ሐሰን ናስራላህ

4 ህዳር 2023, 08:02 EAT

ሐሰን ናስራላህ ከአውሮፓውያኑ 1992 ጀምሮ ሊባኖስ ውስጥ የሚገኘውን ሒዝቦላህን በመምራት አስካሁን ቆይተዋል። ከአገሪቱ ሠራዊት ጎን የታጣቀ ኃይል ያለው ቡድኑ በአሁኑ ጊዜ ሊባኖስ ውስጥ ካሉ የፖለቲካ ኃይሎች ሁሉ ከፍተኛ ተጽእኖ አለው።

መሪው ናስራላህ ከሊባኖስ ባሻገር በሌሎችም የአረብ አገራት ታዋቂ ሲሆኑ፣ ሒዝቦላህ በሊባኖስ መንግሥት መዋቅር ውስጥ ሥልጣን እንዲኖረው በማስቻል ቁልፍ እና ታሪካዊ ሚና ተጫውተዋል።

ናስራላህ ከኢራን እስራላማዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እና ከመሪው አያቶላህ አሊ ኻሚኒ ጋር ልዩ ግንኙነት አላቸው። ምንም እንኳን ሒዝቦላህ በአሜሪካ ሽብርተኛ ድርጅት ቢባልም፣ ኢራን እና ናስራላህ ያላቸውን ጥብቅ ግንኙነት ደብቀው አያውቁም።

ሐሰን ናስራላህ በፍቅር የሚከተሏቸው ደጋፊዎች ያሏቸውን ያህል አደገኛ ጠላቶችም ይከተሏቸዋል።

በዚህም ምክንያት በእስራኤል ሊፈጸምባቸው ከሚችል ግድያ ለመሸሽ ለዓመታት ከሕዝብ ዕይታ ርቀው ቆይተዋል። ያሉበት ባይታወቅም በየሳምንቱ ግን ለተከታዮቻቸው ንግግሮችን ያደርጋሉ። በዚህም ናስራላህ በሊባኖስ እና በዓለም ላይ ስላሉ ጉዳዮች አስተያየት በመስጠት ሥልጣናቸውን ከማሳየት ባሻገር በተቀናቃኞቻቸው ላይ ጫናን ይፈጥራሉ።

ወታደሮች
የምስሉ መግለጫ,ናስራላህ ከተወለዱ ከአጭር ጊዜ በኋላ ነበር በሊባኖስ ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት የተቀሰቀሰው

ልጅንት እና ጉልምስና

ሐሰን ናስራላህ በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ምሥራቃዊ ክፍል ውስጥ በሚገኝ የድሆች መኖሪያ ሰፈር ውስጥ በነሐሴ 1960 (እአአ) ነበር የተወለዱት። አባታቸውም የትንሽዬ ግሮሰሪ ባለቤት የነበሩ ሲሆን፣ ናስራላህ ቤተሰባቸው ካለው ዘጠኝ ልጆች የመጀመሪያው ናቸው።

ናስራላህ የአምስት ዓመት ሕጻን ሳሉ ሊባኖስን ክፉኛ ያፈራረሳት ሃይማኖት እና ጎሳን መሠረት ያደረገው የ15 ዓመቱ የእርስ በርስ ጦርነት ሲጀመር፣ አባታቸው ቤይሩትን ለቀው ሺዓዎች ወደ ሚኖሩበት የአያት ቅድመ አያቶቻቸው መንደር ወዳለበት ደቡብ ሊባኖስ አቀኑ።

የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም ከሺዓዎች ጋር በደቡብ ሊባኖስ ተከታትለዋል። ሺዓዎች በኦቶማኖች እና በፈረንሳዮች የቅኝ ግዛት ዘመን ተገልለው መድልዎ ይደረግባቸው እንደነበር ይሰማቸዋል። ከነጻነት በኋላ የክርስቲያን እና የሱኒ ልሂቃን ሥልጣን ሲይዙ ይኸው ስሜት አብሯቸው ዘልቋል።

