ፓል ካጋሜ

ከ 1 ሰአት በፊት

የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፓል ካጋሜ የአፍሪካ አገራት ዜጎች ወደ ሩዋንዳ ያለ ቪዛ እንዲገቡ የሚፈቅድ አሠራር ይፋ አደረጉ።

ያለ ቪዛ አፍሪካውያን ወደ ግዛቷ እንዲገቡ በመፍቀድ ሩዋንዳ አራተኛዋ አፍሪካዊ አገር ናት።

“ማንኛውም አፍሪካዊ አውሮፕላን ተሳፍሮ ወደ ሩዋንዳ መምጣት እንደሚችል ለመግለጽ እወዳለሁ። አንዳችም ገንዘብ መክፈል አይጠበቅበትም” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ፕሬዝዳንቱ ይህ ውሳኔ የተላለፈው በአህጉሪቱ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ቁጥር ከመጨመሩ ጋር በተያያዘ እያደገ ካለው የአፍሪካ ቱሪዝም አገራቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ መሆኑን አክለዋል።

ሩዋንዳ የቱሪዝም ዘርፏን ለማሳደግ ንቅናቄ እያደረገች ነው።

አገሪቱ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እንደ አርሰናል እና ባየር ሙኒክ ካሉ የእግር ኳስ ክለቦች ጋር ጥምረት ስታደርግ ቆይታለች።

ኬንያ የቪዛ ገደቦችን በማንሳት ሁሉም አፍሪካውያን ቪዛ ሳያስፈልጋቸው ወደ ግዛቷ መግባት እንዲችሉ በሯን ለመክፈት መዘጋጀቷን ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ከቀናት በፊት መግለጻቸው ይታወሳል።

እስካሁን አፍሪካውያን ያለ ቪዛ መግባት እንዲችሉ የፈቀዱ አገራት ሲሸልስ፣ ጋምቢያ እና ቤኒን ናቸው።

ብዙ የአፍሪካ አገራት ያለ ቪዛ እንቅስቃሴ እንዲደረግ የሁለትዮሽ ስምምነት እየተፈራረሙ ይገኛሉ።

ከእነዚህም መካከል ጋና እና ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም ኡጋንዳ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮምጎ ይገኙበታል።

በአህጉሪቱ አገራት መካከል ከቪዛ ነጻ ጉዞ እንዲኖር ማድረግ ከአፍሪካ ኅብረት ያለፉት ዓመታት ግቦች አንዱ ነበር።

በአገራት እና በአገራት መካከል በሚደረጉ ስምምነቶች መሠረት ከቪዛ ነጻ እንቅስቃሴን የፈቀዱ ቢኖሩም የኅብረቱ ግብ ተግባራዊነት ግን አሁንም አዝጋሚ ነው።

አፍሪካ ኅብረት በ2016 ነበር የአፍሪካን ፓስፖርት ይፋ ያደረገው። ዓላማው ሁሉም አፍሪካውያን በአህጉሪቱ ውስጥ ያለምንም ቪዛ በቀላሉ እንዲዘዋወሩ ለማድረግ ቢሆንም በስፋት አልተሰራጨም።

ለዚህ ማነቆ ከሆኑት መካከል ደኅንነት፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና የሥራ ዕድል ጫና ይገኙባቸዋል።

የቪዛ ጥያቄን ማስቀረት ባይቻል እንኳን የቪዛ ዋጋን በመቀነስ፤ በደረሱበት አገር ቪዛ በመስጠት እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የኢ-ቪዛ ሥራ ላይ በማዋል ማሻሻል እንደሚቻል ቪዛ ኦፕነስ ኢንዴክስ ያወጣው ሪፖርት ያሳያል።