የሄዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስራላህ
የምስሉ መግለጫ,የሄዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስራላህ

ከ 2 ሰአት በፊት

የሄዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስራላህ የእስራኤልና ሐማስ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ንግግር ያደርጋሉ ተባል።

የሊባኖሱ የሺዓ ሙስሊም ቡድን መሪ እስከዛሬ ድረስ ለተከታዮቻቸው በአደባባይ ያሉት ነገር የለም።

ሄዝቦላህ በቀጣይ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ሐሰን ናስራላህ ዛሬ በሚያደርጉተe ንግግራቸው እንደሚጠቁሙ ይጠበቃል።

የሄዝቦላህ ታጣቂዎች በእስራኤልና ሊባኖስ ድንበር ላይ ግጭት ውስጥ ገብተዋል።

አካባቢው ሌላ የጦር ግንባር ይሆናል ተብሎ ተሰግቷል።

እስካሁን ግን ግጭቱ ከቁጥጥር ሲወጣ አልተስተዋለም።

የእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት ከተነሳ ወዲህ ሌባኖስ ሄዝቦላህን በቅርበት እየተከታተለች ነው።

ሄዝቦላህ እስራኤል ላይ የሚሰነዝረውን ጥቃት እያጠናከረ መጥቷል።

እስካሁን ሁለቱም ወገኖች ግጭቱን ላለማባባስ ጥንቃቄ እያደረጉ ይመስላል። የአየር ጥቃቶችም በድንበር አካባቢ የተገደቡ ናቸው።

ይህ ግን ሊቀየር ይችላል።

እስራኤል በጋዛ በእግረኛ ጦር ወረራ ቀጥላለች። ሐማስን ማጥፋት ዓላማዬ ነው ትላለች።

በጋዛ የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ9,000 ማለፉ ተገልጿል።

ሐማስ አጋሮቹ ድጋፍ ሰጥተውት ውጊያውን እንዲቀላቀሉ እየጠየቀ ነው። ሄዝቦላህ ለጥያቄው ምላሽ ይሰጥ ይሆን የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ነው።

አሜሪካ ዩናይትድ ኪንግደምና ሌሎችም ምዕራባውያን አገራት ሄዝቦላህን አሸባሪ ቡድን ሲሉ ፈርጀዋል።

ሄዝቦላህ በሊባኖስ ዋነኛው የፖለቲከና ወታደረዊ ኃይል ነው።

የሄዝቦላህ ውሳኔ ከደጋፊዎቹ አልፎ በማይደግፉትም ዘንድ እየተጠበቀ ይገኛል።

እስካሁን ድረስ መሪው ሐሰን ናስራላህ የት እንደሚገኙ አይታወቅም።

ንግግሩ በሊባኖስ በሕዝብ መሰብሰቢያ አካባቢ በሚገኙ ስክሪኖች ነው የሚተላለፈው።

በሄዝቦላህ አባላት ዘንድ ይህ ንግግር ትልቅ ዋጋ ያለው እንደሆነ እየተገለጸ ነው።

ከዚህ ቀደም እንደሚደረገው ሁሉ ንግግሩ እንደሚደረግ ከአምስት ቀናት በፊት ነው ይፋ የተደረገው።

እአአ በ2006 ሄዝቦላህ ከእስራኤል ጋር ያደረገው የአንድ ወር ጦርነትን በርካታ ሊባኖሳውያን ያስታውሳሉ።

አገሪቷን መልሶ ወደ ሌላ ግጭት ያስገባ ነበር።

ሚሳኤሎችን ጨምሮ ሄዝቦላህ በርካታ መሣሪያዎች አሉት። እነዚህም ወደ እስራኤል ዘልቀው መግባት የሚችሉ ናቸው። በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ተገቢ ሥልጠና ያገኙ ተዋጊዎችም አሉት።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ሄዝቦላህ ለሁለተኛ ጊዜ ግጭት ከከፈተ “ለማሰብ የሚከብድ” ምላሽ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

አሜሪካ ግጭቱ እንዳይስፋፋ ወደ ምሥራቅ ሜዲትራኒያን ሁለት ተዋጊ አውሮፕላን ልካለች።

እስራኤል ሰፊ ጥቃት እንዳትከፍት አሜሪካ ማሰሰቧም ይታወቃል።

ጦርነት ሊባኖስን ወደ ከፋ ቀውስ ይከታታል። ከሄዝቦላህ ደጋፊዎች በዘለለ ሕዝቡ በስፋት የሚደግፈውም አይመስልም።

ሊባኖስ ለዓመታት የምጣኔ ሀብት ቀውስ ውስጥ ናት። የፖለቲካ ውጥንቅጡን ተከትሎ አገሪቱን የሚያስተዳድር የመንግሥት መዋቅርም ተሽመድምዷል።

የሄዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስራላህ
የምስሉ መግለጫ,የሄዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስራላህ

ሄዝቦላህ የሐማስን ጥሪ ተቀብሎ የሚሰነዝረውን ጥቃት ሊያሰፋ ይችላል።

ግጭቱ በሰሜናዊ እስራኤል ተወስኖ ሊቀጥል ይችላል።

የጆ ባይደን አስተዳደር ኢራንን በቀጥታና ከመጋረጃ በስተጀርባም ግጭቱን እንዳታባብስ እያሳሰበ ነው።

‘አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ’ በሚል ጥምረት ሥር በዋነኛነት ሄዝቦላህ፣ በኢራቅ የሚገኙ ታጣዊዎች የሶሪያው ፕሬዝዳንት በሽር አል-አሳድ፣ የየመን ሁቲ ታጣቂዎችና ሐማስ ይገኛሉ። ኢራንም ጥምረቱን ትደግፋለች።

ምን ያህል ቀጥተኛ ተጽዕኖ ማሳደር እንደምትችል ግን ግልጽ አይደለም።

ያለ ኢራን ይሁንታ ትልልቅ ውሳኔዎች ያሳልፋሉ ተብሎ ግን አይጠበቅም።

የኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሒም ራኢሲ ባለፈው ሳምንት ባደረጉት ንግግር፣ “እስራኤል ቀይ መስመር አልፋለች። ሁሉም እርምጃ እንዲወስድ ያስገድዳል” ብለዋል።

“አሜሪካ ምንም እንዳናደርግ ታሳስባለች። ሆኖም ለእስራኤል ሰፊ ድጋፏን ትሰጣለች” ሲሉም አክለዋል።

ለሄዝቦላህ ቅርብ የሆነ ምንጭ እንደገጹት ናስረላህ ነገሩን በቅርበት እየተከታተለ ሲሆን፣ ከቡድኑ ወታደራዊ ክንፍ ጋርም እየተነጋገረ ነው።

“ሄዝቦላህ እያንዳንዱን ጥቃቅን ነገር ሳይቀር እየተከታተለ ነው። ሁልጊዜም ስሌት ይሠራል” ብለዋል።