ከሊባኖስ ነጻነት በኋላ ባለው ጊዜ የክርስቲያን እና የሱኒ ሚሊሻ ቡድኖች ወታደራዊ የበላይነትን እንዲያገኙ የውጭ አገራትን እርዳታ ያገኛሉ በሚል ይከሰሱ ነበር።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሐሰን ናስራላህ ፊታቸውን ወደ ሺዓ ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን ወደ ጎሳ ማንነታቸው ፊታቸውን አዞሩ። በ15 ዓመታቸውም በኢራናዊው ሙሳ አል-ሳድር የተመሠረተው እና በወቅቱ በአገሪቱ ዋነኛ የሺዓ ፖለቲካዊ-ወታደራዊ ቡድን የሆነው አማል እንቅስቃሴ አባል ሆኑ።

ሐሰን ናስላራህ (ከመሃል) ኢራቅ ናጃፍ ውስጥ ከአባስ ሙሳቪ (ከቀኝ) ጋር በተገናኙበት ወቅት
የምስሉ መግለጫ,ሐሰን ናስላራህ (ከመሃል) ኢራቅ ናጃፍ ውስጥ ከአባስ ሙሳቪ (ከቀኝ) ጋር በተገናኙበት ወቅት

ስደት እና ወደ ሊባኖስ መመለስ

ሐሰን ናስራላህ በ16 ዓመታቸው ከሊባኖስ በመውጣት ወደ ኢራቋ ናጃፍ ተሰደው ነበር።

በወቅቱ ለተከታታይ ዘመናት መረጋጋት ርቋት የነበረችው ኢራቅ በአብዮቶች፣ በደም አፋሳሽ መፈንቅለ መንግሥቶች እና በፖለቲካዊ ግድያዎች እየተናጠች ነበረ። ሳዳም ሁሴን ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩ ቢሆንም በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ተጽእኖ ነበራቸው።

ሐሰን ናስራላህ ለሁለት ዓመታት ኢራቅ ውስጥ ከቆዩ በኋላ ሳዳም ሁሴን እና ፓርቲያቸው ባዝ ተጨማሪ እርምጃዎችን በመውሰድ የሺዓ ሙስሊሞችን ለማዳከም ውሳኔ ላይ ደረሱ። ከውሳኔያቸው አንዱም በኢራቅ የሃይማኖት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ የሊባኖስ ሺዓዎችን ከአገሪቱ ማባረር ነበር።

ናስራላህም ኢራቅን ከአጭር ጊዜ ቆይታ በኋላ ለመልቀቅ ቢገደዱም፣ በሕይወታቸው ላይ ጉልህ ተጽእኖ የነበራቸውን እና በኢራን ሃይማኖታዊ መሪዎች አስተምህሮ የተቀረጹትን አባስ ሙሳቪ የተባሉትን የሃይማኖት አባት ናጃፍ ውስጥ አግኝተዋል።

ወደ ሊባኖስ ከተመለሱ በኋላ ሁለቱ ሰዎች በእርስ በርስ ጦርነቱ ውስጥ መሳተፍ ጀመሩ። በወቅቱም ናስራላህ የአባስ ሙሳቪ የትውልድ አካባቢ ወደ ሆነው የቤካ ሸለቆ በመሄድ ሃይማኖታዊ ጥናት ማካሄድ ጀምረው ነበር።

ናስራላህ በሊባኖስ የኢራን የሃይማኖት ጉዳዮች ተወካይ ሆነው ተሹመው ነበር
የምስሉ መግለጫ,ናስራላህ በሊባኖስ የኢራን የሃይማኖት ጉዳዮች ተወካይ ሆነው ተሹመው ነበር

የኢራን አብዮት እና የሒዝቦላህ መመሥረት

ሐሰን ናስራላህ ወደ ሊባኖስ ከተመለሱ ከዓመት በኋላ ኢራን ውስጥ አብዮት ተካሄደ። በአባስ ሙሳቪ እና በሐሰን ናስራላህ ዘንድ የሚደነቁት ሩሆላህ ኾሚኒ የኢራንን የመሪነት ሥልጣን ጨበጡ። ይህም ክስተት በሊባኖስ ሺዓዎች እና በኢራን መካከል ያለውን ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ ለወጠው። በተጨማሪም የሊባኖስ ሺዓዎች የፖለቲካ ሕይወት እና የትጥቅ ትግል በኢራን በተካሄዱ ለውጦች እና በሺዓ እስላማዊነት ርዕዮተ ዓለም ተጽእኖ መመራት ጀመሩ።

