ኤሪን ፓተርሰን

ከ 9 ሰአት በፊት

የ49 ዓመቷ አውስትራሊያዊት ኤሪን ፓተርሰን ሦስት ሰዎችን መርዛ በመግደልና የቀድሞ ባለቤቷን አራት ጊዜ ለመግደል በመሞከሯ ተከሰሰች።

በሦስት ግድያ እና አንድ የመግደል ሙከራ ክስ ተመስርቶባታል።

ቪክቶሪያ ግዛት ውስጥ በሚገኝ ቤቷ ምሳ ከጋበዘች በኋላ እንጉዳይ በመጠቀም ለመመረዝ መሞከሯ ተገልጿል።

ተከሳሿ ድርጊቱን እንዳልፈጸመች ተከራከራለች።

በዋስ ለመለቀቅ ግን ጥያቄ አላቀረበችም።

ፖሊስ ቤቷን ሲፈትሽ ያገኘውን ቁሳቁስ እስከሚመረምር ለዐቃቤ ሕግ ጊዜ እንደሚሰጥ ፍርድ ቤቱ ገልጿል።

የቀድሞ ባለቤቷ ሳይመን ፓተርሰን ለመግደል እአአ ከ2021 እስከ 2022 ባሉት ዓመታት ሦስት ጊዜ እንደሞከረች ተገልጿል።

አራተኛውን የግድያ ሙከራ የፈጸመችው ለቀድሞ ባለቤቷ እናትና አባት እንዲሁም አክስት ምሳ ያዘጋጀች ቀን እንደሆነና በዕለቱ ግን ባለቤቷ እንዳልተገኘ ተገልጿል።

ተከሳሿ ምግቡን ያዘጋጀችው ከወራት በፊት ከእስያውያን መደብር በገዛችው እንጉዳይ እንደሆነ ተናግራለች።

ምግቡን ከተመገቡ በኋላ የቀድሞ ባለቤቷ እናትና አባት በጠና ታመው ሆስፒታል ተወስደው ሞተዋል።

ተጠርጣሪዋ እንዲሁም ሁለት ልጆቿ ምንም ሕመም ስላልገጠማቸው ፖሊስ በጥርጣሬ በቁጥጥር ሥር አውሏታል።

ሆኖም ተጠርጣሪዋ እንግዶቿን የመመረዝ ዓላማ እንዳልነበራትና እሷም ምግቡን ከበላች በኋላ ታማ ሆስፒታል ተወስዳ መድኃኒት እንደተሰጣት ተናግራለች።

“እንጉዳዮቹ የምወዳቸው ሰዎች እንዲታመሙ በማድረጋቸው አዝኛለሁ” ስትል ቃሏን ሰጥታለች።

የግድያ መርማሪው ኢንስፔክተር ዲን ቶማስ “እንዲህ የመገናኛ ብዙኃን እና የሕዝብ ትኩረት የሳበ ጉዳይ አልገጠመኝም። እዚህ ቪክቶሪያ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም አነጋጋሪ ሆኗል” ብለዋል።

በአውስትራሊያ ከፍተኛ ትኩረትን የሳበውን የክስ ሂደት ለመከታተል በርካታ መገናኛ ብዙኃን በፍርድ ቤት ተሰባስበው ነበር።