ አእምሮ ነፃ ሆኖ ብዙ ሰዎች በሰላም ወጥተው በሰላም ሲገቡ እና ወደ ተለመደው ኑሯቸው ሲመለሱ ነው። በተግባር ግን የትግራይ ሕዝብ የቀጥታ ጦርነት ቀረለት እንጂ አሁንም መከራ ውስጥ ነው ያለው” ይላሉ።
አክለውም በሽሬ፣ በመቀለ፣ አቢ አዲ እና በሌሎችም ስፍራዎች በጊዜያዊ መጠለያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮችን እንዲሁም የወሲባዊ ጥቃት ሰለባ ለሆኑ የፍትህ ሂደቱ አለመጀመሩ ስምምነቱ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ የሚያሳይ እንደሆነ ይገልጻሉ።
በቅርቡ የትግራይ ብሔራዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሆነው የተሾሙት አቶ ክብሮም በርሄ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “በስምምነቱ አተገባበር የሚሰማኝ ነገር የተደበላለቀ ነገር ነው። የሰላም ተስፋ ነው። በሌላ በኩል፣ የቀረው ተኩሱ ወይም ውጊያው ነው እንጂ ጦርነቱ እንደቀጠለ ነው” ይላል።
ለዚህም ሃሳባቸው ዋነኛው ምክንያት የሚሉት የውጭ ኃይሎች ትግራይን ለቀው እንዲወጡ የሚለው የስምምነቱ አካል ተግባራዊ ባለመሆኑን ነው።
የውጭ ኃይሎች እና የትግራይ ክልል
ከስምምነቱ ዋና ዋና መርሆች አንዱ የትግራይን ክልል የግዛት አንድነት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት እንዲመለስ የሚል ይገኝበታል።
በተለይ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል በይገባኛል የሚያከራክሩ የድንበር ጉዳዮችን በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት ለመፍታት ቃል ተገብቶ ነበር።
“የፌደራል መንግሥቱ ያለውን የወሰን ጉዳይ ወደ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለመምጣት እና ለመፍታት ያለው ፍላጎት በጣም ዝቅተኛ ነው። ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለምን ያህል ጊዜ በሥልጣን ላይ እንደሚቆይ እና መቼ ምርጫ እንደሚካሄድ አይታወቅም። የፌደራል መንግሥት በትግራይ የሚጠበቅበትን ግዴታ እየተወጣ አይደለም” ይላሉ አቶ መኮነን ፍስሃ።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋ “ዋናው እንቅፋት የሆነው የውጭ ኃይሎች በትግራይ ክልል ውስጥ መኖራቸው ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነገር ግን ከጅምሩ ስምምነቱን ያደናቅፋሉ ተብለው የተጠበቁ፣ ነገር ግን የስምምነቱ አካል ያልሆኑ የውጭ ኃይሎች አሁንም በክልሉ ውስጥ ሰፋፊ ቦታዎችን ተቆጣጥረው እንደሚገኙ አቶ አማኑኤል ይናገራሉ።
ፍትህ ያላገኙ ተጎጂዎች
በጦርነቱ ውስጥ የተሳተፉ ኃይሎች በሙሉ በከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት የተከሰሱ ሲሆን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችም እነዚህ ጥሰቶችም ከስምምነቱ በኋላ እንደቀጠሉ ባወጧቸው ሪፖርቶች አመልክተዋል።
ሂዩማን ራይትስ ዋች እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ስምምነቱ ከተፈረመ ከስድስት ወራት በኋላ ባወጡት አጠቃላይ ዘገባ በምዕራብ ትግራይ የሚገኙ የአካባቢ አስተዳዳሪዎች እና የአማራ ኃይሎች “የትግራይ ተወላጆችን በኃይል እያፈናቀሉ የዘር ማጽዳት ወንጀል እየፈጸሙ ነው” ብለዋል።
በተጨማሪም በጦርነቱ ወቅት ከፌዴራል መንግሥቱ ጎን ተደልፈው ሲዋጉ የቆዩ የኤርትራ ወታደሮች በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየፈፀሙት ያለው ጥሰት እንዳልቆመ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኮሚሽን ሰነዶች ያመለክታሉ።
መንግሥት ተፈጽመዋል የተባሉትን ወንጀሎች በሽግግር ፍትህ ሂደት ማየት እንደሚያስፈልግ ሲገልጽ፣ በቅርቡ ሥራው የተቋረጠው የተመድ ኮሚሽን ግን የአገር ውስጥ ሂደቱ ፍትህን ከማስፈን አንጻር “ብቁ ያልሆነ እና ወገንተኛ ነው” ሲል ደምድሟል።
ከዚህ አንጻርም ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በኩል ቅሬታዎችም ይሰማሉ።
የዕርዳታ መቋረጥ
በጦርነቱ ወቅት 90 በመቶው ሕዝብ እርዳታ ጠባቂ ሆኖ እንደነበር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘገባ ያመለክታል። አፋጣኝ እና ያልተገደበ የሰብአዊ አገልግሎት ወደ ክልሉ እንዲገባ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ሲቀርቡ ነበር።
ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በነበሩ የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት የዕርዳታ አቅርቦት ወደ ክልሉ መግባት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ ረጂ ድርጅቶች አጋጥሟል ባሉት ስርቆት እና ዕርዳታው ላልተገባ አላማ ውሏል በማለት አስካሁን ተቋርጦ ይገኛል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) በግንቦት ወር ለትግራይ ያቀርቡ የነበረውን የምግብ እርዳታ አቁመዋል።
በዚህም ምክንያት “ብዙ ሰዎች በሞት አፋፍ ላይ ናቸው” ሲሉ ረዳት ፕሮፌሰር መኮንን ይገልጻሉ።
በመገናኛ ብዙኃን በኩል የወጡ ሰነዶችን እንዳመለከቱት በፌደራል እና በክልል የመንግሥት ተቋማት አማካይነት በዕርዳታ አቅርቦቶች ላይ “የተደራጀ የወንጀል” ድርጊት በመላው አገሪቱ መፈጸሙን አመልክተዋል።
ከተጠርጣሪዎቹ መካከል የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የዕርዳታ ሠራተኞች፣ በግጭቱ የተፈናቀሉ ሰዎችን የሚያስተናግዱ ካምፖች አስተዳዳሪዎች እና የምግብ ዕርዳታ አቅርቦት አጋሮች እንደሚገኙባቸው ተገልጿል።
ትጥቅ ማስፈታት እና ዳግም ማቋቋም
ከፕሪቶሪያው ስምምነት ዋነኛው የተዋጊዎችን ትጥቅ ማስፈታት ሲሆን፣ የትግራይ ታጣቂ ኃይሎችን መልሶ ማቋቋም የስምምነቱ አንድ አካል ነው።
የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢዎች፣ የማዕከላዊው መንግሥት እና የትግራይ መሪዎች እንዳረጋገጡት የትግራይ ኃይሎች በተለያዩ ጊዜያት የከባድ መሳሪያ ትጥቆቻቸውን ፈትተው ለፌደራል መንግሥት አስረክበዋል።
ነገር ግን የትግራይ ኃይል አባላትን በታህድሶ ወደ ሕብረተሰቡ የመቀላቀል ሂደት አለመፈጸሙ አነጋጋሪ ሆኖ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ቅሬታዎችን እያስነሳ ነው።
ይህንን ሥራ ለማቋቋም የፌደራል መንግሥቱ ያዋቀረው ኮሚሽን በአገር አቀፍ ደረጃ ወደ 400,000 የሚጠጉ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም አላማ እንዳለው ቢገልጽም እስካሁን ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የገንዘብ ድጋፍ አላገኘም።
የአተገባበረ ጉድለቶች ምንድን ናቸው?
ረዳት ፕሮፌሰር መኮንን ፍስሃ ሦስት ምክንያቶችን ያስቀምጣሉ።
አንደኛው በተደራዳሪ ወገኖች መካከል ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኝነት እና ፈቃደኝነት አለመኖሩ ነው።
“የፌዴራል መንግሥት ፍቃደኝነት አላሳየም። የትግራይ መንግሥትም አልጠየቀም። ጥያቄህን በአግባቡ አለማቅረብ” ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል ይላሉ።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በትግራይ ሰላም ሰፍኗል፣ ሁሉም ነገር አብቅቷል ብሎ ትኩረቱን በመቀየሩ አተገባበሩ ላይ ችግር ሊከሰት ችሏል በማለት የተደራጀ ሂደት አለመኖሩ ችግር እንደሆነም ያብራራል።
ሌሎች ደግሞ በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች (በተለይም በአማራ ክልል) መባባሳቸው ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ይገምታሉ።
ፖለቲከኛው ክብሮም በርሄ በበኩሉ “የፕሪቶሪያ ስምምነት የሰላም ተስፋ ቢፈጥርም በወረቀት ላይ ተንሳፎ የቀረ ነው። ምክንያቱም የትግራይ ኃይል ከሁሉም በላይ በሥልጣኑ ላይ አተኩሮ እየሠራ ነው። ከማንኛውም አካል ጋር ያለው ግንኙነት ሥልጣኑን ያማከለ ነው” ሲል ይወቅሳል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩስ ምን ይላል?
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ዋናው እንቅፋት የአማራ እና የኤርትራ ኃይሎች ከክልሉ አለመውጣታቸው በማንሳት፣ ለዚህም “የፌዴራል መንግሥት የተጣለበትን ኃላፊነት እና ተግባር ባለመወጣቱ ነው” ይላሉ።
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና በፓርቲ ደረጃ ያለው የፖለቲካ መከፋፈል ሂደቱን በአግባቡ ላለመከታተል እና ላለማስፈጸም አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳለው አቶ አማኑኤል ያነሳሉ።
‹‹እንደ ጊዜያዊ አስተዳደር በትኩረት እየሰራበት ነው። ነገር ግን ከሁኔታዎች ጋር የማይጣጣሙ የውስጥ ግጭቶች በጉዳዩ ላይ ሙሉ በሙሉ ትኩረት ተደርጎ እንዳይሰራ አድርጓል።”
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋነኛ አጀንዳ “የትግራይ ሕዝብን ህልውናውን እና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ ግዛቱን እና ሕዝቡን ከወራሪ ኃይል ነፃ ማውጣት፣ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ነው” የሚሉት አቶ አማኑኤል፣ “ነገር ግን የውስጥ ግጭቶች እነዚህ አጀንዳዎች በቂ ትኩረት እንዳያገኙ እያደረጋቸው ነው” ብሏል።