በ1981 (እአአ) ናስራላህ በወቅቱ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መሪ ከነበሩት ኾሚኒ ጋር ቴህራን ውስጥ ተገናኝተዋል። በተጨማሪም ሊባኖስ ውስጥ ለእርዳታ እና ለበጎ ሥራዎች የኢራን ተወካይ እንዲሆኑ ሾመዋቸዋል።

ናስራላህ በተለያዩ ጊዜያት ወደ ኢራን ጉዞ ያደረጉ ሲሆን፣ በዚህም በአገሪቱ የመንግሥት ሥልጣን ውስጥ ከፍተኛ ውሳኔ ከሚያሳልፉ ሰዎች ጋር ግንኙነትን መፍጠር ችለዋል።

በኢራን ሥልጣን በጨበጡት በሺዓ መሪዎች ዘንድ ፀረ-ምዕራባውያን እና ፀረ-እስራኤል የሆነ አመለካከት እና ፖሊሲ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የመጣ ሲሆን፣ ከዚያም “የፍልስጥኤማውያን ጥያቄ” በአብዮታዊት ኢራን የውጭ ፖሊሲ ላይ ከሁሉም የላቀ ቦታን ይዟል።

በዚያ ወቅትም ሊባኖስ በጦርነት እና ባለመረጋጋት ውስጥ ሆና፣ ለፍልስጤማውያን ተዋጊዎች ዋነኛዋ መጠለያ ሆነች። ከቤይሩት በተጨማሪም በደቡባዊ ሊባኖስ ጠንካራ ይዞታ ነበራቸው።

በሊባኖስ ውስጥ አለመረጋጋቱ እየተባባሰ በነበረበት ጊዜ በ1982 (እአአ) እስራኤል በፍልስጤማውያን ወረራ ተፈጸመብኝ በማለት በሊባኖስ ላይ ጥቃት ሰንዝራ፣ የአገሪቱን ሰፊ ግዛቶች በቁጥጥሯ ስር አስገባች።

የእስራኤልን ጥቃት ተከትሎ ኢራን ከኢራቅ ጋር በነበራት ጦርነት ወቅት በመደበኛ ውጊያ ሰፊ ልምድ ያዳበሩት የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጓድ አዛዦች ከአገራቸው ጋር ግንኙነት ያለው የሚሊሻ ቡድን በሊባኖስ ውስጥ ለመመሥረት ወሰኑ። የቡድኑንም ስም እነሱ ኢራን ውስጥ በቅጽል ስምነት የሚጠሩበትን “ሒዝቦላህ” (የፈጣሪ ፓርቲ) ብለው ሰየሙት።

በ1985 (እአአ) ሒዝቦላህ መመሥረቱን በይፋ አስታወቀ። ሐሰን ናስራላህ እና አባስ ሙሳቪ ከሌሎች የአማል እንቅስቃሴ አባላት ጋር በመሆን አዲሱን ቡድን ተቀላለቀሉ። በወቅቱም ሱብሂ አል-ቱፋያህ በተባለ ግለሰብ ነበር የሚመራው።

ሒዝቦላህ ከተመሠረተ ብዙም ሳይቆይ በሊባኖስ ውስጥ በሚገኙ የአሜሪካ ኃይሎች ላይ ጥቃት በመፈጸም በቀጠናው ፖለቲካ ውስጥ በፍጥነት ስሙን ተከለ።

ናስራላህ ሁልጊዜም ለኢራን ያላቸውን ታማኝነት ለማሳየት ይሞክራሉ
የምስሉ መግለጫ,ናስራላህ ሁልጊዜም ለኢራን ያላቸውን ታማኝነት ለማሳየት ይሞክራሉ

ጉዞ ወደ ሒዝቦላህ መሪነት

ናስራላህ ሒዝቦላህን ሲቀላቀሉ ገና የ22 ዓመት ወጣት ነበሩ። በ80ዎቹ አጋማሽ ላይ ከኢራኖች ጋር የነበራቸው ግንኙነት እየተጠናከረ ሄዶ፣ ለሃይማኖታዊ ትምህርት ወደ ኢራን አቅንተው የፋርስ ቋንቋን አቀላጥፈው መናገር በመቻል ከኢራን ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ መሪዎች ጋር የቅርብ ወዳጅነት ለመመሥረት ችለዋል።

