
ከ 5 ሰአት በፊት
ለሦስተኛ ጊዜ ነው ድንበር ለመሻገር የሞከሩት።
አሁን ግን ተስፋ አላቸው። ድንበሩ በቅርቡ እንደሚከፈት ተነግሯል።
ይሄ ቤተሰብ በራፋህ በኩል እንዲወጣ በዮርዳኖስ ኤምባሲ ተነግሯታል።
ታላ አቡ ናህላ እናቷ የዮርዳኖስ ዜጋ ናቸው።
የውጭ አገር ፓስፖርት ያላቸው እንዲሁም የተጎዱ እና ክፉኛ የታመሙ ሰዎች በራፋህ ድንበር በኩል እንዲወጡ እንደሚፈቀድ ተገልጿል።
የታላ ወንድም 15 ዓመቱ ነው። አካል ጉዳተኛ ሲሆን፣ የሚጥል ሕመም አለበት። የሚንቀሳቀሰው በተሽከርካሪ ወንበር (ዊልቼር) ብቻ ነው።
በጋዛ ያሉ ሆስፒታሎች ለእሱ የሚሆን መድኃኒት ጨርሰዋል።
የቦምብ ፍንዳታዎች ደግሞ ሕመሙን አባብሰውበታል።
“ግጭቱ ሲጀመር በጣም ነው የፈራው። የሚጥል ሕመሙ እየተባባሰ መጣ። ከዚህ አይብስም ብዬ ባሰብኩ ቁጥር ሕመሙ የበለጠ እየባሰ ይሄዳል” ትላለች ታላ።
- “ይሄ የትንሿ ልጄ ፒጃማ ነው” 11 የቤተሰቡን አባላት በአንድ ጥቃት ያጣው የጋዛው አባት2 ህዳር 2023
- በጋዛ የካቶሊክ መነኮሳት፡ “ሕዝባችንን ጥለን ወደ የትም አንሄድም”27 ጥቅምት 2023
- የግጭቱ ሰለባ ሆነው ሞታቸው ያልታመነላቸው የ4 ዓመቶቹ የፍልስጥኤም እና የእስራኤል ሕጻናት27 ጥቅምት 2023
የእነ ታላ ቤተሰብ ስድስት ናቸው። ብቸኛው የቤቱ አስተዳዳሪ ታላ ናት።
ነጻ የትምህርት ዕድል አግኝታ በአሜሪካ እና ሊባኖስ ተምራለች።
በራሷ የምትተማመነው እና ራሷን ለመግለጽ የማትቸገረው ታላ፣ ቤተሰቧን ከጋዛ ድንበር ውጭ ስትመራ ለመመልከት አይቸግርም።
“ለመኖር እየታገልን ነው” ትላለች።
“እንደሚሳካልን እርግጠኛ አይደለንም። ግን ለመኖር ስንል ማድረግ የምንችለውን ሁሉ እያደረግን ነው። ምክንያቱም በ24 ዓመቴ በፍጹም መሞት አልፈልግም።”
በዚህ የድንበር አካባቢ “ዕድል” የሚለው ቃል ትርጉሙ ሌላ ነው።
በዚህ አካባቢ ዕድል ማለት ከቦምብ ጥቃት ማምለጥ፣ ከመራብ እና ከመጠማት ማምለጥ ማለት ነው።
የውጭ አገር ፓስፖርት የሌላቸው የቤተሰብ አባላትን ጥሎ መውጣትንም ይጨምራል።
የሚወዱትን ቤተሰብ፣ በጥቃት መካከል ወደ ድንበሩ መጓዝ ያልቻለን ቤተሰብ ወይም ከፍተኛ የአካል ጉዳት ስላልደረሰበት መውጣት ያልቻለን ቤተሰብ ወደኋላ ጥሎ መሄድን ይጨምራል።

በጋዛ 2.2 ሚሊዮን ሰዎች ናቸው የሚኖሩት። ከእነዚህ ነዋሪዎች መካከል ከጋዛ የወጡት ወይም መውጣት የሚችሉት በጣም ጥቂት ናቸው።
ሞና በጋብቻ አውስትራሊያዊ ዜግነት አላት።
ወደ ራፋህ ድንበር የመጣችው ብቻዋን ነው። ቤተሰቧን ጋዛ ውስጥ ጥላ መምጣቷ ይረብሻታል።
“ደስተኛ አይደለሁም” ትላለች።
“ደስተኛ አይደለሁም። ምክንያቱም ግማሽ አካሌን ጥዬ ነው የመጣሁት። ወንድሞቼ፣ እህቶቼ እና ቤተሰቦቼም እዚያ ናቸው። ፈጣሪ ፈቅዶ ደኅንነቱ የተጠበቀ ቦታ ቢሆኑ እመኛለሁ። እዚያ ያለው ሁኔታ አሰቃቂ ነው። እጅግ እጅግ የከፋ ነው።”

በድንበሩ በጋዛ በኩል የሰዎች ስም ዝርዝር ተጽፏል።
እንዲወጡ ፈቃድ የተሰጣቸው ሰዎች ስም ዝርዝር ነው። ሰዎች ይህንን ዝርዝር እያዩ ስማቸውን ይፈልጋሉ።
መጠባበቂያ አዳራሽ ውስጥ ቤተሰቦች ላስቲክ አንጥፈው ተቀምጠዋል።
በዚህች ጠባብ ቦታ ትልቅ ተስፋ ተሰንቋል።
በመጀመሪያው ቀን ከጋዛ መውጣት የቻሉት 400 የውጭ ዜጎች እና የተጎዱ ሰዎች ናቸው።
ታላ አቡ ናህላ እና ቤተሰቧ በዚህ ቀን ለመውጣት አልተሳካላቸውም።
ወደ ቤታቸው መመለስ ግድ ሆኖባቸዋል። ቤታቸውን ጨለማ ውጦታል። መብራት የለም።
ታላ ምን ማሰብ እንደምትችል እና እንዴት እንደሚሰማት የማታውቅበት ደረጃ ላይ መድረሷን ትናገራለች።
“ወደ ጨለማ ቤት ተመለስን። ዛሬ ምግብ የለም። ንጹህ የመጠጥ ውሃም የለም። የወንድሜ መድኃኒት ሊያልቅ ተቃርቧል። አሁንም እዚህ ነን። ጨልሟል። እስከ ነገ ስለመቆየታችን እንጃ። ተስፋ ግን አደርጋለሁ።”