November 4, 2023 – Konjit Sitotaw 

የኢትዮጵያ የውጭ ብድር የመክፈል አቅም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ተቀመጠ

መቀመጫውን በኒው ዮርክ ያደረገውና የመንግሥታትን ብድር የመመለስ አቅም በመገምገም ደረጃ ከሚያወጡ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው ፊች ሬቲንግስ፤ የኢትዮጵያን የውጭ ብድር የመክፈል አቅም ከዚህ ቀደም ከሰጠው የምዘና ደረጃ ዝቅ አድርጓል።

ዓለም አቀፍ የብድር ምዘና ኤጀንሲ የሆነው ተቋም፤ ትናንት ይፋ ባደረገው ሰነድ የኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ አከፋፈል ምን ሊመስል እንደሚችል ትንበያ አስቀምጧል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያን የሚጠበቅባትን ብድር ሳትከፍል የመቅረት ዕድል ከዚህ ቀደም ከነበረው ከሲሲሲ ማይነስ (CCC_) ወደ ሲሲ (CC) ዝቅ ማለቱን አስታውቋል።

እንደ ፌች ግምት ከሆነ ኢትዮጵያ በቀጣዩ ሐምሌ ወር በሚጠናቀቀው እና አሁን በተያዘው የበጀት ዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር ገደማ የውጭ ዕዳ ክፍያ ይጠበቅባታል። ይኸው ክፍያው በፈረንጆቹ 2025 የበጀት ዓመት ወደ 2 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ሊል እንደሚችልም ተቋሙ ግምቱን አስቀምጧል፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ የመክፈል አቅም ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያት፤ ብድር እና ቦንድን የመሳሰሉ የገንዘብ ፍስሰት ምንጮች መቀነስ እንዲሁም በሚፈለገው እና ባለው ፋይናንስ ላይ ያለው ክፍተት መስፋት መሆኑን ተገልጿል፡፡

ይህም የደረጃ ዝቅ ማለት አገሪቷ በገንዘብ እጥረት የመፈተን ዕድሏን የሚያመላክት መሆኑንም ማስታወቁን አዲስ ማለዳ ተቋሙ ካወጣው መረጃ ተመልክታለች፡፡

ተቋሙ ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ክፉኛ እየተደቆሰች መሆኑን በማንሳት፤ በአሁኑ ሰዓት ያላት የውጭ ምንዛሬ ክምችት ከአንድ ወር የማይዘልል እንደሆነም አመላክቷል፡፡

በዚህም አገሪቷ ለዕዳ ክፍያ የምታወጣውን ዳጎስ ያለ ክፍያ ተሸክማ እስከቀጠለች እና የውጭ የፋይናንስ ምንጮች ለማግኘት የተቀላጠፈ ስኬትን እስካላስመዘገበች ድረስ፤ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ እየተባበሰ ሊቀጠል ይችላል ሲል ጠቁሟል፡፡

ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) እና ከሌሎችም ዓለም አቀፍ ምንጮች የፋይናንስ ድጋፍን ለማግኘት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ረዘም ያለ ጊዜን መውሰዳቸው፤ ለዚህ ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ተቋሙ ግምቱን አስቀምጧል፡፡

በኦፊሴላዊው የውጭ ምንዛሬ ምጣኔ እና ኢመደበኛ በሆነው የምንዛሬ ገበያ መካከል ያለው ልዩነት እጅግ መስፋቱ ይፋዊውን ምጣኔ በከፍተኛ ደረጃ ለማሻሻል ዕድል እንዳለ ያሳያል የሚለው ተቋሙ በአገር ውስጥም ቢሆን ኢትዮጵያ በፋይናንስ ምንጭነት በባንክ ዘርፉ ላይ መንጠልጠሏ እየጨመረ መሄዱን አመላክቷል፡፡

ዓለም አቀፍ የብድር ምዘና ኤጀንሲ በፈረንጆቹ 2023 የዋጋ ግሽበት መጠኑ በአማካይ ከ32 በመቶ በላይ ነው ያለ ሲሆን፤ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲውን ለመቆጣጠር እርምጃ በሚወስድበት ወቅት የምጣኔ ኃብት ፈተናዎች ሊኖሩ ይችላሉ ሲልም ጠቁሟል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የካፒታል ገበያን መልሳ እንድታገኝ እና ኢኮኖሚያዊ ተስፋዋን እንድታሳድግ፤ በአገሪቷ እየተካሄደ ያለውን የእርስ በእርስ ጦርነት መፍታት እንዲሁም የፋይናንስ ክፍተቶችን ማስተካከል ይገባታል ሲል ተቋሙ አሳስቧል፡፡