ወደ ሊባኖስ ሲመለሱም በናስራልህ እና በአባስ ሙሳቪ መካከል ጉልህ አለመግባባት ተፈጠረ። በወቅቱ ሙሳቪ በሃፊዝ አል አሳድ የምትመራው ሶሪያ፣ በሊባኖስ ውስጥ ከፍ ያለ ሚና እንዲኖራት ይደግፍ ነበር። ናስራልህ ደግሞ ሒዝቦላህ በአሜሪካ እና በእስራኤል ወታደሮች ላይ ጥቃት በመፈጸም ላይ ማተኮር አለበት ይሉ ነበር።

በቡድኑ ውስጥ ደጋፊ ያጡት ናስራላህ ብዙም ሳይቆዩ “በኢራን የሒዝቦላህ ተወካይ” ተብለው ተሾሙ። ይህም ናስራላህ ወደ ኢራን እንዲሄዱ እና ከሊባኖስ ፖለቲካ እንዲርቁ አደረጋቸው።

ምንም እንኳን ኢራን ለሒዝቦላህ አጠቃላይ ድጋፍ ብትሰጥም በወቅቱ በቡድኑ ውሳኔዎች ላይ ተጽእኖ ማሳደር ግን አዳግቷት ነበር። ውጥረቱም ተባብሶ በ1991 (እአአ) ሱቢህ አል-ቱፋይሊዋስ ቡድኑ ከኢራን ጋር ያለውን ቅርርብ በመቃወም በያዘው አቋም ከዋና ፀሐፊነት ተነስቶ በአባስ ሙሳቪ ተተካ።

በቡድኑ ውስጥ ከተካሄደው ለውጥ በኋላ ሐሰን ናስራላህ ወደ ሊባኖስ ተመልሰው የቡድኑን ምክትል መሪነት ቦታ ለመያዝ ቻሉ።

ናስራላህ የሒዝቦላህ ዋና ፀሐፊ የሆኑት በ32 ዓመት ዕድሜያቸው ነበር
የምስሉ መግለጫ,ናስራላህ የሒዝቦላህ ዋና ፀሐፊ የሆኑት በ32 ዓመት ዕድሜያቸው ነበር

የናስራላህ ወደ መሪነት መምጣት

አባስ ሙሳቪ የሒዝቦላህ ዋና ፀሐፊነትን ቦታ በያዙ ከዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በእሰራኤል ሰላዮች ተገደሉ። ይህም የመሪነቱ ቦታ በሐሰን ናስራላህ እጅ ላይ እንዲገባ ዕድል ፈጠረ።

የናስራላህ መሪ መሆን በብዙዎች ዘንድ ከኢራን ጋር ባላቸው ልዩ ትስስር ምክንያት እንደሆነ ይታመናል። በ32 ዓመታቸው የሂዝቦላህ መሪ የሆኑት ናስራላህ ከሺዓ መሪዎች አንጻር በሃይማኖታዊ ትምህርት ያልበቁ በመሆናቸው ትምህርታቸውን ከመሪነት ኃላፊነታቸው ጋር ጎን ለጎን ማስኬድ ጀመሩ።

ሐሰን ናስራላህ ወስደዋቸዋል ከሚባሉ ወሳኝ እርምጃዎች መካከል የተወሰኑ የሒዝቦላህ ደጋፊዎች እና አባላት በሊባኖስ ምርጫ ውስጥ ዕጩ ሆነው እንዲቀርቡ ማድረጋቸው ነው።

በሊባኖስ ይካሄድ የነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ሲያበቃ፣ ናስራላህ የሒዝቦላህ ፖለቲካዊ ክንፍ ከወታደራዊ ክንፉ ጋር በመሆን በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ዋነኛ ሚና እንዲጫወት ወሰኑ። በዚህም ምክንያት ቡድኑ በሊባኖስ ፓርላማ ውስጥ ስምንት መቀመጫዎችን ለማሸነፍ ቻለ።

ነገር ግን የሒዝቦላህ ቡድን የሽብር ጥቃቶችን በማቀድ እና በመፈጸም ይከሰስ ነበር። በወቅቱም በአርጀንቲና በሚገኙት የአይሁዶች ማዕከል እና የእስራኤል ኤምባሲ ላይ የቦምብ ጥቃት ተፈጽሞ ነበር።

