November 3, 2023 – Getachew Shiferaw 

ክብር አይሰጡትም!
ነገ ሰሜን ዕዝ የተመታበት ዕለት ነው። ጥቅምት 24!

ይሁንና አገዛዝ ለይምሰል እንጅ ለሰራዊቱ ክብር አይሰጥም። ትህነግ/ህወሓት በክልል ደረጃ ሶስት ቀን አውጆ ለታጣቂዎቹ “መከላከያን ማርኮ፣ ገድሎ” እያለ አስፎኮሮላቸዋል። ሰራዊቱን ነዳነው እያሉ ዘፍነዋል። በቅርቡ ነው።

የሰሜን ዕዝ መጠቃት ግን በአገዛዙ አይታወስም። ምክንያቱም ሰራዊቱን ሞቶ ስልጣን እንዲያስጠብቅላቸው እንደ ክብሪት እያነደዱ የሚጠቀሙበት እንጅ ክብር አይሰጡትም።

ሰሜን ዕዝን ቢያስታውሱ ለሰራዊቱ ክብር ከመስጠታቸው ባሻገር ማን አዳነው ሲባልም አማራና ኤርትራ ሊሆንባቸው ነው። እንዲጠቀስ አይፈልጉም።

ያን ያስመቱትንና ክብር የማይሰጡትን ሰራዊት በአማራ ላይ አዝምተውታል። ቢሞት ጉዳያቸው አይደለም። እንዲያውም ወደ ስልጣን እንዳያይ በጦርነት ማባከን አለባቸው። በሁለት አመቱ ጦርነት ወቅት ሰሜን ዕዝ የተመታበት ተከብሮ ነበር። አሁን እየረሱት ነው። ምክንያቱም ጊዜያዊ መቀስቀሻ እንጅ ሰራዊቱን በመርህ ስለማያከብሩት ነው።

ሰሜን ዕዝን ሲያጠቃ የተመታ የትህነግ/ህወሓት ታጣቂ ሰሞኑን በሰመአትነት ሲወደስ ሰንብቷል። የተጠቃው ሰራዊት ግን አስታዋሽ የለውም። ሰራዊቱ ያለ ማቋረጥ ጦርነት ውስጥ እንዲከርም እንጅ እንዲታወስ አይፈልጉም! የምታውቁትን የሰራዊት አባል “ይኸው በአገዛዙ ዘንድ ክብር የለህም” በሉት። ጠላቱ አገዛዙ እንደሆነ ድገሙለት። (ጌታቸው ሽፈራው)