በትግራይ ክልል 1 ሺሕ 329 ያህል ተፈናቃዮች በምግብ እጥረት ብቻ መሞታቸው ተገለጸ
ከ1 እስከ 5 ዓመት ዕድሜ ያላቸው 970 ተፈናቃይ ሕፃናት ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል
ቅዳሜ ጥቅምት 24 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በትግራይ ክልል በ5 ከተሞች በሚገኙት 53 የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎቸ እንደ ናሙና ተወስዶ በተደረገ ጥናት፣ በሌሎች ምክንያቶች የሞቱ ሰዎችን ሳይጨምር ቢያንስ 1 ሺኽ 329 ተፈናቃዮች በምግብ እጥረት ብቻ መሞታቸው ተገልጿል።
በምግብ ድጋፍ መቋረጥ ሳቢያ እና ተያያዥ ምክንያቶች በትግራይ ክልል ቁጥራቸው ከፍ ያለ ተፈናቃዮች መሞታቸውን እና በሞት አፋፍ ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የዚህን ጥናት ግኝት ኢሰመኮ በራሱ ምርመራ ያረጋገጠው ባይሆንም የጉዳዩን ከፍተኛ አሳሳቢነት የሚያሳይ መሆኑን ጠቁሟል።
በክልሉ ኮሚሽኑ በአካል ተገኝቶ ክትትል ባደረገባቸው አካባቢዎች ለተፈናቃዮች የመጨረሻው የምግብ ድጋፍ የቀረበው በጥር ወር 2015 መሆኑ የገለጸ ሲሆን፤ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ በመጋቢት ወር 2015 መሆኑን አመላክቷል።
በተጨማሪ ቁጥራቸው 970 የሆኑ ከ1 እስከ 5 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃይ ሕፃናት ለከፍተኛ የምግብ እጥረት (Malnutrition) መጋለጣቸው በተከናወነ የልየታ ሥራ መረጋገጡን ገልጿል፡፡
ሕጻናቱም በተወሰኑ የጤና ተቋማት እና የተራድዖ ድርጅቶች በኩል ተጨማሪ አልሚ ምግቦችን እየወሰዱ በክትትል ላይ እንደሚገኙም ኮሚሽኑ አመላክቷል።
አብዛኞቹም አሳሳቢ በሚባል ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆኑን ኮሚሽኑ ከተፈናቃዮች፣ ከቤተሰብ አባላት፣ ከካምፕ አስተዳዳሪዎች፣ እንዲሁም ከአካባቢው የጤና ተቋማት ኃላፊዎች እና ከተራድዖ ድርጅቶች ተወካዮች ማረጋገጡን ገልጿል፡፡
ምልከታ በተደረገባቸው መጠለያ ጣቢያዎች እና አካባቢዎች በተለይም ሕፃናት፣ አረጋውያን፣ የሚያጠቡ እናቶች፣ አካል ጉዳተኛ እና ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸው ተፈናቃዮች ለከፍተኛ የምግብ እጥረት መጋለጣቸውንም ጠቁሟል።
በዚህም የተነሳ በተለይ ሕፃናት እና አረጋውያን ቀን ላይ ከመጠለያ ውጭ በከተሞች ውስጥ እየተዘዋወሩ ምግብ ለምነው ማታ ወደ መጠለያ ጣቢያ የሚመለሱ መሆኑን፣ ወጣቶች ለስደት እና ሌሎች አሉታዊ ውጤት የሚያስከትሉ የገቢ ማግኛ አማራጮች ላይ ለመሰማራት መገደዳቸውን አዲስ ማለዳ ኮሚሽኑ ካወጣው ሪፖርት ተመልክታለች።
እንዲሁም በመጠለያ ጣቢያዎች በተከፈቱ የሕፃናት መማሪያ ማእከላት ትምህርት ሲከታተሉ የነበሩ አብዛኞቹ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውም ገልጿል።
በተመሳሳይም ኮሚሽኑ በሪፖርቱ የአፋር፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ዙምዝ እና ሶማሌ ክልሎችን አሁናዊ ኹኔታ በሚመለከት መረጃዎችን ያወጣ ሲሆን፤ በክልሎቹ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የሚቀርበው የምግብ ድጋፍ በቂ፣ ተደራሽ እና ወቅቱን የጠበቀ እንዳልሆነ፤ እንዲሁም ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ የሚቀርብ እንዳልሆነ ገልጿል።
ነሐሴ ወር 2015 የዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት መድረስ የቻላቸውን አካባቢዎች መሠረት አድርጎ ባወጣው ሪፖርት በአፋር ክልል 290 ሺሕ የሚሆኑ፣ በትግራይ ክልል 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ፣ በአማራ ክልል 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን እንዲሁም በኦሮሚያ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች እና ተመላሾችን የሚያስተናግዱ ክልሎች መሆናቸውን ገልጿል።