
ከ 4 ሰአት በፊት
የእስራኤል ጦር የሐማስ ጠንካራ ይዞታ የሆነውን የጋዛ ከተማን መክበቡን ገልጾ የሐማስ ተዋጊዎች ከዋሻዎች እየወጡ ጥቃት እየከፈቱ ነው ብሏል።
ጦሩ ከሐማስ ተዋጊዎች ጋር በቅርብ ርቀት ጦርነት መግጠሙንና የሐማስ ተዋጊዎች ከዋሻዎች በመውጣት ጥቃት ሰንዝረው እየሸሹ መሆኑን ጠቁሟል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለመጠለያነት ሆነው በማገልግል ላይ ያሉት አራት ትምህርት ቤቶቹ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጾ፤ የውሃ እጥረት እየተባባሰ መጥቷል ሲል አስጠንቅቋል።
በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከ9,000 በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ብሏል።
የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ኤጀንሲ ሐሙስ ዕለት እንደገለጸው ከ24 ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለመጠለያነት የሚያገለግሉ አራት ትምህርት ቤቶቹ ተጎድተዋል።
በጃባሊያ የስደተኞች ጣቢያ ውስጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት አንድ ህጻንን ጨምሮ ቢያንስ 20 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።
ቢቢሲ ከትምህርት ቤቶቹ የተገኙ ሁለት ቪዲዮዎችን ለማረጋገጥ ችሏል።
በሰሜናዊ ጋዛ በሚገኘው በጃባሊያ የስደተኞች ካምፕ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የተቀረጸ ተንቀሳቃሽ ምስል መጀመሪያ ከትምህርት ቤቱ ዋና በር እና ቀጥሎም በግቢው ውስጥ ያለውን ሁኔታ ያሳያል።
ህይወታቸው ያለፉ ወይንም የተጎዱ ህጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 20 ሰዎች መሬት ላይ ይታያሉ።
- “ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጠብ ከሚያጭሩ ድርጊቶች መቆጠብ አለባቸው” አንቶኒ ብሊንከንከ 5 ሰአት በፊት
- ከሰላም ስምምነቱ አንድ ዓመት በኋላ በትግራይ የሚገኙ ተፈናቃዮች ሁኔታከ 5 ሰአት በፊት
- “በ24 ዓመቴ በፍጹም መሞት አልፈልግም”፡ ከራፋህ ድንበር መሻገር ያልቻለችው ወጣትከ 5 ሰአት በፊት
በሰሜን ጋዛ በሚገኘው በቢች ስደተኞች ጣቢያ ባለ ትምህርት ቤት ዋና ህንጻ ጀርባ ጭስ ሲወጣ በሁለተኛው ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ይታያል።
በጋዛ የሚገኙ የሐማስ ባለስልጣናት የእስራኤል የአየር ጥቃትን ተጠያቂ አድርገዋል። የእስራኤል ጦር በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን አስተያየት አልሰጠም።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጃባሊያ የስደተኞች ካምፕ በደረሰ ፍንዳታ በትንሹ 20 ሰዎች መሞታቸውን ገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያዎች በጋዛ የሰብዓዊነት ተኩስ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል። በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማዊያን ላይ “የከፋ የዘር ማጥፋት አደጋ” ሊደርስ ጊዜው እያለቀ ነው ብለዋል።
“በጋዛ ያለው ሁኔታ አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል” ሲሉም ነዳጅ ወደ ጋዛ እንዳይገባ መከልከሉ እና የውሃ አቅርቦት በመቋረጡ ምክንያት ሰዎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ እያገኙ አይደለም ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
“ዛሬ ሁለት ሚሊዮን ጋዛውያን የመጠጥ ውሃ ለማግኘት እየታገሉ ነው” ብለዋል።
የእስራኤል ጦር ባለፈው ሐሙስ 130 የሚጠጉ የሐማስ ተዋጊዎችን መግደሉን ተናግሯል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው ሠራዊቱ በጦርነቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል።
“አስደናቂ ስኬቶችን አግኝተናል፤ የጋዛ ከተማን ዳርቻ አልፈናል። ወደፊት እየሄድን ነው” ሲሉ በመግለጫቸው ተናግረዋል።
ጋዛን ከግብጽ በሚያዋስነው የራፋህ ማቋረጫ ለሁለተኛ ቀን መከፈቱን ተከትሎ በርካታ የውጭ ዜጎች ጋዛን ለቅቀው መውጣት ችለዋል። ከእነዚህ መካከል ከ70 በላይ አሜሪካውያን መሆናቸውን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተናግረዋል።
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ግን ከ 20,000 በላይ የቆሰሉ ሰዎች ከግዛቱ መውጣት አንዳልቻሉ አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሊባኖሱስ ሂዝቦላህ በእስራኤል የሚገኙ 19 ዒላማዎችን በአንድ ጊዜ ማጥቃት መቻሉን ገልጿል።
የእስራኤል ጦር በሊባኖስ የሚገኙ የሂዝቦላ ዒላማዎችን በተከታታይ እየመታ መሆኑን ገልጿል።