November 4, 2023 – Konjit Sitotaw
በሶማሌ ክልል በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ከ20 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ተገለጸ
በሶማሌ ክልል ሰሞኑን እየዘነበ በሚገኘው ከባድ ዝናብ ሳቢያ በተለያዩ አካባቢዎች ከባድ የጎርፍ አደጋ መከሰቱን የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ቢሮ አስታውቋል፡፡
በቢሮው የቅድመ ማስጠንቀቂያ አስተባባሪ በሺር አረፕ በጎርፍ አደጋው እስካሁን ከ20 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን የገለጹ ሲሆን፤ ከ12 ሺሕ በላይ አባወራዎች መፈናቀላቸውንም ተናግረዋል።
በተጨማሪም በእንስሳት ሀብት፣ በሰብል እና በንብረት ላይም ጉዳት መድረሱን መግለጻቸውን ኢብኮ ዘግቧል።
የሶማሌ ክልል መንግሥት እና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ግብረሰናይ ድርጅቶች የዕለት ደራሽ እርዳታዎችን ለማድረስ እየሰሩ ቢሆንም፤ ድልድዮችና መንገዶች በጎርፉ በመወሰዳቸው ሥራውን አስቸጋሪ ማድረጉን የቢሮው አስተባባሪ ተናግረዋል።
እየጨመረ ያለው የዝናብ መጠን እና ትንበያዎች እንደሚያሳዩት የጎርፍ አደጋው ስጋት አሁንም ከፍተኛ ነው።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በቀጣዮቹ አስር ቀናት አንዳንድ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፤ በጥቂት ስፍራዎቻቸው ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖርም ማስታወቁን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል፡፡