
ከ 1 ሰአት በፊት
ከአገሪቱ ጦር ሠራዊት ጋር እየተዋጋ ያለው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መላውን የሱዳን አካባቢዎች እቆጣጠራለሁ አለ።
የፈጥኖ ደራሹ ምክትል ኮማንደር የሆኑት አብዱልራሂም ሐምዳን ዳጋሎ ኃይላቸው ወደፊት የሚያደርገውን ግስጋሴ አስቀጥሎ ሁሉንም የሱዳን ግዛቶች በቁጥጥሩ ስር ያስገባል ብለዋል።
የቡድኑ ምክትል ኮማንደር ይህን ያሉት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የአገሪቱን ጦር ኃይል ከሱዳን ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ማስወጣቱ ከተገለጸ ከቀናት በኋላ ነው።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሠራዊት ከወራት ውጊያ በኋላ የአገሪቱን ጦር በማስወጣት የደቡብ ዳርፉር ዋና መዲና የሆነችውን ኛላ ከተማ ይዘዋል።
ምክትል ኮማንደር አብዱልራሂም ሐምዳን ዳጋሎ በማዕከላዊ ዳርፉር ግዛት ከድል በኋላ ደስታቸውን እየገለጹ ለነበሩ ወታደሮች ንግግር ሲያደርጉ፤ “ወደ ተቀሩት ግዛቶች እና የጦሩ ዋና መቀመጫዎች እንዘምታለን፤ ፈጣሪ ከፈቀደ በቁጥጥራችን ስር እናስገባቸዋለን” ብለዋል።
የጀነራል ሃምዳን ደጋሎ ወንድም እንደሆኑ የሚገለጸው የፈጥኖ ደራሹ ምክትል መሪ አብዱልራሂም ዳጋሎ ኛላ ከተማን ለመያዝ የተደረገውን ኦፕሬሽን መምራታቸው ተገልጿል።
በምዕራብ ዳርፉር በሰላማዊ ዜጎች ላይ በተፈጸመው የዘር ማጽዳት ወንጀል በአሜሪካ መንግሥት ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።
- የእስራኤል ጦር ጋዛ ከተማን ሙሉ በሙሉ መክበቡን አስታወቀ29 ጥቅምት 2023
- የሄዝቦላ መሪ ሐሰን ናስራላህ የቡድኑን ቀጣይ እርምጃን የሚጠቁም ንግግራቸው ዛሬ ሊያደርጉ ነውከ 2 ሰአት በፊት
- “ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጠብ ከሚያጭሩ ድርጊቶች መቆጠብ አለባቸው” አንቶኒ ብሊንከንከ 5 ሰአት በፊት
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በርካታ አካባቢዎች እና የአገሪቱ ጦር ማዘዣ ጣቢያዎችን ስለመቆጣጠሩ ሲገለጽ ቆይቷል።
የአገሪቱ ጦር መሪ ሌተናል ጀነራል አብደለ ፋታህ አል-ቡርሃን ግን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አስመዝግቧል የተባለውን ድል አጣጥለዋል።
አል ቡርሃን ከትናንት በስቲያ በመዲናዋ ካርቱም በሁለት የጦር ካምፖች የሚገኙ ወታደሮችን ጎብኝተው ንግግር ሲያደርጉ “መዋጋታችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።
ከስድስት ወራት በላይ ባስቆጠረው የሱዳን ጦርነት በአገሪቱ ጦር ሠራዊት መሪ ጀነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን የሚመራው ኃይል እና በጀነራል ሃምዳን ደጋሎ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል ውጊያ እየተካሄደ ነው።
እስካሁን ድረስ በዚህ ግጭት ከ7ሺህ በላይ ሰላማዊ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከአምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ መፈናቀላቸው ተገልጿል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከቅርብ ግዚያት ወዲህ ከውጪ መንግሥታት በሚያገኛቸው ድጋፎች ታግዞ በአገሪቱ ጦር ላይ ድል እየተቀናጀ መሆኑ እየተገለጸ ይገኛል።
የተባባሩት አረብ ኤሜሬቶች ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በቻድ እና በመካከለኛው አፍሪካ ሪፓብሊክ በኩል የጦር መሳሪያ ድጋፍ እያደረገች ነው በሚል ትወቀሳለች።
አቡ ዳቢ ግን ይህን አስተባብላለች።