በተጨማሪም የሊባኖስን የእርስ በርስ ጦርነትን ባስቆመው በሳዑዲ አሸማጋይነት በተደረሰው ስምምነት መሠረት ሒዝቦላህ የታጠቀውን የጦር መሳሪያ ይዞ እንዲቆይ ተወስኖ ነበር።

ቡድኑ ከኢራን በሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ ናስራላህ ለሺዓዎች የእርዳታ እና የማኅበራዊ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች እና ሌሎች የበጎ አድራጎት ተቋማትን ለማቅረብ ችለዋል። ይህ የናስራላህ ተግባርም በሊባኖስ ወስጥ የሺዓ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ዋነኛ ገጽታ ሆኖ አሁን ድረስ ቀጥሏል።

በናስላራህ አመራር ስር ሒዝቦላህ በከፍተኛ ደረጃ ተጽእኖ ፈጣሪ ለመሆን ችሏል
የምስሉ መግለጫ,በናስላራህ አመራር ስር ሒዝቦላህ በከፍተኛ ደረጃ ተጽእኖ ፈጣሪ ለመሆን ችሏል

የእስራኤል መውጣት እና የናስራላህ ዝና

በአውሮፓውያኑ 2000 እስራኤል በወረራ ይዛው ከነበረው ከደቡበ ሊባኖስ ሙሉ ለሙሉ ለቃ እንደምትጣ ስታሳውቅ፣ ሒዝቦላህ ይህንን እንደ ራሱ ታላቅ ድል የወሰደው ሲሆን ናስራላህም አድናቆትን አግኝተውበታል።

እስራኤል በፈቃዷ ያለምንም ድርድር ከሊባኖስ ግዛት ብትወጣም ሒዝቦላህ ትጥቁን እንዳነገተ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ኃያል ሆኖ እስካሁን ድረስ አለ። ኋላ ላይ ደግሞ ከእስራኤል ጋር በተደረገ ድርድር ናስራላህ ከ400 በላይ ፍልስጤማውያን፣ ሊባኖሳውያን እና የሌሎች አረብ አገራት እስረኞችን ለማስለቀቅ ችለዋል።

በዚህ ጊዜም ናስራላህ ከምንጊዜውም በላይ ኃያል እና ተጸእኖ ፈጣሪ ሆነው ታዩ፣ በዚህም ሳቢያ የሊባኖሰ የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸው ናስራልህን ለመገዳደር እና በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ እየሰፋ የመጣውን ተጽእኗቸውን ለመከላከል ከባደ ፈተና ገጠማቸው።

እምብዛም በአደባባይ የማይታዩት ናስራላህ ጥብቅ ጥበቃ ይደረግላቸዋል
የምስሉ መግለጫ,እምብዛም በአደባባይ የማይታዩት ናስራላህ ጥብቅ ጥበቃ ይደረግላቸዋል

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ግድያ እና የሶሪያ መውጣት

በ2005 (እአአ) የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር መገደል በሕዘቡ አመለካከት ላይ ለውጥን አስከተሏል። ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የቀረበ ግነኙነት የነበራቸው የተገደሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ራፊክ ሐሪሪ የሒዘቦላህን ኃያል እየሆነ መምጣተ ለመከላከል ሰፊ ጥረት ሲያደርጉ ነበረ።

በግድያው ምክንያት በሊባኖስ አና በሶሪያ ያሉ ደጋፊዎቹን ጨምሮ ሒዝቦላህ በግድያው እጃቸው አለበት በሚል የሕዝቡ ቁጣ በሒዝቦላህ ላይ በርትቶ ነበር። ተቃዋሚዎች ቤይሩት ውሰጥ በጣም ብዙ ሕዝብ የተሳታፈበት ሰልፍ ኣካሄዱ ሲሆን በዚህም ሳቢያ ሶሪያ በአገሪቱ ያሉ ወታደሮቿን እንደምታስወጣ አስታውቃ ነበር።

ነገር ግን በዚያው ዓመት በተካሄደው የፓርላማ ምርጫ ሒዝቦላህ ያገኘው መቀመጫ መጨመሩ ብቻ ሳይሆን፣ ሁለት አባላቱ በመንግሥት ውስጥ ሁለት የሚኒስትርነት ቦታዎችን ለመያዝ በመቻላቸው ጉልበት እያገኘ መጣ።

በ2006 (እአአ) ደግሞ ሒዝቦላህ ወደ እስራኤል ዘልቆ በመግባት አንድ ወታደር በመግደል ሁለት ወታደሮችን አግቶ ሄደ። በዚህ ድርጊት የተቆጣችው እስራኤል ለ33 ቀናት በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ 1,200 የሚጠጉ ሊባኖሳውያን ተገድለዋል።

በዚህም ሳቢያ የናስራላህ ታዋቂነት የጨመረ ሲሆን፣ በአረቡ ዓለምም ናስራላህ እስራኤልን በመጋፈጥ የመጨረሻው ሰው ተደርገው ቀርበዋል።

ናሰራላህ በአሁኑ ጊዜ በሊባኖስ ውስጥ ዋነኛው ታዋቂ የሆኑ የሺዓ መሪ ናቸው
የምስሉ መግለጫ,ናሰራላህ በአሁኑ ጊዜ በሊባኖስ ውስጥ ዋነኛው ታዋቂ የሆኑ የሺዓ መሪ ናቸው

ኃያልነት እና የናስራላህ ሥልጣን መጠናከር

የሒዝቦላህ ሥልጣን እና ኃይል እየጨመረ ሲሄድ ተቀናቃኝ የሊባኖስ ቡድኖች በተለይም ሱኒ ፖለቲከኞች፣ ሒዝቦላህ በመንግሥት ውስጥ መንግሥት መሥርቷል በማለት የአገሪቱን ደኅንነት እና ምጣኔ ሃብት ያዳክማል ሲሉ ስጋታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።

ለወራት ከቆየ ፖለቲካዊ ሽኩቻ በኋላ በ2007 (እአአ) የሊባኖስ መንግሥት በሒዝቦላህ ቁጥጥር ስር የነበሩ የቴሌኮምዩኒኬሽን ሥርዓቶች በሙሉ በመንግሥት ስር እንዲሆኑ ወሰነ። ናስራላህ ግን ይህንን ውሳኔ ከመቃወማቸው ባሻገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ታጣቂዎቻቸው ዋና ከተማዋ ቤይሩትን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ስር አስገቡ።

ይህ እርምጃም በናስራላህ ላይ ከምዕራባውያን በኩል ሰፊ ትችትን አስከትሏል። ነገር ግን ፖለቲካዊ ድርድሮች ከተደረጉ በኋላ ሒዝቦላህ በአገሪቱ ካቢኔ ውስጥ ያለው ሥልጣን እንዲጨምር ከማድረግ በላይ በካቢኔው ውሳኔ ላይ ድምጽን በድምጽ የመሻር ሥልጣንን አግኝቷል። ከዚያም በኋላ የናስራላህ ቡድን እንደታጠቀ እንዲቆይ የሚስችል ስምምነት ተደርሷል።

በዚህ የተነሳ ሐሰን ናስራላህ በሊባኖሰ ውስጥ ያለ የትኛውም ፖለቲከኛ ከአገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ላይ ሊያስወግዳቸው ወይም ተጽእኗቸውን ሊቀንስባቸው የሚችልበት አቅም የለውም።

ናስራላህ በሊባኖስ ወስጥ ለዓመታት የገነቡት ኃያልነትን የአገሪቱ ፖለቲከኞችም ሆኑ የሌሎች አገራት ኃያልን መንግሥታት ሊገዳደሩት ወይም ገለል ሊያደርጉት ከማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሷል።

ሐሰን ናስራላህ ሒዝቦላህን በመሩባቸው ከሦስት አስርት ዓመታት በሚበልጠው ጊዜ ውስጥ ከኢራን በሚያገኙት ድጋፍ የአረብ አብዮትን፣ የሶሪያን የእርስ በርስ ጦርነት እና በሊባኖስ ያለውን የምጣኔ ሃብት ቀውስን የመሳሰሉ ታሪካዊ ቀውሶችን ለማለፍ ችለዋል።

አሁን 63 ዓመት የሆናቸው ናስራላህ በሊባኖስ ውስጥ ለየት ያሉ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ኃይል ሆነው ከመታየታቸው በተጨማሪ ለአስርታት በትግል ላይ መቆየታቸውን ይነሳል።